1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎች ሥጋትና አቤቱታ

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 12 2016

ቀደም ሲል በኮሮና ቫይረስ ተፅዕኖ፣ ከዚያም በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ይፈጠሩ በነበሩ የፀጥታ ችግሮችና አሁን ደግሞ በአማራ ክልል ባለው ወቅታዊ የሰላም መደፍረስ ምክንያት ትምህርታቸውን ባግባቡ መማር ሳይችሉ እንደቆዩ ነው ተማሪዎቹ ለዶይቼ ቬሌ የሚናገሩት

https://p.dw.com/p/4aUYJ
ወሎ ዩኒቨርስቲ-ደሴ
ወሎ ዩኒቨርስቲ-ደሴምስል Gonder & Wello University

ተማሪዎቹ ለሚያቀርቡት ጥያቄ መልስ የሚሰጥ አካል የለም

በአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች  ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች እስካሁን ይማሩባቸው ወደነበሩዩኒቨርሲቲዎች ባለመጠራታቸው በዚህ ዓመት ላንማር እንችላለን የሚል ስጋት እንዳደረባቸው ተናገሩ፣ በተለያዩ መንገዶች መረጃ ለማግኘት ቢሞክሩም መልስ የሚሠጣቸው አካል እንደሌለ አመልክተዋል፣ ለሚመለከታቸው አካላት ምላሽ እንዲሰጡን ብንምክርም አልታሳካልንም፡፡
ቀደም ሲል በኮሮና ቫይረስ ተፅዕኖ፣ ከዚያም በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ይፈጠሩ በነበሩ የፀጥታ ችግሮችና አሁን ደግሞ በአማራ ክልል ባለው ወቅታዊ የሰላም መደፍረስ ምክንያት ትምህርታቸውን ባግባቡ መማር ሳይችሉ እንደቆዩ ነው ተማሪዎቹ ለዶይቼ ቬሌ የሚናገሩት፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች አለመጠራታቸው ሌላ ችግር ሆኗል ነው የሚሉት፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህግ ተማሪ የሆነው ጌታቸው አስረሳ በአማራ ክልል ባለው ጦርነት ምክንያት በዚህ ዓመት ተማሪዎች እስካሁን ወደ ዩኒቨርሲቲ አልተጠሩም፣ ተገቢ መረጃም የሚሰጥ አካልም የለም ይላል፣ አጠቃላይ ባለፉት ጊዜዎችም በነበሩ የተለየዩ ሳንካዎች ተገቢውን ትምህርት እንዳልወሰዱም ያስረዳል፡፡

የባህርዳር ዩኒቨርስቲ
የባህርዳር ዩኒቨርስቲምስል A. Mekonnen/DW

“የሚያሳዝነው ነገር እየደወልን የሚመለከታቸውን አካላት ስንጠይቅ ምንም አናውቅም ይላሉ፣ አንዳንዶች ስልክ አያነሱም፣ አጭር የፅሁፍ መልዕክትም አይመልሱም፣ ተስፋ የሚሰጥ ነገር አይናገሩም፣ የዚህ ጊዜ “ባች” ከአንደኛ ዓመት ጀምሮ ብዙ ተግዳሮቶችን እየተጋፈጠ የመጣ “ባች” ነው፣ በኮሮና ምክንት ብዙ ጊዜ ግቢ ውስጥ ቆየን፣ በተለያዩ አለመረጋጋቶች የትምህርት ክፍለጊዜዎች እየተጓተቱ፣ እየተቆራረጡ፣ አንድ ወሰነ ትምህርት በ45 ቀናት እየተማርን ነው የመጣነው፣ ብዙ የትምህርት ክፍሎች አልተሸፈኑም፣ እነዚህ ደግሞ የመውጫ ፈተና አካል ናቸው፣ ተማርናቸውም አልተማርናቸውም “ተምረዋቸዋል” ተብሎ ነው የሚታሰበው፣ የተማርናቸው የትምህርት ክፍሎች እንኳ በበቂ አልተማርናቸውም፤፣ወደ ዩኒቨርሲቲው ብንገባ እንኳ እንዴት መሸፈን እንዳለብን ስናስብ ተማሪዎች ካሁኑ ጭንቅ ውስጥ ገብተናል፡፡” ብሏል፡፡

