አሳሳቢው የሶማሊያና የሱዳን ፖለቲካዊ ቀውስ ወዴት እያመራ ይሆን?
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 23 2014እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በ 1991 ዓ.ም ሶማሊያን ከሁለት ዓስርተ ዓመታት በላይ በአምባገነንነት የመሩት ፕሬዝዳንት ሙሃመድ ሲያድ ባሬ ለውጥ እናመጣለን ብለው በተፋለሟቸው አማጽያንና በሕዝባዊ አመጽ ከስልጣን ተባረው ወደ ናይጄሪያ ከኮበለሉ በኋላ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት መገንባት አቅቷት በጎሳ ግጭት ስትናጥ የቆየችው የሶማሊያ ሪፐብሊክ በእርስ በእርስ ጦርነትና በጎሳ የጦር አበጋዞች መሪዎች መካከል በተካሄዱ ተከታታይ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ሳቢያ ለሶስት የመከፈል ዕጣ ገጥሟታል:: ዚያድባሬ ዋና መዲናዋን ሞቃዲሾ በኃይል ከለቀቁ በኋላ ማዕከላዊ ከተማዋን የመቆጣጠር ዕድል በገጠመው የሶማሊያ አንድነት ኮንግረስ መሪ የኮሎኔል አሊ ማሃዲ ሞሃመድ ቡድንና የዚያድባሬን ታማኝ ጦር በደቡብ ሶማሊያ እግር በእግር እየተከታተለ ሲፋለም በነበረው በተባበረችው የሶማሊያ አንድነት ካውንስል መሪ በህንድ የሶማሊያ አምባሳደር የነበሩት ጄነራል ሞሃመድ ፋራህ አይዲድ ቡድን ደጋፊዎች መካከል ከድል በኋላ የፕሬዝዳንትነቱን ስልጣን ማን ይቆጣጠር የሚለው የይገባኛል አታካሮ ወደ ስምምነት ባለማድረሱ ዛሬም ድረስ ያላባራው የእርስ በእርስ ጦርነት በሶሚሊያ ምድር መቀጣጠሉ ነው የሚነገረው::
በ 1992 ዓ.ም የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ በሶማሊያ የሰፈነውን አስከፊ የእርስ በእርስ ግጭት ለማብቃት የተለያዩ ሃገራት ወታደሮችን ያካተተ የተባበሩት የተልዕኮ ኃይል ቢልኩም በሃገሪቱ ሰላምን ለማምጣት ይከተለው በነበረው የኃይል እርምጃ ምክንያት ክፉኛ ሕዝባዊ ተቃውሞና ጥቃት ስለገጠመው ተልዕኮውን ሳያሳካ ለመውጣት ተገዷል:: እሱን የተኩት የተባበሩት መንግሥታት ዩኒሶም እና የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ አሚሶምም በ 10 ሺህ የሚቆጠሩ ወታደሮችን በማስፈር በሶማሊያ ሰላምን ለማስፈን በርካታ ጥረቶችን ማድረጋቸው ይጠቀሳል:: በጎሳ ግጭት ምክንያት ጠንካራ መንግሥት አለመመስረቱ ሃገሪቱን እንደ አልሽባብ ላሉና ሌሎችም ዓለማቀፍ አሸባሪዎች መናኸሪያ ያደረጋት ሲሆን በሕንድ ውቅያኖስ ዳርቻ መገኘቷም የአያሌ ሃገራትን ግዙፍ የንግድ መርከቦች ከሶማሊያ ለሚንቀሳቀሱ በጦር መሳሪያ የተደራጁ የባህር ላይ ወንበዴዎች ዘረፋ ግድያና የንብረት ውድመት አጋልጧቸው ቆይቷል:: አንዳንድ ጥናቶች እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር ከ 2010 እስከ 2020 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ብቻ በሶማሊያ ከ 160 በላይ የባሕር ላይ ጥቃቶች መፈጸማቸውናን ከ 358 የሚልቅ የሕይወትና የንብረት ጉዳት መድረሱን ይፋ አድረገዋል::
