1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ «አዲስ ፓሪስ መጽሔት»

ሐሙስ፣ ጥቅምት 8 2016

«አዲስ ፓሪስ» ማለት በአዲስ አበባ እና በፓሪስ ከተሞች ያሉትን የባህል የፍልስፍና፤ የታሪክ እና የቱሪዝም ለየከተሞቹ የሚያስተዉቅ መሳርያ ነዉ። ፓሪስ የሚገኘዉን ለአዲስ አበባ፤ አዲስ አበባ የሚገኘዉን መረጃ ፤ ለፓሪስ ከተማ ማለት ነዉ። ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዝ የፈረንሳይ አገር ጎብኝ «አዲስ ፓሪስ»ን ከያዘ ብዙ ነገሮችን የማግኘት እድል ይኖረዋል።

https://p.dw.com/p/4Xly5
«አዲስ ፓሪስ» መጽሔት የመጀመርያ እትም
«አዲስ ፓሪስ» መጽሔት የመጀመርያ እትም ምስል Addis Paris

«አዲስ ፓሪስ» መጽሔት አዲስ አበባን እና ፓሪስን በባህል በታሪክ በአዉደ-ርእዮችን ጉዳዮች የሚያስተሳስር ድልድይ ነዉ።

«አዲስ ፓሪስ» ማለት  በአዲስ አበባ እና በፓሪስ ከተሞች ያሉትን የባህል የፍልስፍና፤ የታሪክ እና የቱሪዝም ለየከተሞቹ የሚያስተዉቅ መሳርያ ነዉ። ፓሪስ የሚገኘዉን ለአዲስ አበባ፤ አዲስ አበባ የሚገኘዉን መረጃ ፤ ለፓሪስ ከተማ ማለት ነዉ። ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዝ የፈረንሳይ አገር ጎብኝ «አዲስ ፓሪስ»ን ከያዘ ወደ ኢትዮጵያ መዲና ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ በቀላሉ ብዙ ነገሮችን የማግኘት እድል ይኖረዋል። ይህ መጽሔት በሁለቱ ከተሞች መካከል የሚገኝ እንደድልድይ የሚያገለግል መሳርያ ነዉ።  ሲል የገለፀልን የመጽሔቱ ዋና አዘጋጅ ደራሲ አቤል ፊጣ መኮንን ነዉ። 
ደራሲል አቤል ሁለት ካቴና በሚል የልብ-ወለድ መጽሐፉ ይታወቃል። ከሳምንታት በፊት አቤል ፊጣ አዲስ ፓሪስ የሚል ስያሜ የሰጠዉን የመጀመርያዉን በአማርኛ፤ በፈረንሳይኛ እና በእንጊሊዘኛ ያሳተመዉን መጽሔት ፓሪስ ላይ ለአንባብያን ማቅረብ ጀምሯል።

