1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኖተር ዳም፤ የዓለም የታሪክ የሥነ-ጥበብ የሃይማኖት ማኅደር

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 10 2011

ኖተር ዳም እንዲታደስ 700 ሚሊዮን ያስፈልጋል ሲባል ሕዝቡ መቶ ሚሊዮን ብቻ አዋጣ፤ በተሰበሰበዉ ገንዘብ እድሳቱ ጀመረ። አልዘለቀም ተቃጠለ። ከቃጠሎዉ በኋላ ከአንድ ቢሊዮን ዩሮ በላይ ተዋጣ። ታድያ ይህ የፈጣሪሥራ አይደለም? ይላሉ አንድዋ የኖተርዳም ምዕመን። ኖተር ዳም በ1991 ዓ.ም በዓለሙ የቅርስ በ«UNESCO» ተመዝግቦአል።

https://p.dw.com/p/3GzlW
Frankreich Paris | Brand der Kathedrale Notre-Dame de Paris
ምስል Getty Images/AFP/G. van der Hasselt

«ኖተር ዳም በ 1991 ዓ.ም ዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል »

« 700 ሚሊዮን ይሮ ሰብስበዉ ቤተ-ክርስትያኒቱን ለማደስ ፈልገዉ ነበር። ነገርግን የሚያዋጣ ጠፋ በአጠቃላይ ቤተ-ክርስትያኒቱን ለማደስ የተሰበሰበዉ ገንዘብ 100 ሚሊዮን ይሮ ብቻ ነበር። እንድያም ሆኖ እደሳዉ በተገኘዉ 100 ሚሊዮን ይሮ ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ተቃጠለ። ታድያ ከተቃጠለ በኋላ ለመልሶ ግንባታ 24 ሠዓት ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ ከአንድ ቢሊዮን ዩሮ በላይ ተዋጣ። ታድያ ይህ የፈጣሪ ስራ ነዉ ብዬ ነዉ የማምነዉ። እመቤታችን የራስዋን ቤት መሥራት ፈልጋ ነዉ ብዬ ነዉ ያልኩት። »

Frankreich Paris | Brand der Kathedrale Notre-Dame de Paris
ምስል Getty Images/AFP/Y. Herman

ለፓሪስዋ ነዋሪ ወ/ሮ ሂሩት፤ በኖተር ዳም ካቴድራል ማለት የፓሪሷ የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ-ክርስቲያን ላይ የደረሰዉ ክስተት ምናልባትም ከላይ ከፈጣሪ የመጣ ሊሆን ይችላል። 850 ዓመት የሞላዉን ቤተ-ክርስትያን ለማደስ ገንዘብ በመዋጮ ይሰብሰብ ተብሎ መቶ ሚሊዮን እንኳ አልደረሰም ነበር፤ እድሳቱ ጀመረ ፤ እድሳቱ በተጀመረበት ቦታ ዛሬ ዉድም ብሎ ተቃጠለ ብለዋል። እናማ አሁን ከቃጠሎዉ በኋላ በአንድ ቀን ጊዜ ዉስጥ ከአንድ ቢሊዮን ይሮ በላይ ለካቴድራሉ ግንባታ ተዋጣ። የፈረንሳይ ብሎም የዓለም ቱጃሮች ለእድሳቱና ለመልሶ ግንባታዉ ገንዘብ ሲሰጡ አብዛኞቹ ስማቸዉ እንዲጠቀስ እንኳ አይፈልጉም ተብሎአል። ጤና ይስጥልኝ አድማጮች እንደምን ሰነበታችሁ! ፓሪስ እምብርት ላይ የሚገኘዉ እና ቃጠሎ የደረሰበትን ኖተር ዳም ካቴድራል ወይም ፓሪስ የሚገኘዉ የፈረንሳዉያኑ የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ-ክርስትያን ታሪካዊ፤ ሃይማኖታዊ እና ሥነ-ጥበባዊ ገጽታዉን እንቃኛለን ።