ሶማሊያ እስካሁን ሁሉንም የሃገሪቱ ጎሳዎች የሚያግባባ ማዕከላዊ መንግሥት መመስረት ተስኗት ብትቆይም በፈረንጆቹ 2000 ዓ.ም በጅቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጉሌህ ሃሳብ አመንጪነትና በተባበሩት መንግስታት በአሜሪካና በአውሮጳ ሕብረት የፋይናንስ ድጋፍ የጎሳ የጦር አበጋዞች የፖለቲካ ልሂቃንና የሃይማኖት አባቶችን ያሳተፈ የሰላም ጉባኤ በማካሄድ የሽግግር መንግሥት ለመመስረት ተችሏል:: በዓለማቀፉ ማህበረሰብ ዕውቅና የተቸረው "የሶማሊያ ብሔራዊ የሽግግር መንግሥት" በሚል የብህዙሃኑ ሕዝብ ውክልና ያለው መንግሥት ለመመስረት ቢችልም ዛሬም ድረስ ሃገሪቱን ከሽብር ሃይሎች ጥቃትና ከገጠማት ውስብስብ ቀውስ አላቆ ብሔራዊ አንድነትና መግባባት ለማስፈን እንዲሁም የብዙሃን ቅቡልነት ያለው አመራር ስልጣን ላይ ማውጣትና የተረጋጋ ሃገረ መንግስት ማቆም ተስኖት ቆይቷል:: ለዚህም ዓብይ ምክንያቱ የሽግግር መንግሥቱን የተወሰኑ ቡድኖች በጉባኤ ተወያይተው የሰየሙት እንጂ በሕዝባዊ ምርጫ ወደ ስልጣን የመጣ ባለመሆኑ እንደነበር የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ:: ለአብነትም እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በ 2017 ዓ.ም ወደ ስልጣን ለመጡት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሙሃመድ ፋርማጆን የሕጋዊነት ጥያቄ በማንሳት እንደ ቦሶሳ ፑንትላንድና የጁብላንድ የጎሳ መሪዎች ዛሬም ድረስ እንደማይቀበሉ በይፋ መግለጻቸው ሀገሪቱ የገባችበት ከፍተኛ የፖለቲካ ቅርቃር አንዱ ማሳያ ነው ተብሎ ይነገራል:: ይህ ሁሉ ውስብስብ ዘረፈ ብዙ ችግር የተጋረጠባት ሶማሊያ ባሳለፍነው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በኮረና ወረርሽኝ መስፋፋት ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ ከተላለፈ በኋላ ባለፈው ሚያዝያ ወር የሃገሪቱ የታችኛው ምክርቤት የምርጫ ማራዘሚያ ውሳኔ አጽድቆ የርዕሰ ብሄሩን የስልጣን ዘመን ለሁለት ዓመታት ማራዘሙን ተከትሎ በሃገሪቱ ከፍተኛ ውጥረት የተከሰተ ሲሆን በተቀሰቀሱ ሕዝባዊ ተቃውሞዎችም በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው የሚታወስ ነው:: ይህ ሁሉ ውዝግብ ባለበት ሁኔታ ነው እንግዲህ የሶማሊያ መንግሥት የወሰዳቸው ሁለት እጅግ ፈታኝ የሆኑ እርምጃዎች ላለፉት ቀናት ሀገሪቱን የበለጠ አጣብቂኝና ቀውስ ውስጥ እንድትገባ ያደረጋት:: አንደኛው የፖለቲካ ትኩሳት የፋርማጆ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ጦር ባልደረቦች ለዓመታት በሶማሊያ የኤደን አዲ ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ኤርፖርት ለብቻቸው ይጠቀሙበት የበረውንና ከማናቸውም ፍተሻና ቁጥጥር ነጻ የነበረውን የሞቭኮን ተርሚናል ለሃገሪቱ ፀጥታና ደህንነት በሚል መዝጋቱ ሲሆን ይህም እርምጃው ከተባበሩት መንግሥታት ጋር ከፍተኛ አታካሮ ውስጥ ከቶታል:: መንግሥት እንዳለው አንዳንድ የሞቭኮን ተልዕኮ አባላት ከመንግሥት ዕውቅና ውጪ የተከለከሉ የኮምኒኬሽን መሳሪያዎችን ማስገባታቸውና በሕገወጥ ተግባር ውስጥ መገኘታቸው በማስረጃ በመረጋገጡ የመንግስታቱ ድርጅት ሲቭልና ወታደራዊ ባልደረቦች እንደማንኛውም መንገደኛ በመደበኛ ተርሚናሎች ተፈትሸው እንዲያልፉ ውሳኔውን ሊያሳልፍ ችሏል:: ድርጊቱ ያስቆጣው የተባበሩት መንግሥታት በበኩሉ ወሳኔው ባልደረቦቹ ያላቸውን ልዩ የዲፕሎማቲክ መብት የሚጋፋና በተልዕኮውንም እንቅስቃሴ ላይ እክል የሚፈጠር በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲነሳ አሳስቧል:: የሶማሊያ መንግሥት የኢሚግሬሽናን ደህንነት ስምምነቶች ተጥሰዋል በማለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰራተኞች፣ አሚሶምና የውጭ ዲፕሎማቶች ብቻ የሚጠቀሙበትን ሞቭኮን ተርሚናል መዝጋቱን በይፋ ያስታወቀው ባለፈው ታህሳስ 15, 2014 ዓ.ም ነበር::
