ትግራይ ክልል ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ያስከተለው የምሁራን ፍልሰት
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 9 2017ከፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት በኋላ ባለው ጊዜ በርካታ ሐኪሞች፣ መምህራ እና ሌሎች ባለሞያዎች ከትግራይ ክልል ወደ ተለያዩ አካባቢዎች እየተሰደዱ ነው ተባለ ። የትግራይ ጤና ባለሞሙያዎች ማኅበር ባደረገው ጥናት እንዳመለከተው፦ ስፔሻላይዝድ ዶክተሮችን ጨምሮ ከ900 በላይ የጤና ባለሞያዎች በአጭር ግዜ ውስጥ ትግራይ ክልልን ለቅቀው ሄደዋል ። ከዚህ በተጨማሪ ከ14 ሺህ በላይ የሚሆኑ አስተማሪዎች በሥራቸው እንደሌሉም የትግራይ ትምህርት ቢሮ በቅርቡ ዐስታውቆ ነበረ ። ፖለቲካዊ ሁኔታ አለመረጋጋት፣ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ እና ሌሎች ምክንያቶች በርካቶች ትግራይ ክልልን ለቅቀው እንዲሄዱ ምክንያት ሆንዋል ተብሏል ። የመቐለ ወኪላችን፦ ሚሊዮን ኃይለሥላሴ ተጨማሪ ዘገባ አጠናቅሯል ።
ከሁለት ዓመቱ ጦርነት በኋላ በትግራይ አንፃራዊ ሰላም ቢሰፍንም፥ መቋጫ ያጣው ፖለቲካዊ ውጥረት እና ኢኮኖሚያዊ ውድቀት ተከትሎ በርካቶች ትግራይ ክልልን ለቅቀው የሚወጡበት እና እግራቸው ወደመራቸው የሚያመሩት ሁኔታ በስፋት ይስተዋላል። አሳሳቢ ደረጃ ላይ ከደረሰው የወጣቶች ሕገወጥ ስደት በተጨማሪ በርካታ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው የሕክምና ባለሞያዎች፣ መምህራን እና ሌሎች ሥራቸውን እየለቀቁ ከትግራይ ውጭ እየሄዱ መሆኑ ተገልጿል ። የትግራይ ጤና ባለሞያዎች ማኅበር በቅርቡ ይፋ ያደረገው የጥናት ግኝት እንደሚያመለክተው፥ ከፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት በኋላ እንዲሁም እስካለፈው ዓመት ጥር ወር ድረስ ባለው ግዜ ከዘጠኝ መቶ በላይ የሕክምና ባለሞያዎች ትግራይን ለቅቀው መሄዳቸው አመልክቷል። ይህ ከሥራቸው ለቅቀው ከትግራይ ውጭ የሄዱ የጤና ባለሞያዎች መጠን ከአጠቃላይ በትግራይ ያለው የሕክምና ባለሞያ 4 ነጥብ 5 በመቶ እንደሚደርስም የትግራይ ጤና ባለሙያዎች ማሕበር ሊቀመንበር ዶክተር ፍስሃ አሸብር ተናግረዋል።
የትግራይ የጤና ባለሙያዎች ማሕበር ሊቀመንበር ዶክተር ፍሰሃ አሸብር " እስካለፈው ጥር ወር ድረስ 86 ስፔሻሊስት ሐኪሞች ለቀው የሄዱ ሲሆን፣ 150 ጠቅላላ ዶክተሮች ጨምሮ ሌሎች በርካታ የጤና ባለሙያዎች በድምር 900 ባለሞያዎቻችን ከሥራ ለቅቆ ሄድዋል። ይህ ማለት ከአጠቃላይ ሐኪማችን 4 ነጥብ 5 በመቶ ከዚህ ሀገር ኮብልሏል። ካለፈው ዓመት ወዲህም ቢሆን እየጨመረ ነው እንጂ አልቀነሰም" ብለዋል።
ከዚህ ውጪ የትግራይ ትምህርት ቢሮ በቅርቡ እንዳስታወቀው በመማር ማስተማር ሂደት የነበሩ 14 ሺህ መምህራን አሁን ላይ የስራ ገበታቸው ላይ የሉም። የበርካታ ወራት ውዝፍ ደሞዝ አለመከፈል፣ የሚከፈለው ደሞዝም ቢሆን አነስተኛ መሆን እና የዋጋ ግሽበት ጫና አለመቋቋም እንዲሁም ሌሎች በርካታ ምክንያቶች መምህራን ጨምሮ ሌሎች የተማሩ ባለሙያዎች ከስራቸው እንዲለቁ እንዲሁም እንዲሰደዱ እየገፋቸው መሆኑ ተገልጿል። ከሽረ ከተማ ያነጋገርናቸው የሽረ መምህራን ማሕበር ሰብሳቢ መምህር ተክላይ በላይ ከአካባቢያቸው በርካታ መምህራን ስራቸው ለቀው ወደ ስደት መሄዳቸውን፣ በሊብያ ሌሎች ሀገራት በአጋቾች ተይዘውም ለከፍተኛ መከራ የተዳረጉ መኖራቸው ገልፀውልናል።
ይህን በትግራይ እየተበራከተ ያለው የምሁራን እና ባለሞሙያዎች ስደት ለመግታት ርምጃዎች እንዲወስዱ የትግራይ ጤና ባለሙያዎች ማሕበር ጥሪ ያቀርባል። የትግራይ ክልል አስተዳደር የምሁራንና ባለሙያዎች ጨምሮ የወጣቶች ስደት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ሲገልፅ ቆይቷል። የ17 ወራት ደሞዝ መንግስት አልከፈልንም ያሉ በትግራይ የሚገኙ መምህራን በበኩላቸው በማሕበራቸው በኩል በፌደራሉ እና የክልሉ መንግስት ላይ ክስ መመስረታቸው፥ የክሱም ሂደት ላይ እንዳለ መዘገባችን አይዘነጋም ።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