በጎርጎረሳዉያኑ 1163 ተጀምሮ በ 1345 ዓ.ም ግንባታዉ የተጠቃለለዉ በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ እንብርት ላይ የሚገኘዉ የፈረንሳዉያኑ የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ-ክርስትያን  ኖተር ዳም ካቴድራል  የአንደኛ እና የሁለተኛ ዓለም ጦርነት ያልነካዉ የሰዉ ልጆች ጥበብ እድገትን ፖለቲካና ማኅበራዊ ኑሮ ታሪክን የያዘ ህንጻ እንደሆን ይነገርለታል። ፓሪስ ከተማን አየሁ ያለ፤ ይህን ካቴድራል የጎበኘ መሆን አለበት ሲሉ ፈረንሳዉያን ይናገራሉ። የፓሪስ ነዋሪዎችም ካለ ፓሪስዋ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ-ክርስትያን  ወይም ካለ ኖተር ዳም ካቴድራልን  ፓሪስ ፓሪስ አለመሆንዋን ይገልፃሉ። ካቴድራልዋ የፈረንሳይን ብሎም የሰዉ ልጆች ጥበብን ፤ እምነትን ሥነ-ጥበብ ታሪክን አቅፎ የያዘ ሲሉ ባጭሩ ይገልፆአታል።  የጀርመኑ ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር-ሽታትይን ማየር «የአዉሮጳ መለያ» ያሉትን ካቴድራል ለመጠገን የጀርመንና የመለዉ አዉሮጳ ሕዝብ ርዳታ እንዲሰጥ ጠይቀዋል። የጀርመንዋ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልም በፓሪሱ ኖተርዳም ቃጠሎ ጀርመናዉያን አዝነናል ብለዋል።    

Frankreich, Paris: Brand in der Kathedrale Notre Dame
ምስል Getty Images/AFP/L. Marin

«ኖተር ዳም የፈረንሳይን የክርስትና ሃይማኖት ታሪክ የሚሳይ ብቻ ሳይሆን የአዉሮጳ ቅርስም ነዉ። ለዚህም ነዉ ከጀርመን የባህል ሚኒስትር ጋር በመነጋገር በመልሶ ግንባታዉ ላይ ለመሳተፍና ባለሞያዎችን እና ልምዳችንን በመቀያየር ርዳታ ለመስጠት ዝግጁነታችንን የገለፅኩት። የባህል ሚኒስትሮቹ በኖተር ዳሙ ካቴድራል እድሳት ላይ ምልከታዎቻቸዉን ይለዋወጣሉ። በዚህም አለ በዝያ በፓሪስ በተከሰተዉ ነገር ጀርመናዉያን እጅግ አዝነናል» 

ኖትረ ዳም ካቴድራል ለ9 ሰዓታት ሲነድ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ተለይ በቴሌቭዥን በቀጥታ እየዘገቡት ነበር። የዓለም የታሪክ የቅርስ ምሁራን ከተለያዩ ዓለም ሃገራት ቁጭታቸዉን በሃዘኔታ ይገልፁም ነበር። በፓሪስ የሚገኙ አንድ የታሪክ ምሁር ከኖተር ዳም ካቴድራል ከ12ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የዓለም ደስታ እና ሃዘን ደውል ተደዉሎአል፤ አሁን በእሳት ሲንቦገቦግ ማየቱ እጅግ ያሳዝናል ነበር ያሉት።

ኖትረ ዳም ለፈረንሳውያን ብሔራዊ አርማቸዉ እንደሆን የሚናገሩት ኢትዮጵያዊትዋ ወ/ሮ ማርታ በፓሪስ ሲኖሩ ከ 15 ዓመት በላይ ሆንዋቸዋል። ከኖተር ዳም ሰባት ስምንት ኪሎ ሜትር ርቀዉ እንደሚኖሩም ተናግረዋል።  ወይዘሮ ማርታ እንደሚሉት በኖተርዳም መቃጠል የፈረንሳይ አልያም የአዉሮጳ ነዋሪ ብቻ ሳይሆን የዓለም ሕዝብን አሳዝኖአል።እንድያም ሆኖ የፈጣሪ ነገር አስገርሞኛል ብለዋል።   