የፕሬዝዳንት ፎርማጆ ህጋዊ የስልጣን ገደብ በጎርጎሮዋዊው የካቲት ወር ላይ በይፋ ቢያበቃም አዲሱ ርዕሰ ብሔር እንዴት ይመረጥ በሚለው ጉዳይ ላይ አሁንም እንደቀድሞው ሁሉ በተፈጠረው ውዝግብና አለመግባባት ምክንያት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫው በድጋሚ ወደ መጪው ዓመት እንዲሸጋገር ተወስኗል:: የፋርማጆ መንግሥትና ዓለማቀፉ ድርጅት እንዲህ ውዝግብ ውስጥ ባሉበትና "የሶማሊያ ሽግግር" በሚል ስም የሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በተቃረበበት በአሁኑ ወቅት ፕሬዝዳንት ሙሃመድ ፋርማጆ ለሃገሪቱ ብሄራዊ የመከላከያ ጦር ማስፋፊያና ለባሕር ኃይል ማሰልጠኛ ተቋም ግንባታ የተዘጋጀ ሰፊ መሬት ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ሕገወጥ የመሬት ወረራና ስልጣንን አለ አግባብ በመጠቀም ወንጀል ተሳትፈዋል በሚል ክስ ያቀረቡባቸውን የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መሃመድ ሃሰን ሮበለን እንዲሁም የሃገሪቱን የባሕር ኃይል አዛዥ ጄነራል አብዲሃሚድ ሞሃመድ ዲሪርን ከስልጣን ማገዳቸው በሃገሪቱም በምሥራቅ አፍሪቃ ቀጣናም ከፍተኛ ውጥረት እንዲሰፍን አድርጓል:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ በተጠረጠሩበት የምዝበራ ወንጀል ከስልጣን ታግደው ምርመራ እንዲካሄድባቸው ፕሬዝዳንቱ ያሳለፉት ውሳኔ በሮበሌ ጎሳ አባላትና ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአሜሪካና ሸሪኮቿ ዘንድ ሳይቀር ከፍተኛ አቧራን አስነስቷል:: ትውልደ ሶማሊያዊቷ የአሜሪካ የኮንግረስ አባል ኤልሃን ኦማር የሃሰን ሮበል ከስልጣን መታገድን እንደሰሙ በቲውተር ገጻቸው በኃይለ ቃል ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ፎርማጆን "የስልጣን ጊዜዎት ካበቃ አንድ አመት አልፎታል ከሃላፊነት ዞር ይበሉ" በማለት መንበረ ስልጣናቸውን እንዲለቁ አሳስበዋል:: ዩናይትድስቴትስም በውጭ ጉዳይ ሚስቴር መስሪያቤቷ በኩል የፕሬዝዳንቱን ውሳኔ በማውገዝ ሁኔታው አሳሳቢ መሆኑን ገልጻ በሃገሪቱ ተዓማኒነት ያለው ምርጫ እንዲካሄድና የሶማሊያ መሪዎች ውጥረትንና ግጭትን ከሚያባብሱ ድርጊቶች ሊቆጠቡ ይገባል ብላለች:: ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከንም ከኬንያው ፕሬዝዳንት ኡኹሩ ኬንያታ ጋር በሶማሊያና በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ላይ መምከራቸው ተገልጿል::