ገረመው ጌታሁን የተባለ የስነምጣኔ ሀብት የ4ኛ ዓመት ተማሪ ወደዩኒቨርቲቸው እንዲመለሱ በተለያዩ መንገዶች ቢጠይቁም ተገቢ ምላሽ እንዳልተሰጠ ይገልፃል፣ ያለትምህርት መቀመጥም የስነ ልቦና ጫና እንደፈጠረበት አመልክቷል፡፡

“...እንዲጠሩን የተቻለንን ሁሉ አቅም  ከጥቅምት ወር ጀምሮ  ግፊት ለማድረግ ሞክረናል፣ ትምህርት ሚኒስቴር ድረስ ተማሪዎች ተወክለው  ጠይቀዋል፣ ሆኖም ብዙ አጥጋቢ ምላሽ የለም፣ የመውጫ ፈተና አለብን፣ ባለፈው ዓመት የዓመቱን ትምህርት ያላጠናቀቁ ተማሪዎች አሉ፣ ለረጂም ጊዜ ቤት ውስጥ መቀመጥ አሰልቺ ነው፣ የስነ ልቦና ጫናም አለው” ነው ያለው፡፡
በሰሜኑ ጦርንት ወቅት ወደ አማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው ለነበሩ ተማሪዎች አሁን በወቅቱ ጥሪ አለመደረጉ ሌላ ጫና እየፈጠረባቸው እንደሆነም ተማሪዎቹ ይገልጣሉ፣ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረው ጦርነት ምክንያት አንድ የትምህርት ዓመት ባክኖባቸዋል፣ በኮሮና ሌላ መራዘም ተፈጥሮባቸው ነበር፣ አሁን ደግሞ ሌላ ፈተና ነው ያጋጠማቸው በማለት ተማሪዎቹ ያስረዳሉ፡፡
ማሪያማዊት ማናዬ የጤና ተማሪ ናት፣ እርሷ እንደምትለው የጤና ትምህርት ሌሎች ተጫማሪ ኮርሶች ያሉት የትምህርት መስክ ነው ፣ በመሆኑም በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ትምህርቱ ካልተሰጠ አስቸጋሪ እንደሚሆን ነው የተናገረችው፣ ምናልባትም ጊዜ ካለፈ በኋላ ወደ ዩኒቨርሲቲው ገብቶ በይድረስ ይድረስ ትምህርቱ የሚሰጥ ከሆነ ተማሪው በቂ እውቀት ይዞ አይወጣም ብላለች፡፡

የጎንደር ዩኒቨርስቲ
የጎንደር ዩኒቨርስቲምስል Gonder & Wello University

መረጃ ለማግኘትና ጥሪ እንዲደረግላቸው ጥረቶች በተደጋጋሚ ቢያደረጉም ተስፋ እንዳጡ ነው ተማሪዎቹ ያመለከቱት፡፡
የቀረቡትን የተማሪዎች ጥያቄዎች መሰረት በማድረግ ለአንዳንድ ዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎች ስልክ ብደውልም ስልካቸው አይነሳም፣ ለአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ፕሬዚደንት ብደውልም ማንነቴን ከገለፅሁላቸው በኋላ ስላክቻውን ዘግተዋል፣ ከዚያ በኋላም ማንሳት አልፈለጉም፣ ለፃፍኩላቸው ዐጭር የፀሁፍ መልዕክትም ምላሽ አልሰጡም፣ ለትምህርት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊም ደውየ ስልካቸው አይነሳም፡፡በአማራ ክልል 10 የመንግስት ዩኒቭርሲቲዎች ይገኛሉ፡፡

ዓለምነው መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