1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታገዱ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ወደ ትምሕርት ቤት እንዲመለሱ የሚደረገዉ ግፊት

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 24 2017

ከትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በአክሱም የሚገኙ አራት ትምህርት ቤቶች በአጠቃላይ 159 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ከራቁ 23 ቀናት ሆኗቸዋል

https://p.dw.com/p/4olOK
 ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ትምሕርት ቤት እንዳይገቡ መታገዳቸዉን የተለያዩ ወገኖች ተቃዉመዉታል።
የአክሱም ከተማ ባለሥልጣናት ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ትምሕርት ቤት እንዳይገቡ ካገዱ አንድ ወር ሊሞላቸዉ ነዉ።ምስል Million Haileselassie/DW

አክሱም ዉስጥ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ወደ ትምሕርት ቤት እንዲመለሱ የሚደረገዉ ግፊት

በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ከአለባበሳቸው ጋር በተገናኘ በተላለፈ መመርያ አንድ ወር ገደማ ከትምህርት ውጭ ሆነው ይገኛሉ ሲል የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት አስታወቀ። በአክሱም የሚገኙ 159 ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ከትምህርት ውጭ ከሆነ 23 ቀናት ማለፋቸው ደግሞ የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት ገልጿል። የትግራይ ትምህርት ቢሮ ጉዳዮ አስመልክቶ ባሰራጨው ደብዳቤ አዲስ የአለባበስ አሰራር ባልወጣበት፥ አዲስ ክልከላ ይሁን አዲስ ጥያቄ ተቀባይነት የለውም፥ ትምህርት ቤቶች በነባር የአለባበስ ስርዓት ይቀጥሉ ብሏል።

 

ካለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ በአክሱም ከተማበሚገኙ ትምህርት ቤቶች እየታየነ ነው ከተባለ፥ ሒጃብ የለበሱ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቶች እንዳይገቡ የመከልከል እርምጃ ጋር በተገናኘ ውዝግቡ ቀጥሏል። ከትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በአክሱም የሚገኙ አራት ትምህርት ቤቶች በአጠቃላይ 159 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ከራቁ 23 ቀናት ሆኗቸዋል። ይህንኑ ሁኔታ ያወገዘው የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት፥ ከትላንት በስትያ ማክሰኞ ከትግራይ ትምህርት ቢሮ በተፃፈ ደብዳቤ መሰረት ሴት ሙስሊም ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ገበታቸው ይመለሳሉ የሚል ተስፋ ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም፥ ከትምህርት ገበታቸው እንዲገለሉ ብቻ ሳይሆን ማስፈራርያዎች ጭምር እየደረሳቸው እንዳለ ተገልጿል። ለዶቼቬለ የተናገሩት የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት ፀሓፊ ሓጂ መሓመድ ካሕሳይ፥ የትግራይ ትምህርት ቢሮ ከሰጠው ማብራሪያ በኃላም ቢሆን የተለያዩ ምክንያቶች በመፍጠር ሒጃብ የለበሱ ሴት ተማሪዎች በአክሱም ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተገልለዋል ብለዋል።

አክሱም ዉስጥ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች እንዳይማሩ በመታገዳቸዉ የሚሰማዉ ተቃዉሞ እንደቀጠለ ነዉ
የአክሱም ከተማ በከፊል።የከተማይቱ ባለሥልጣናት ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ትምሕርት እንዳይማሩ አግደዋልምስል Million Hailesilassie/DW

 

በዚህ የአክሱም ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ጉዳይ ትላንት ታህሳስ 23 ቀን 2017 ዓመተምህረት መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ከአለባበሳቸው ጋር በተገናኘ በተላለፈ መመርያ አንድ ወር ገደማ ከትምህርት ውጭ ሆነው እንዳለ፥ ከዚህም አልፎ ተማሪዎቹ እና ቤተሰቦቻቸው ለእስር የተዳረጉበት ሁኔታ ስለመኖሩ ጠቁሟል። የትግራይ ክልል አስተዳደር፣ የፌደራሉ መንግስት እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እንዲሁም የሰብአዊ መብት ተሟጓቾች ይህ የእምነቶች በጋራ የመኖር እሴት የሚሸረሽር ተግባር ልያወግዙ ይገባል እንዲሁም ይህን ተግባር በሚፈፅሙት ላይም እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርቧል።

 

ከዚህ በተጨማሪ ከአክሱም የመረጃ ምንጮቻችን እንደነገሩን ሁኔታው ተባብሷል፣ ትላንት ችግሩ ተፈትዋል በሚል ወደ ትምህርት ቤታቸው ለመመለስ የሞከሩ ተማሪዎች ወደ ፖሊስ ጣብያ ተወስደው ማስፈራርያ እና ዛቻ ደርሶባቸዋል፣ ከዚህም አልፎ ወደአንዳን ተማሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው መኖርያ ቤት በመሄድ ጭምር ማስፈራራቶች አሉ ብለውናል።

 

ከትላንት በስትያ ማክሰኞ ጉዳዩ አስመልክቶ ለአክሱም ከተማ ትምህርት ፅሕፈት ቤትበሚል ደብዳቤ አሰራጭቶ የነበረው የትግራይ ትምህርት ቢሮ፥ በአክሱም ከተማሪዎች የአለባበስ ስርዓት ጋር በተገናኘ አስቀድሞ ከአክሱም እስልምና ጉዳዮች ቀጥሎም ከትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት ቅሬታዎች እንደደረሱት በማንሳት፥ አዲስ አሰራር ባልወጣበት አዲስ ክልከላ ይሁን አዲስ ጥያቄ ተቀባይነት እንደሌለው በማንሳት ትምህርት ቤቶች በነባር የአለባበስ ስርዓት እንዲቀጥሉ ሲል ገልጿ ነበር።

የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እንዳለዉ ሙስሊም ሴት ተማሪዎችና ቤተሰቦቻቸዉ እስራት፣ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸዉ ነዉ
የአክሱም ባለስልጣናት ጂጃብ የሚያስሩ ሴት ሙስሊም ተማሪዎችን ከትምሕርት ገበታ ማገዳቸዉን የትግራይ ክልልና የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤቶች ተቃዉመዉታልምስል Million Haileselassie/DW

በደብዳቤ ዙርያ ማብራሪያ ለማግኘት ወደ ክልሉ ትምህርት ቢሮ የስራ ሐላፊዎች በተደጋጋሚ በመደወል እና በአካል በመቅረብ ምላሽ ለማግኘት ጥረት ብናደርግም አልተሳካም። በተመሳሳይ ጉዳይ ከአክሱም ከተማ ትምህርት ፅሕፈት ቤት ምላሽ ለማግኘት የተደረገ ጥረትም ቢሆን ሐላፊዋ ስልካቸው ባለማንሳታቸው አልተሳካም።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