ፕሬዝዳንት ፋርማጆ ያቀረቡባቸው የክስ ወንጀል በሕግ መምሪያው አማካኝነት ምርመራው ተጠናቆ ውሳኔ እስኪሰጠው ከስልጣን እንዳገዷቸው ለሮበሌ ቢገልጹም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው እሳቸውም ከእንግዲህ በሀገር መሪነት እንደማያውቋቸው በመገናኛ ብዙሃን "የቀድሞው ፕሬዝዳንት" በሚል ዘለፋ ጭምር ገልጸዋል:: ፎርማጆም ሆነ ሌሎቻንም ለቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ የተዘጋጀን እጩ ተወዳዳሪዎች በመሆናችን እኩል ሕገ መንግሥታዊ ስልጣንና መብት ነው ያለን ያሉት ሮበል ከዚህ አልፎ ግን ሕገመንግስቱን እንደግል መመሪያው በመውሰድ ማንንም ከሃላፊነት የሚያባርርበት የተለየ ስልጣን ስለሌለው የሃገሪቱ ጦር የሽግግር ሂደቱ እንዳይደናቀፍ ከእንግዲህ ስልጣንና መመሪያ የሚቀበለው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ብቻ ይሆናል ሲሉ ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጥተዋል::
በአሜሪካና ምዕራባውያን ሸሪኮቿ የሚደገፉት በመንግሥት መሬት ወረራና መቀራመት በምዝበራና ስልጣንን አለ አግባብ በመጠቀም ወንጀል ተደጋግሞ ስማቸው የሚጠቀሰው በፕሬዝዳንቱ ከስልጣን የታገዱት ጠቅላይ ሚኒስትር መሃመድ ሁሴን ሮበሌ ከሁለት ቀናት ቆይታ በኋላ የፕሬዝዳንቱን ግቢ ለመክበብ የጎሳቸውን አባላት ደጋፊዎቻቸውን አደራጅተውና የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖችን ሰብስበው በጦር ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች ጭምር ታጅበው ዋና መዲና ሞቃዲሾ የሀገሪቱ ርዕሰ ብሄር የሚገኙበትን ብሔራዊ መንግስቱን ለመክበብና ለመውረር ጥረት አድርገው እንደነበር ታውቋል:: ይህም ኃይላቸውን በማሳየት የፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ፎርማጆ መኖሪያ የሚገኝበትን ጎዳና ከቦ ጥቃት ለመፈጸም አልያም በጫና አስገድዶ ወደ ድርድር ለማምጣትና ካልሆነም መፈንቅለ መንግስት ለማካሄድ ያለመ እንቅስቃሴ ነበር ተብሏል:: ከዚህ ውዝግብ በፊትም ቢሆን እንደ ባሉ እንደ ፑንትላንድና ጁብላንድ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ የሶማሊያ ተወላጆች እስከዛሬ ለፎርማጆ የፕሬዝዳንትነት ስልጣን ዕውቅና እንደማይሰጡ ሲገልጹ መቆየታቸው አሁን ላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩና በፕሬዝዳንቱ መካከል የተፈጠረውን የተካረረ ግጭት ከስልጣንና የፖለቲካ ሹክቻ ወደ ጎሳ ግጭት እንዳያሸጋግረው ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል:: ዘግይተው በወጡ መረጃዎች ደግሞ ሃሰን ሮበለ ፕሬዝዳንቱ ሕገመንግሥቱን በመጣስ ቢሮዋቸውን በወታደራዊ ኃይል ለመቆጣጠር ያደረጉት ጥረት አለመሳካቱን በመግለጽ የወነጀሏቸው ሲሆን ለሚፈጠሩ ማናቸውም ችግሮች ፋርማጆ ኃላፊነቱን ይወስዳሉ ሲሉ አስጠንቅቀዋል:: ደጋፊዎቻቸውም ፕሬዝዳንቱ ሕገመንግስቱን የጣሰ እርምጃ ወስደዋል በማለት ቁጣቸውን እየገለጹ ቢሆንም በበርሚንግሃም ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ተንታኙ አብዲወሊ ጋራድ ግን በሃገሪቱ ሕገመንግሥት በወንጀል የተጠረጠረን ባለስልጣን የማገድና ከስልጣን የማንሳት መብት ለፕሬዝዳንቱ መስጠቱን በመግለጽ ይከራከራሉ::
"የሕገመንግስቱ አንቀጽ 87 ንዑስ አንቀጽ 3 እና 4 ለርዕሰ ብሄሩ በሰጠው ልዩ ስልጣን መሰረት የሃገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር የመሾም ከስልጣን የማንሳትና የማገድ ሙሉ መብት አለው:: ፋርማጆም በወንጀል የጠረጠሯቸው ሀሰን ሮበለ ጉዳያቸው እስኪጣራ ማገዳቸው ህጉ ይደግፋቸዋል"
