1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

አሜሪካ ከሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ቅርበት ባላቸው ሦስት ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጣለች

Eshete Bekele
ሐሙስ፣ ጥር 23 2016

በሱዳን ጦርነት 8 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች እንደተፈናቀሉ የተባበሩት መንግሥታት አስታውቋል። አሜሪካ “የሱዳንን ሠላም፣ ጸጥታ ወይም መረጋጋት አደጋ ላይ በሚጥሉ ድርጊቶች” በመሳተፍ በወነጀለቻቸው ሦስት ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጥላለች። ጦርነቱ ሱዳን ከኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወደ ምትዋሰንባቸው ምሥራቃዊ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመስፋፋት ዝንባሌ አሳይቷል

https://p.dw.com/p/4bvai
የሱዳን ጦርነት ያፈናቀላቸው ሰዎች
በሱዳን ጦርነት 8 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት አስታውቋልምስል AFP

በሱዳን ጦርነት የተፈናቀሉ ሰዎች ስምንት ሚሊዮን ገደማ መድረሱን ፊሊፖ ግራንዴ ተናግረዋል

አሜሪካ “የሱዳንን ሠላም፣ ጸጥታ ወይም መረጋጋት አደጋ ላይ በሚጥሉ ድርጊቶች በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ” በመሳተፍ በወነጀለቻቸው ሦስት ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጥላለች። ማዕቀቡ ከተጣለባቸው ሦስት ኩባንያዎች ሁለቱ በመሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ከሚታዘዘው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ግንኙነት ያላቸው ናቸው።

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የሚቆጣጠረው ዑልኻሊጅ ባንክ ማቀብ ከተጣለባቸው አንዱ ሲሆን ታጣቂ ቡድኑ ወታደራዊ ዘመቻዎቹን በገንዘብ ለመደገፍ በሚያደርገው ጥረት ቁልፍ ሚና እንዳለው የአሜሪካ ግምዣ ቤት አስታውቋል።

ማዕቀቡ ይፋ ያደረገው መግለጫ እንደሚለው ባንኩ በሚያዝያ 2015 የሱዳን ጦርነት ከመቀስቀሱ ጥቂት ጊዜያት በፊት 50 ሚሊዮን ዶላር ከሱዳን ማዕከላዊ ባንክ ተረክቧል።

በሱዳን ፈጥሮ ደራሽ ኃይል ከፍተኛ አመራሮች የተመሠረተው እና የታጣቂ ቡድኑን ወርቅ ለውጭ ገበያ የሚያቀርበው አል-ፋክር የተባለ ኩባንያ ተመሳሳይ ማዕቀብ ተጥሎበታል። መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመሩት ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በአል-ፋክር ኩባንያ በኩል ወርቅ በመሸጥ ባገኘው ገንዘብ የቡድን የጦር መሣሪያዎች እና ሮኬቶች ጭምር እንደገዛበት አሜሪካ ወንጅላለች።

ከሱዳን ብሔራዊ ጦር ቁልፍ የንግድ ተቋማት አንዱ እንደሆነ የተነገረለት ዛድና የተባለ ኩባንያ ተመሳሳይ ማዕቀብ ተጥሎበታል። በሱዳን ጦር የማኅበራዊ ዋስትና ልዩ ፈንድ ሥር የሚገኘው ዛድና ወታደራዊ የገንዘብ ማዘዋወሪያ መሣሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል አሜሪካ ወንጅላለች።

አብደል ፋታኅ አል-ቡርኻን እና መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ
የምሥራቅ አፍሪካ በይነ-መንግሥታት (ኢጋድ) አብደል ፋታኅ አል-ቡርኻን እና መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎን ፊት ለፊት ለማገናኘት ያደረገው ጥረት እስካሁን አልተሳካም። ምስል Mahmoud Hjaj/AA/picture alliance

የአውሮፓ ኅብረት ባለፈው ሣምንት የሱዳን መከላከያ ኢንዱስትሪ ሲስተም እና ዛድናን ጨምሮ በስድስት ኩባንያዎች ላይ ተመሳሳይ ማዕቀብ ጥሏል። በኅብረቱ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል ይፋ የሆነው ማዕቀብ መቀመጫቸውን በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ያደረጉ እና የመሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የሚቆጣጠራቸው ኩባንያዎችን ጭምር ያካተተ ነው።

የአሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት ማዕቀቦች የተከታተሉት ዘጠኝ ወራት ባስቆጠረው የሱዳን ጦርነት የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 8 ሚሊዮን ገደማ መድረሱን የተባበሩት መንግሥታት ባስታወቀበት ወቅት ነው። ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ ስድስት የሱዳን ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል። በሱዳን ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ሚያዝ 2015 ጀምሮ ከ100 ሺሕ በላይ ሱዳናውያን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ተሻግረው ገብተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዴ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ሲያጠናቅቁ ትላንት ረቡዕ በአዲስ አበባ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የግጭቱ ብርታት እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያስከተለው ዳፋ መበርታቱን ተናግረዋል። መግለጫውን ከሰጡ በኋላ ወደ ሱዳን ያቀኑት ግራንዴ ለስደተኞች በቂ ዕገዛ እየተደረገ እንዳልሆነ ነቅፈዋል።

