ትግራይ ክልል የ3 ወራት ደሞዝ ተከፈለ
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 12 2015ላለፉት 22 ወራት ደሞዝ ሳያገኙ ቆይተው የነበሩ በትግራይ ክልል የሚገኙ የመንግስት ሠራተኞች የ3 ወራት ክፍያ እየተሰጣቸው መሆኑ ገለፁ ። ደሞዛቸው ማግኘት መጀመራቸው በአወንታ ያነሱት የክልሉ የመንግስት ሠራተኞች ለረዥም ጊዜ ያልተከፈላቸውን ውዝፍ ክፍያ አለማግኘታቸው ግን ቅሬታ ፈጥሮባቸዋል ። የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ቀሪ የመንግስት ሠራተኞች ውዝፍ ክፍያ እንዲያገኙ ጥረት እንደሚያደርግ ገልጿል ። ከዚህ ውጭ ከሥራ ገበታቸው ውጭ ያሉ የመንግስት ሠራተኞች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ጥሪ ቀርቦላቸዋል ።
ላለፊት 22 ወራት መደበኛ ደሞዛቸው ሳያገኙ ቀርተው የነበሩ በትግራይ የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች፣ በቅርቡ በተቋቋመው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በኩል ከረዥም ግዜ በኃላ ደሞዝ መቀበል ስለመጀመራቸው ገልፀውልናል። በትግራይ የሚገኙ የክልሉ መንግስት የመንግስት ሰራተኞች ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ እየተቀበሉት ያለው ደሞዝ የ2015 ዓመተምህረት የጥር፣ የካቲት እና መጋቢት ወራት መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ይጠብቁት የ22 ወር ውዝፍ ክፍያ አለመለቀቁ ግን ቅሬታ ፈጥሮባቸዋል። ያነጋገርናቸው የመንግስት ሰራተኛ አቶ አባዲ ደስታ "መንግስት ሰራተኛው ዕዳ ላይ ነው የቆየው፣ የኑሮ ውድነቱ ከፍቷል፣ስለዚህ ይህ ለመደገፍ ውዝፍ ክፍያው ሊያገኝ ይገባል" ብለዋል።
በመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ክፍያ እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ዙርያ መግለጫ የሰጡት የትግራይ ክልል ፋይናንስ እና ሀብት ማሰባሰብ ቢሮ ሐላፊ ወይዘሮ ምሕረት በየነ እስካሁን ለመንግስት ሰራተኛው የተፈቀደው ክፍያ የሶስት ወራት ብቻ መሆኑ አንስተው የቀረው ለማግኘት ጥረት ይደረጋል ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ በቅርቡ የተቋቋመው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ስራ ላይ ያልነበሩት የክልሉ የመንግስት ሰራተኞች በመጪዎቹ አስር ቀናት ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ ጥሪ አድርጓል።
በሕወሓት እና በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ይሁንታ የተመሰረተው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር 27 አባላት ያሉት ካቢኔ አዋቅሮ ወደ ስራ የገባው ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