የፕሬዝዳንቱና የታገዱት ጠቅላይ ሚኒስትር መኖሪያ ቤት ከብሔራዊ ቤተመንግሥቱ በቅርብ አቅራቢያ የሚገኝ ሲሆን ከስልጣን እገዳው በፊትም ባለፈው ዕሁድ ሁለቱ ባለስልጣናት ለምክር ቤቱ ምርጫው መጓተት አንዱ ሌላውን ተጠያቂ በማድረግ በመገናኛ ብዙሃን ሲወነጃጀሉ ታይተዋል::
ዘግይቶ በተሰማው ዜና ሮብለ ፋርማጆን መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ ሞክረዋል ሲሉ የከሰሷቸው ሲሆን ሥልጣናቸውን እንደማይለቁም አስታውቀዋል። የመንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት ሞሃመድ ኢብራሂም ሞአሊሙም ፕሬዝዳንቱ ያሳለፉት ውሳኔ ሕገመንግስቱን መሰረት ያደረገ አለመሆኑን በመግለጽ ሮበለ በኃላፊነታቸው እንደሚቀጥሉ በፌስ ቡክ ገጻቸው አስታውቀዋል::
በአፍሪቃ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ጦር አሚሶም የሚደገፈው የሶማሊያ ብሔራዊ ጦር ከጽንፈኛው አክራሪ ቡድን አልሽባብ ጋር ሲዋጋ አያሌ አመታትን ቢያስቆጥርም ተልዕኮው እየተገባደደ መሆኑ መገለጹ ከጽንፈኛው ቡድን አልሽባብ እየተተናከረ መምጣት ጋር መጪውን ጊዜ ለሶማሊያ የከፋ አድርጎታል:: ሚልዮኖች በረሃብና ጠኔ የሚረግፉባትና በአሸባሪዎች ጥቃት እንዲሁም በጎሳ አበጋዞች ሹክቻ ሚልዮኖች ሀገራቸውን ጥለው የሚሰደዱባት ሶማልያ ሃገሪቱንና የምሥራቅ አፍሪቃን ቀጠና ለመቆጣጠር በሁለቱ ባለስልጣናት መካከል የጎሳ ግጭት እንዲቀጣጠል የውጭ ኃይላት እጅ አለበት ሲሉ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ግምታቸውን ይገልጻሉ:: የሶማሊያ ቀውስ ከድጥ ወደ ማጡ በሆነበት በአሁኑ ወቅት በነዳጅና በተፈጥሮ ሃብት በበለጸገው በሕንድ ውቅያኖስ በሚገኝ የባሕር ይዞታ ለዓመታት በይገባኛል ውዝግብ እስከ ዘ ሄግ ዓለማቀፉ ፍርድ ቤት የተዳረሱት ኬንያ እንዲሁም እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በ 2019 ዓ.ም ከሶማሊያ መንግስት ጋር ጠንካራ ወታደራዊና የምጣኔ ሃብት ትብብር ለመመስረት ከስምምነት የደረሱት ጎረቤት ኢትዮጵያና ኤርትራ ምላሻቸው ምን ሊሆን እንደሚችል እስካሁን የታወቀ ነገር ባይኖርም የሶማሊያ ቀውስ ወደነዚህ ሀገራት እንዳይስፋፋ ጉዳዩን በልዩ ትኩረት ሊያጤኑት እንደሚገባ የፖለቲካ ልሂቃን ምክረ ሃሳባቸውን ይሰነዝራሉ::
በመንግሥታዊ አምባገነንነትና ሕዝባዊ ተቃውሞ የምትናጠው ሱዳን
በዳቦ ዋጋ መናር ምክንያት በሱዳን የተቀጣጠለ ሕዝባዊ አመጽ ለ 30 ዓመታት ሀገሪቱን በጠመንጃ አፈሙዝ አንቀጥቅጠው የገዙትን ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ከመንንበረ ሥልጣናቸው ካስወገደ ሁለት ዓመታት አለፉ:: የኑሮ ውድነትንና የምጣኔ ኃብት ቀውስን በመቃወም በአደባባይ ተከታታይ ሕዝባዊ እምቢተኝነት አንዱን አምባገነን አስወግዶ ወደ ሌላ አምባገነን የተሸጋገረው የሱዳን ሕዝብ ለለውጥ የከፈለው መስዋዕትነትና የአብዮቱ ዓላማ ግቡን መሳቱን በውል ለመረዳት ጊዜ አልፈጀበትም:: ሕዝቡ ሀገራዊ ምርጫ እስኪካሄድ በሲቭሎች የሚመራ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ፍላጎቱ ቢሆንም በተለያዩ ወንጀሎች የንጹሃን ዜጎች ግድያና በመብት ጥሰት ተደጋግሞ የሚከሰሰው ወታደራዊው ኃይል ግን ያለመከሰስ መብቱ እንዲረጋገጥና ዋስትና እንዲሰጠው በመጠየቅ ስልጣኑን ለሲቭል ተቃዋሚዎች እንደዘበት አሳልፎ መስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል:: በመጨረሻም ለረጅም ጊዜያት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ግጭት ለማስቆም የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክርቤትና ተቃዋሚዎች ከብዙ ውይይት ውዝግብና እሰጣገባ በኋላ እንደ ጎርጎሮዋዊው በ 2019 ዓ.