Frankreich, Paris: Brand in der Kathedrale Notre Dame
ምስል picture-alliance/dpa/J. Mattia

ከ 12 ኛዉ ክፍለዘመን ጀምሮ ፓሪስ ከተማ የቆመዉና ሰማይ ጠቀስ ህንጻ የተባለዉ ካቴድራል፤ በቁመት ከቆመ ወደ 100 ዓመት ከሆነዉን የፓሪሱን አይፍል ማማ  በቁመት ትንሽ አለስ ያለ ግን በፓሪስ ሁለተኛዉ ሰማይ ጠቀስ ህንጻ እንደሆን ይነገርለታል። የፓሪስዋ ኖተር ዳም ቤተ-ክርስትያን በአማርኛ የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ- ክርስትያን ማለት ነዉ ያሉን ወ/ሮ ማርታ፤ ኢትዮጵያ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳሉ ትምህርት ቤተ-መጽሐፍ ላይ ስለ ኖተር ዳም ታሪክ ማንበባቸዉን መማራቸዉን ያስታዉሳሉ።  

«ኖትር ማለት የኛ ማለት ነዉ ዳም ማለት እመቤታችን ማለት ነዉ። ቅድስት ማርያም ቤተክርስትያን ማለት ነዉ። »

Dornenkranz Christi Notre-Dame
ምስል picture-alliance/dpa/Godong/P. Deliss

የፓሪስዋ የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ-ክርስቲያን ማለት ኖተር ዳም ላይ ቃጠሎ ሲነሳ የፓሪስ ነዋሪዎች አብዛኞች አልቅሰዋል፤ በየጎዳናዉ በመሰባሰብ ፀልየዋል፤ መዝሙር ዘምረዋል። በፓሪስ የሚገኙ  ሌሎች አብያተ ክርስትያናትም ደውል ሲያሰሙ ማምሸታቸዉ በቀጥታዉ ስርጭት ቴሌቭዥን ሲሰራጭ ነበር። ኖተር ዳም በዓመት ከ 12 እስከ 13 ሚሊዮን ሕዝብ እንደሚጎበኘዉ ተመልክቶአል። ቤተ-ክርስትያኒቱ በተለይ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ላይ የተደረገዉ የእሾህ አክሊል የተቀመጠበት በመሆኑ በሃይማኖቱ ተከታዮች ይታወቃል። ቤተ-ክርስትያኒቱ በወር በገባ የመጀመርያ አርብ እለት እለት በሚደረግ ፀሎት ላይም ለምዕመናን ለእይታ ይቀርብ እንደነበር ተመልክቶአል። አንድ የፓሪስ ጋዜጣ እንዳስነበበዉ የእሾክ አክሊሉ ከእሳት መጋየት ተርፎአል። ይህንን ከእሳት ያዳነዉም የእሳት አደጋ ሰራተኛ ጀግና በሚል ተወድሶአል። ወ/ሮ ማርታ በኖተር ዳም ስለአለዉ የእሾህ አክሊል ያዉቃሉ።   

Frankreich Paris | Zerstörung nach Brand der Kathedrale Notre-Dame de Paris
ምስል Reuters/C. Petit Tesson

« የሾህ አክሊሉ ወር በገባ የመጀመርያዉ አርብ ይታያል ። በሁዳዴ ጾምም አርብ አርብ ይወጣል። እምድር ቤት የቤተክርስትያኒቱ ሙዚየም ይገኛል እና እሳት የደረሰበት አይመስለኝም አብዛኛዉ እቃ ተርፎአል ነዉ የሚባለዉ። »