በሱዳን ጦርነት የወደመ በኻርቱም የሚገኝ መኖሪያ ቤት
በሱዳን ዋና ከተማ ኻርቱም ከሚያዝያ 2015 ጀምሮ የተደረገ ውጊያ ብርቱ ጉዳት አድርሷልምስል Marwan Ali/Ap Photo/picture alliance

ፊሊፖ ግራንዴ “በቂ ምግብ፣ መድሐኒት ወይም መጠለያ የማይቀርብላቸው ስደተኞች ጉዟቸውን ይቀጥላሉ። በአሁኑ ወቅት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላው መጓዝ ቀላል ነው። ከዚያ የአውሮፓ ሀገራት ስደተኞች ሊቢያ፣ ቱኒዝያ እና የሜድትራኒያን ባሕርን አቋርጠው እየመጡብን ነው እያሉ ያማርራሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

ግራንዴ የጠቀሱት በሜድትራኒያን ባሕር ላይ የሚደረግ ጉዞ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያንን ጨምሮ የተሻለ የሥራ ዕድል እና ገቢ የሚፈልጉ ሰዎች ወደ አውሮፓ ለመግባት የሚሞክሩበት ነው። “ተፈናቃዮቹን ካላረጋጋናቸው እነዚህ ሰዎች ጉዟቸውን ይቀጥላሉ” የሚል ማስጠንቀቂያ የሰጡት የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር “የሰብዓዊ ዕርዳታ እነዚህን ሰዎች ለማረጋጋት የመጀመሪያው እርምጃ ነው” የሚል ጥሪ አቅርበዋል።

በአብደል ፋታኅ አል-ቡርኻን የሚታዘዘው የሱዳን ብሔራዊ ጦር እና መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመሩት ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ውጊያ 49 ሚሊዮን የሀገሬው ሰዎችን ዕርዳታ ጠበቂ አድርጓቸዋል። የተባበሩት መንግሥታት እስከ ጎርጎሮሳዊው 2023 መጨረሻ 12 ሺሕ ሰዎች መገደላቸውን ቢያስታውቅም ትክክለኛው ቁጥር ከዚያ የላቀ እንደሆነ ይታመናል።

የምሥራቅ አፍሪካ በይነ-መንግሥታት (ኢጋድ) አብደል ፋታኅ አል-ቡርኻን እና መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎን ፊት ለፊት ለማገናኘት ያደረገው ጥረት ከሽፏል። ፍልሚያ የገጠሙት የጦር ጄኔራሎች ወደ ድርድር እንዲያመሩ ጫና ለማሳደር የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ ከደቡብ ሱዳን እና ከኬንያ መሪዎች ተገናኝተው ተነጋግረዋል። የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና ተፋላሚዎቹ ልዩነቶቻቸውን በድርድር እንዲፈቱ የሚደረገው ጥረት ግን እስካሁን ፍሬ አልተገኘበትም።

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ እና የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ሚያርዲት በጁባ
የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ ወደ ጁባ አቅንተው የሱዳንን ጦርነት በፊት አውራሪነት የሚመሩት የጦር ጄኔራሎችን ወደ ድርድር መምራት በሚቻልበት ስልት ላይ ከደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ሚያርዲት ተነጋግረዋል።ምስል Michael Kappeler/dpa/picture alliance

በሱዳን ቀውስ በተለይ በዳርፉር ግዛት የጦር ወንጀል እየተፈጸመ ነው የሚል ሥጋት ፈጥሯል። ከግዛቲቱ 555,000 ሰዎች ወደ ቻድ እንደተሰደዱ ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት በዚህ ሣምንት የተናገሩት የዓለም አቀፉ የወንጀል መዳኛ ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ ካሪም ክኻን የዳርፉር ሁኔታ “አሳሳቢ” እንደሆነ አስጠንቅቀዋል። ባለፈው ሐምሌ ምርመራ የጀመሩት ክኻን ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች በተለይ በዳርፉር ግዛት የጦር ወንጀል እየፈጸሙ ነው ሲሉ ወንጅለዋል።

ፈጥኖ ደራሹ ኃይል ወደ አል-ጀዚራ ግዛት የጀመረው ግስጋሴ ጦርነቱ ሱዳን ከኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወደምትዋሰንባቸው አካባቢዎች እንዲስፋፋ ሊያደርገው እንደሚችል አስግቷል። በኤርትራ ውስጥ በሚገኙ አምስት ጣቢያዎች የሱዳን ወታደሮች እየሰለጠኑ መሆኑን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት በደሕንነት ሥጋት ሳቢያ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የዐይን እማኞች ዋቢ አድርጎ ዘግቧል። በዘገባው መሠረት ሥልጣናው የሚሰጥባቸው ጣቢያዎች አል-ቡርኻን ከሚመሩት ብሔራዊ ጦር እና በቀድሞው ፕሬዝደንት ኦማር አል-በሺር መንግሥት ሥልጣን ላይ ከነበሩ ግለሰቦች ግንኙነት ያላቸው ናቸው።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