ም ላይ ስልጣንን ለመጋራትና ምክር ቤቱን ለሶስት ዓመታት እየተፈራረቁ ለመምራት የሚያስችላቸው ስምምነት ላይ ደረሱ:: አሜሪካም የለውጡን ጅማሮ በማየት ሱዳንን ለሽብር ድጋፍ ከሚያደርጉ ሀገራት ዝርዝር እንደሰረዘቻት በይፋ አስታወቀች:: ሆኖም ሀገራዊ ምርጫ እስኪካሄድ በጋራ የተመሰረተው ጥምር የሽግግር መንግሥት ዜጎች ለዓመታት ይጠይቁት የነበረውን የምጣኔ ሃብት ቀውስና መሰረታዊ የኑሮ ውድነት ችግር ከመፍታት ይልቅ የስልጣን ሽኩቻ ላይ በመጠመዱ ስር ነቀል ለውጥን የሚጠይቁ ሕዝባዊ ቁጣዎችና ተቃውሞዎች አደባባዩን ቀስ በቀስ ማጥለቅለቅ ጀመሩ:: ባለፈው ኅዳር ወር ለሲቭል ፖለቲከኞች ስልጣን ማስረከብ የነበረባቸው የሀገሪቱ የጦር ኃይሎች ዋና አዛዥና የሉዓላዊ የሽግግር ምክርቤቱ ሊቀመንበር ጄነራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ከአንድ ወር በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በሚመራው የሲቭል አስተዳደሩ ላይ መፈንቅለ መንግስት በማካሄድ መሉ ለሙሉ ስልጣን መቆጣጠራቸውን በግልጽ አወጁ:: በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ በአሜሪካ በአውሮጳ ህብረት በፈረንሳይና በሌሎች ሃገራት የሚገኙ የሃገሪቱን አምባሳደሮችም ከስራ የማባረር እርምጃ ወሰዱ::
የተባበሩት መንግሥታትና ዓለማቀፉ ማህበረሰብ የጄነራል ቡርሃንን እርምጃ በመቃወም የቁም እስረኛ ያደረጓቸውን ሃምዶክንና ሲቭል አስተዳደሩን በሙሉ ወደ ስልጣን እንዲመልሱ ከፍተኛ ጫና ጀመሩ:: አሜሪካ እንግሊዝ ሌሎች ሃገራትና ዓለማቀፍ የገንዘብ አበዳሪ ተቋማት ጭምር ለሲቭል አስተዳደሩ ያላቸውን ድጋፍ ሲገልጹ የአፍሪቃ ሕብረትም ሲቭል አስተዳደሩ እስኪመለስ ሱዳንን በጊዜያዊነት ከህብረቱ አገደ:: ሕዝባዊ ተቃውሞውም እጅግ በተጠናከረ መልኩ የሱዳንን አደባባዮች ማጨናነቅ ጀመረ:: ከዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡና ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጭምር ጠንካራ ነቀፋና ውግዘት የገጠመው አልበሽርን በዳርፉርና በተለያዩ የሱዳን ግዛቶች በተፈጸሙ የዘር ማጥፋት ወንጀሎችና የመብጥ ጥሰቶች ዓለማቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለማቅረብ ስምምነት ላይ የደረሰው የአልቡርሃን ወታደራዊ ቡድን ለተቃውሞ አደባባይ የሚወጡትን አያሌ ሰላማዊ ዜጎች ሕይወት ቀጠፈ::
ጄኔራል አል-ቡርሃን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከማድረጋቸው በፊት አልበሺርን ከስልጣን ለማውረድ ተቃውሞ ያቀጣጠሉት ቡድኖችና ጦሩን የሚደግፉ የነጻነትና የለውጥ ኃይሎች በሁለት ጎራ ተሰልፈው የአደባባይ ተቃውሞና የድጋፍ ሰልፎችን ሲያካሂዱ ቆይተዋል:: በወቅቱ አብደላ ሃምዶክ ሀገራቸው ወደ ሲቭል አስተዳደር የምታደርገው ሽግግር የከፋ ቀውስ ገጥሞታል ሲሉ ያስጠነቀቁ ሲሆን የሱዳን ዋንኛ የገቢና ወጪ ንግዶች መናኸሪያ የሆነው ፖርት ሱዳን ከሃገሪቱ ምጣኔ ኃብት ጥቅምና ክፍፍል ተገለናል የሚል ተቃውሞን ባቀጣጠሉ የቤጃ ጎሳ አባላት አመጽ መዘጋቱና ወደ ኦምዱርስማንና ዋና መዲናይቱ ካርቱም የሚደረገው ትራንስፖርት በዚሁ ለሳምንታት በዘለቀው ሕዝባዊ እምቢተኝነት መዘጋቱ በአገሪቱ ሰላም ማህበራዊ ኑሮና ኢኮኖሚ ላይ አስከፊ ጫናን አሳድሯል:: ጄነራል አልቡህራን ሲቭል አስተዳደሩን አባረው የመሰረቱት መንግሥትም በሃገር ውስጥም በውጭም ከፍተኛ ተቃውሞ ከገጠመው በኋላ በሰሜናዊ የናይል ሪቨር ግዛት ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ተቃውሞን በማቀጣጠል ወታደራዊ ኃይሉ ላይ ሕዝብ እንዲያምጽ እየጎተጎቱ ናቸው ያሏቸውን የውጭ ሃይላት አስጠንቅቀዋል::
"አንዳንድ የውጭ ኃይላት ሕዝቡን ለአመጽ በማነሳሳት ዓለማቀፉ ማህበረሰብ በወታደራዊ ኃይሉ ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንዲያሳድር እየጣሩ ነው:: በሱዳን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የሚገባውን የዲፕሎማትክ ማህበረሰብ በፍጹም አንታገስም:: በሀገሪቱ ደም አፋሳሽ ግጭት እንዲቀሰቀስ በሚደረግ ማናቸውም የውጭ ጣልቃ ገብነት ላይም ህጋዊ እርምጃ የምንወስድ ይሆናል"
ሲቭል አስተዳደሩ ወደ መንበረ ሥልጣኑ እንዲመለስ በመጠየቅ ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ በተካሄዱ ተከታታይ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ከ 58 በላይ ሰላማዊ ዜጎች ሲገደሉ አያሌ ንጹሃንም የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ታውቋል:: የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ባለፈው አንድ ወር ተኩል በተካሄደው ሕዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት ቢያንስ ከ 30 በሚልቁ ሴቶች ላይ የአስገድዶ መድፈርና የፆታ ጥቃት እንዲሁም በሰላማዊ ዜጎች ላይ ግድያና አስከፊ የመብት ጥሰት መፈጸሙን በመጥቀስ ድርጊቱን በጽኑ አውግዟል:: ይህ ሁሉ ግድያ እስርና ጥቃት ያልበገራቸው በሃገሪቱ የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የአስለቃሽ ጋዝና የጥይት እሩምታ ያላንበረከካቸው የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ጠያቂ ሱዳናውያን ከቀን ወደ ቀን የአደባባይ ተቃውሞዋቸውን በማጠናከር የፕሬዝዳንቱን ቤተመንግስት ከአንድም ሶስት ጊዜ በሃይል ጥሰው እስከመቆጣጠር ደርሰዋል::ይህ የማያባራ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ጫናና ተቃውሞ ያሰጋው በሌተናል ጄነራል አልቡርሃን የሚመራው ወታደራዊ ኃይሉ ከበርካታ ውይይትና ድርድር በኋላ ሃምዶክን ወደ ቀደመው ስልጣናቸው ለመመለስ ተገዷል:: ሃምዶክ ለጋዜጠኖች በሰጡት መግለጫ የተለየ ዝናና ክብርን በመሻት ሳይሆን ከዚህ በኋላ ያለአንዳች ጫና ጥምር የሽግግር መንግስቱ የጊዜ ገደብ እስከሚያበቃበት ጊዜ ድረስ የሕዝባቸውን መሰረታዊ ጥያቄዎች በጋራ ለመፍታት በተደረሰ ስምምነት ወደ ኃላፊነት መመለሳቸውን ገልፀዋል::
"አሁን ላይ በሀገሪቱ የተንሰራፋው ደም አፋሳሹ ፖለቲካዊ ቀውስ በሰላም እንዲያበቃ የተደረሰ ወሳኝ ስምምነት ነው:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለ አንዳች ጫና ነጻና ገለልተኛ የሆነ ቴክኖክራቱን ጭምር ያሳተፈ የሲቭል አስተዳደርን እንዲያዋቅር ዕድድልን የሚሰጥ ድርድር ነው የተካሄደው:: እውነቱን በግልጽ መናገር እፈልጋለጉ:: እኔ ከዚህ ውጪ የተለየ የግል ፍላጎት የለኝም:: የተወሰነ ቡድንን ለማስደሰትና ለመቀላቀል የሆነ ፓርቲን ለመደገፍ አልያም ዝናና ዕውቅናን በመሻት አይደለም ወደ ሃላፊነት የተመለስኩትና ለስምምነቱ ተገዢ የሆንኩት:: አሁንም ሆነ ወደፊት ተገዢነቴ በጫንቃዬ የተሸከምኩትን የሱዳን ሕዝብ አደራ ከግብ ማድረስ ነው "
ምንም እንኳን ሃምዶክ ወደ ሥልጣናቸው ዳግም ቢመለሱም በብዙዎች ዘንድ የተፈጠረው የመከዳት ስሜትና አሁንም ወታደር መር በሆነው የሃገሪቱ አገዛዝ ቁጣው የገነፈለው ሕዝብ በቅርቡ ሰላም ያመጣል ተብሎ በተደረሰው ስምምነት ላይ ተስፋው እንዲሟጠጥ ከማድረጉም ሌላ በሃምዶክም ላይ ጭምር ተቃውሞውን ማንጸባረቅ ጀምሯል:: "አምባገነናዊ ወታደራዊ አገዛዝ ይብቃ!" ያሉ ሱዳናውያን ሰልፈኞች በተለይም ባለፈው ሃሙስ በካርቱምና በኦምዱርስማን ከተሞች ከወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ ለ 11 ጊዜ ባካሄዱትና በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተካፈሉበት እጅግ ግዙፍ የተባለውን የዲሞክራሲ ለውጥ አራማጆች ያዘጋጁት የአደባባይ ተቃውሞ ሰልፉን ለመበተን የኃይል እርምጃ እንዲጠቀሙ የታዘዙት የፀጥታ ኃይላት በፈፀሙት ጥቃት በርካቶች ሲገደሉ አያሌ ሰዎች ላይም ጉዳት መድረሱ ታውቋል:: መንግሥት አመጹን ተከትሎ የኢንተርኔት አገልግሎት በአንዳንድ ቦታዎች ማቋረጡ ተረጋግጧል::እስካሁን በጸጥታ ኃይሎች ጥቃትየ 4 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ሲነገር ገለልተኛው የሱዳን የሕክምና ባለሙያዎች ማህበር በየጎዳናውና መስጂዱ የተገደሉና ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ብዛት ለማጣራት ጥረት እያደረገ መሆኑን ሲገልጽ የሳውዲው አል አረቢያ ቴሌቪዥን ጣቢያም የፀጥታ ኃይሎች በጋዜጠኞቹ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ይፋ አድርጓል:: በሱዳን የአሜሪካ ኤምባሲ የመንግሥት ኃይላት በአንድ የራዲዮ ጣቢያ ስቱዲዮ ውስጥ ጋዜጠኞችን ሲደበድቡ የሚያሳይ የቪድዮ ምስል በማህበራዊ ድህረ ገጽ ከተሰራጨ በኋላ ድርጊቱን አውግዞ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸመው ግድያና የኃይል ጥቃት እንዲቆም አሳስቧል:: የተባበሩት መንግሥታት ልዩ ልዑክ ፎከር ፔርዝስ በበኩላቸው በዜጎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት አሳሳቢ መሆኑን በመግለጽ ግድያና የመብት ጥሰቶቹ በገለልተኛ ወገን በአስቸኳይ እንዲጣሩ ጠይቀዋል:: ከወታደራዊው ኃይል ጋር የተደረሰው ስምምነት እየተተገበረ አይደለም ሲሉ ቅሬታቸውን ያሰሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዶክ ከሳምንት በፊት ስልጣን መልቀቃቸው ከገለጹ በኋላ ወዲያው ውሳኔያቸውን መቀልበሳቸው ቢነገርም እየተባባሰ በመጣው ሕዝባዊ ተቃውሞና ሊገታ ባልቻለው የወታደራዊ ኃይሉ ተጽዕኖ ምክንያት ስልጣናቸውን በማንኛውም ጊዜና ሰዓት ሊለቁ ይችላሉ የሚለው ዜና በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን አሁንም ድረስ እየተስተጋባ ይገኛል::
እንዳልካቸው ፈቃደ