የቤተ-ክርስትያኑ የደወል ቤት መቃጠሉ ተነግሮአል ማማዉም በቃጠሎዉ ወድቆአል። እንድያም ሆኖ በቤተክርስትያኒቱ የነበሩ ሥነ- ጥበባዊ ሃይማኖታዊ እንዲሁም ታሪካዊ እሴቶች አብዛኞቹ መትረፋቸዉን የፈረንሳይ የባህል ሚኒስቴር አስታዉቋል። የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኤማኑኤል ማክሮ ፤ ሃገራችን ብዙ ችግርን ተጋፍጣለች እንድያም ሆኖ ጉልበታችን አስባስበን ችግርን ማሸነፍ እንችላለን፤ ኃይሉም አለን ሲሉ ነበር በቁጭት በቴሌቭዥን ቀርበዉ ለሕዝባቸዉ ንግግር ያደረጉት   

Frankreich Präsident Macron TV Rede
ምስል Getty Images/AFP/L. Marin

«ፓሪስ ላይ ትናንት የተከሰተዉን እና ያየነዉን ነገር ለመቋቋም ዛሬም ኃይሉ አለን። ታሪካችን እንደሚያሳየዉ ፈረንሳዉያን ከተሞችን ወደቦችን አብያተ ክርስትያናትን ገንብተናል። ከነዚህ መካከል አብዛኞቹ በአብዮት በጦርነት በሰዉ ስህተት ተቃጥለዋል፤ ከጥቅም ዉጭ ሆኖ ያዉቃል። ግን ሁልጊዜም ቢሆን የተበላሸብንን የፈረሰንን መልሰን ገንብተናል። »

እናም አሉ ይህን ፤ ክፉ እጣ ወደ እድል ቀይረን ለብሔራዊ እቅዶቻችን አንድ እንሁን አሉ ፕሬዚዳንት ማክሮ በመቀጠል።

«ይህ የደረሰብንን ከፍተኛ አስከፊ ነገር ሁላችንም ወደ አንድነትና መምጫ አጋጣሚ እንወስደዋለን የሚል ፅኑ እምነት አለኝ።  ምን እንደነበርን፤ አሁን ማን እንደሆንን ወደፊት ከአሁን ይበልጥ እንዴት እንደምንሻሻል፤ በጥልቅ ሳስብ ነበር። ስለፈረንሳይ የመቆርቆራችን ሰብዓዊነት የተሞላዉ ብሔራዊ የሆነ እቅዶቻችንን የማግኘት እድሉ በእጃችን ነዉ።»

የ 850 ዓመት እድሜ ያለዉ የፓሪስዋ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስትያን ኖተር ዳም፤ ለፈረንሳዉያኑ የላሊበላ ዉቅር ቤተ-ክርስትያን አይነት ታሪካቸዉ ነዉ ሲሉ ታሪኩን በጥልቀት የሚዉቁ ኢትዮጵያዉያን ሲገልፁት ይሰማል። ፓሪስ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ማርታም ፓሪስን ለመጎብኘት የሚመጣባቸዉ እንግዳ መጀመርያ የሚያሳዩት ይህችኑ ቤተ ክርስትያን እንደሆን ይናገራሉ። ምክንያቱም አሉ፤ የቤተ- ክርስትኒቱ ፀጥታ የመብራት እና ዉጋጋን  በግድግዳዉ እና በደወል ላይ ያለዉ የሥነ ጥበብ ሁኔታ ሁሉ አብዛኛዉ ከኢትዮጵያዉ ቤተ- ክርስትያን ጋር ተመሳሳይነት አለዉ።   

Frankreich Brand Notre Dame
ምስል picture-alliance/NurPhoto/M. Stoupak

ከአምስት ስድስት ዓመት በፊት ፈረንሳዉያን መሃንዲሶች ከመዲና ፓሪስ ዉጭ በምህንድስና ስራ ላይ ሳሉ እጅግ ግዙፍ የሆነ ደወል ተቀብሮ በማግኘታቸዉ ደወሉ ወደ ፓሪሱ ኖተር ዳም በትልቅ የበዓል ሥነ-ስርዓት መጥቶ መገጠሙን የሚያስታዉሱት ወ/ሮ ማርታ፤ ከቃጠሎዉ ወዲህ ቤተ ክርስትያኒቱን ለማየት ሄደዉ በርካታ ወጣቶችን በማየታቸዉ ተደንቀዋል ተደስተዋልም።

ታሪካዊዉ የፓሪስ ቤተ-ክርስትያን ዳግም ለማነፅ፤ በርካታ የዓለም መንግሥታት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁነታቸዉን እየገለፁ ነዉ።  በጥንታዊ ሥነ-ሕንፃ ጥበብ የታወቁት የግሪክና የቼክ መንግሥታት ባለሞያዎችን ለመላክ ዝግጁ መሆናቸዉን አስታዉቀዋል። የፈረንሳይ ቱጃሮች ፤ የፈረንሳዩ የነዳጅ ኩባንያ  እንዲሁም  የፈረንሳዩ የመዋቢያዎች አምራች ኩባንያ በሚሊዮን የሚቆጠር ዩሮን ሰጥተዋል። ከዚህ ሌላ ስማችን እንዳይነገርብን ብለዉ እንዲሁ በሚሊዮን የሚቆጠር ድጋፍ ያደረጉ ጥቂቶች አይደሉም። የፓሪስ ከተማ ከንቲባ ቤተ-ክርስትያኒቱን ለማደስ የገቢማሰባሰብያ ጉባዔ እንደሚካሄድ ይናገሩ እንጂ፤ እስካሁን የገባዉ የርዳታ ገንዘብ ከአንድ ቢሊዮን ዩሮ መብለጡ ተነግሮአል።  ታሪካዊዉን ሕንፃ ስላጋየዉ ቃጠሎ እንዴትነት ምንነት በዉል አይነገር አይታወቅ እንጂ፤ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኤማኑኤል ማክሮ እድሳቱን በአምስት አመት ዉስጥ እንዲጠናቀቅ እንደሚፈልጉ ገልፀዋል።

Kathedrale Notre-Dame in Paris
ምስል picture-alliance

 «ዛሬ በድፍረት ልነግራችሁ የምፈልገዉ ነገር ቢኖር እኛ የግንባታ ሰዎች መሆናችንን ነዉ። ብዙ የሚጠገኑ ዳግም የሚገነቡ ነገሮች አሉን፤ አዎ አሉን። ኖተር ዳም ካቴድራልንም መልሰን እንገነባለን። እንደዉም ከበፊቱ ይበልጥ አሳምረን እንገነባዋለን። ይህ ሥራ በአምስት ዓመት እንዲያልቅ እፈልጋለሁ። ይህን ማድረግም እንችላለን፤ ሥራችን ጀምረናል።»     

የፓሪስ ምልክቶች ከሚባሉት አንዱ የሆነው የኖተር ዳም ካቴድራልን ግማሽ አካል ያወደመዉ እሳት የሰዉን ልጅ የሥነ-ጥበብ የሃይማኖት እንዲሁም የታሪክ እሴትን መፈታተኑ ብዙዎችን ቢያስቆጣ ቢያሳዝንም ቱራጃሮች የፓሪሱን የሰዉ ልጅ ጥንታዎ የታሪክ ለማደስ የመሯሯጣቸዉን ያህል፤ ምነዋ የየመኑን የሶርያዉን የኢራቅን ታሪካዊ ባህላዊ እሴት ከቦንብ ለመጠበቅ አለመጣራቸዉ የሚል አስተያየትን የሰጡ ማኅበራዊ መገናና ዘዴ እደምቶች ጥቂቶች አይደሉም ። አድማጮች እኔም በዚሁ የእለቱን መሰናዶዬን ልቋጭ አዜብ ታደሰ ነኝ መልካም ምሽት ጤና ይስጥልኝ ።  

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