ፓሪስ ከተማ
ፓሪስ ከተማ ምስል DW

አቤል እንደነገረን አዲስ ፓሪስ የሁለቱን ሃገራት መዲና ስሞች ይያዝ እንጂ የባህል የታሪክ የዘመናዊ የጥበብ ጽሑፎች የሚነበቡበት ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይን  የሚያገናኝ ድልድይ ሆኖ የሚሰራ መሳርያ ነዉ ሲል መጽሔቱን ይገልጸዋል። ከዓለም ሃገራት የሚጎርፉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቱሪስቶች የሚጎበኝዋት የፈረንሳይዋ መዲና ፓሪስ በዓለማችን ከሚገኙ የጥበብ እና የባህል ማዕከሎች መካከል አንዷ ከተማ እንደሆነች ይነገርላታል። በፓሪስ ታዋቂ እና በሞገስ የተሞሉ የጥበብ ሙዚየሞች፣ ቤተ-መፃህፍት ፣ ሲኒማ ቤቶች እና የቲያትር አዳራሾች ብሎም ከዓለም የተሰበሰቡ ሞዴሎች ዘመናዊ የተባሉ አልባሳቶቻቸዉን አድርገዉ በየቀኑ የሚታዩባት ሽቅርቅር ከተማ በመሆንዋም ትታወቃለች።
አሁን አሁን ደግሞ ፓሪስ ቆሻሻ ከተማ ሆናለች ሲሉ ከተማዋን ጎብኝተዉ የተመለሱ ቱሪስቶች በምሪት የሚገልጿት ከተማ መሆንዋ በተደጋጋቢ እየተዘገበ ነዉ። የሆነ ሆኖ በፓሪስ ነዋሪ የሆነዉ ጎልማሳዉ ደራሲ አቤል ፊጣ መኮንን በፓሪስ እና በአዲስ አበባ ከተማ መካከል አዲስ ፓሪስ የሚባል መጽሔትን እንደድልድይ ዘርግቶ፤ ኢትዮጵያን እና ፈረንሳይን ለማገናኘት ለዘመናት የያዘዉን እቅድ በቅርቡ እዉን አድርጓል። የፈረንሳዩ አመጽ መንስኤ ፤ዘረኝነትና የቅኝ ግዛት ታሪክ
አቤል ከሳምንታት በፊት ለአንባብያን የቀረበዉ አዲስ ፓሪስ መጽሔት በሦስቱም ቋንቋዎች መታተሙን እና በአንድ መጽሔት ዉስጥ በሦስቱም ቋንቋዎች መረጃን ማግኘት እንደሚቻል ገልጾልናል። ደራሲ አቤል በዚህ በዲጂታል ዘመን ዓለም ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላዉ ጫፍ በቀላሉ በሚገናኝበት ዘመን ቢሆንም፤ መጽሔትን ማሳተሙ ይዞት የነበረዉን የረጅም ጊዜ እቅድ እዉን ለማድረግ እንደሆንም ገልጿል።  
የፈረንሳይ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት የረጅም ዓመታት ወዳጅነትን ያስቆጠረ ነዉ። ከ 130 ዓመታት በላይ ያስቆጠረዉ የኢትዮ - ፈረንሳይ የትብብር ግንኙነት በተለያዩ መስኮች እያደገ መምጣቱ  ይገለፃል። በተለይ ለሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ትልቅ አሻራ የሆነው የቀድሞው የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር (ፍራንኮ-ኢትዮጵያ የምድር ባቡር ድርጅት) የ784 ኪ.ሜ ርዝመት የነበረዉ እና ብቸኛና ባለ አንድ መስመር  የኢትዮጵያ ዋና መዲና አዲስ አበባን እና ጅቡቲ ከተማን የሚያያይዝ የባቡር መስመር  ነበር። የባቡር መስመር ዝርጋታዉ ከሃያ ዓመታት አድካሚ ስራ በኋላ በ1911 ተሰርቶ መመረቁም የታሪክ መዝገባት ያሳያሉ። በምስራቅ ኢትዮጵያ በምትገኘው ድሬዳዋ መንገደኞች አሁንም ከመቶ ዓመት በፊት በፈረንሳዮች የተሠራውን ፍራንኮ-ኢትዮጵያ ባቡርን ይጠቀማሉ። በቅርቡ በቻይና የተዘረጋዉ ዘመናዊ ባቡር ስራ ቢጀምርም፣ የድሮው ባቡር ለንግድ እና ትራንስፖርት አሁንም ተፈላጊ መሆኑ ይነገራል። የፈረንሳይና የኢትዮጵያን ግንኙነት ያዳብራል የተባለዉ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ደራሲ አቤል ፊጣ ወደ መዲና ፓሪስ ከመጣ ስድስት ዓመት እንደሆነዉም ተናግሯል።   የፈረንሳይ ጦር ከኒዤር ለቅቆ እንዲወጣ ተገደደ

አዲስ ፓሪስ መጽሔት በፓሪስ ለአንባብያን መቅረብ ጀመረ
ደራሲ አቤል ፌጣ መኮንንምስል Addis Paris

በመጀመርዉ አዲስ ፓሪስ መጽሔት ሽፋን ላይ ፎቶዋ የሚታየዉ ኢትዮጵያዊትዋ ሞዴል ብሎም ሙዚቀኛ  ሄላር ተስፋዬ  በፓሪስ የፋሽን መድረክ ላይ ተሳትፋለች። የመጀመርያዉ የመጽሔት እትም እዉቁን አዲስ አበቤ እና የፈረንሳይ ከተማ ነዋሪ የነበሩትን አንጋፋዉን የስፖርት ሰዉ የፍቅሩ ኪዳኔን እና የእዉቁ ሙዚቀኛ የክብር ዶክትሬት አሊቢራን የህይወት ታሪክ አስነብቧል። 
በጣም ጥሩ ነዉ እንደዉ ግን ይህን መጽሔት የሚያነብ፤ በተለይ ከኢትዮጵያ ርቆ የሚገኝ አንባቢ፤ ስለኢትዮጵያ ፋሽን እና ታሪክ ሲያነብ፤  ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታም ማሰቡ እና ማንበብ እንደሚፈልግ የገለፀዉ የመጽሔቱ አዘጋጅ ስለኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በጥቂቱም ቢሆን  ለማስነበብ እንደሚጥር ተናግሯል።  
አዲስ ፓሪስ መጽሔት ከመታተምዋ በፊት በዝግጅት እና ሃሳብን በማካፈል ድጋፍ የሰጠዉ ሌላዉ ኢትዮጵያዊ የፓሪስ ከተማ ነዋሪ ጋዜጠኛ መርድ እስጢፋኖስ ይባላል። ጋዜጠኛ መርድ ፓሪስ መኖር ከጀመረ ወደ 12 ዓመት ሆኖታል። የአዲስ ፓሪስ መጽሔት የመጀመርያዋ በፈረንሳይ በአማርኛ የታተመች መችሄት ሲል የዋና አዘጋጁን ጥረት አድንቋል።   
አዲስ ፓሪስ መጽሔት ጎልብታ አድጋ ተመንድጋ በኢትዮጵያ እና በፈረንሳይ መካከል ጠንካራ ድልድይን እንድትገነባ በመመኘት ሙሉዉን ጥንቅር የድምጽ ማዕቀፉን በመጫን እንድታደምጡ እንጋብዛለን። 


አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