1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«አዲስ አበባን ጥቅም አልባ የማድረግ» እንቅስቃሴ

ማክሰኞ፣ የካቲት 21 2015

በኦሮሚያ ክልል ትናንት ሥራ መጀመሩ በተነገረለት ሸገር ከተማ ውስጥ በታቀፉት ከተሞች ቤታቸው የፈረሰባቸው በርካታ ሰዎች ለሁለንተናዊ ኪሳራ መዳረጋቸውን ገለፁ ። አንደኛ ቅድሚያ ከማልማታችን በፊት ለምን በግልጽ አልተከለከልንም? ሁለተኛ ቤት እየተመረጠ ለምን ይፈርሳል ሲሉም አማረዋል ።

https://p.dw.com/p/4O4Df
Äthiopien | Zerstörte Unterkünfte in Addis Abeba
ምስል Solomon Muche/DW

«የድርጊቱ ሕጋዊነት ላይ ጥያቄ ያስነሳል»

በኦሮሚያ ክልል ትናንት ሥራ መጀመሩ በተነገረለት ሸገር ከተማ ውስጥ በታቀፉት ከተሞች ቤታቸው የፈረሰባቸው በርካታ ሰዎች ለሁለንተናዊ ኪሳራ መዳረጋቸውን ገለፁ ። አንደኛ ቅድሚያ ከማልማታችን በፊት ለምን በግልጽ አልተከለከልንም? ሁለተኛ ቤት እየተመረጠ ለምን ይፈርሳል ሲሉም አማረዋል ።  የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በተቃራኒው የተመሰረተው የሸገር ከተማ በአከባቢው የሚኖሩ ማኅበረሰቦችን በከተማው ባለቤትነት አቅፎ የመልማት ጥያቄዎችን ይመልሳል ሲሉ ተደምጠዋል ። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) እና ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች የፈረሳ ተግባራቱን «የሕግ ሥነ ሥርዓትን ያልተከተሉ» እንዲሁም «አዲስ አበባን ጥቅም አልባ የማድረግ» ተግባር ማሳያ ብለውታል ። የቦረናው የከፋ ድርቅ ከመንግሥት አፋጣኝ ምላሽ እንደሚያሻው አሳስበዋል ። 

ወይዘሮ ትእግሥት የተባሉ ሴት በአረብ ሀገር ሲሠሩ ኖረው ከተመለሱ በኋላ ባጠራቀሟት ገንዘብ በለገጣፎ ለገዳዲ ባዶ ቦታ ገዝተው ቤት ሠርተው መኖር ከጀመሩ አምስት ዓመታት አልፈዋል። ለመብራት እና ለውኃ አገልግሎት ለመንግሥት ተቋማትም የሚጠበቅባቸውን ሲከፍሉ ኖረዋል።  ባለፉት ሳምንታት ግን ቤታቸው ሕገ- ወጥ መስመርን ተከትሎ የተሠራ መሆኑ እንኳን በውል ሳይነገራቸው ፈርሶባቸው አሁን በችግር ለመኖር መገደዳቸውን ይገልጻሉ። «መጀመርያ ሲገቡ ባዶ ቤት ነው የምናፈርሰው አሉ። አጥር እንኳን አይሆንም በጭቅጭቅ ብሏል። ሰባት ዓመት ሰርቼ ነው ሳውዲአረቢያ አምጥቼ ገንዘቤን አፍስሼ ዛሬ ባዶ እጄን የቀረሁት ።» 

የሸገር ከተማ ሥራ መጀመሩ በተገለጠበት ወቅት
የሸገር ከተማ ሥራ መጀመሩ በተገለጠበት ወቅትምስል Seyoum Getu /DW

ሰበታ፣ ቡራዩ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ፣ ሱሉልታ፣ ኤር ሞጆ፣ ገላን ውስጥ የሚታዩ ፈረሳዎች የቤት ግንባታዎቹ ሳይጀመሩ በፊት ማስቆም ሲገባ ብዙ ሀብት ከፈሰሰበት በኋላ እና ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ባለበት ሁኔታ አልፎም ሕጋዊ ቤቶች ጭምር መፍረሳቸው እንዳሳዘነው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ገልጿል ። 

ሌላኛው ቤት የፈረሰባቸው ግለሰብ ሰዎች እየተለዩ ያንዱ ሲፈርስ የሌላው መጠበቁ ይበልጥ አስቆጭቷቸዋል ። ከተሠሩ ከ15 እስከ 20 ዓመታት የሆናቸው ቤቶች መፍረሳቸው የድርጊቱ ሕጋዊነት ላይ ጥያቄ ያስነሳል ሲል የገለፀው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ምትክ ወይም ጊዜያዊ ማቆያ ስፍራ ሳይዘጋጅ ቤታቸው መፍረሱ ተገቢነት የሌለው ነው ብሏል ። 

መኢአድ ፣ እናት እና ኢሕአፓ የተባሉ ፓርቲዎች ደግሞ ድርጊቱ «አዲስ አበባን ጥቅም አልባ የማድረግ ሥራ ማሳያ ነው» ሲሉ ገልፀዋል ። የእናት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ አቶ ጌትነት ወርቁ ።

በዚሁ ጉዳይ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎችን ለማግኘት በተደጋጋሚ ጥረት ባደርግም ለጊዜው አልተሳካም ።

የኦሮሚያ ክልል ርእሠ መሥተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የ
የኦሮሚያ ክልል ርእሠ መሥተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የምስል Seyoum Getu /DW

የኦሮሚያ ክልል ርእሠ መሥተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የተመሰረተው የሸገር ከተማ በአከባቢው የሚኖሩ ማኅበረሰቦችን በከተማው ባለቤትነት አቅፎ የመልማት ጥያቄዎችን እንደሚመልስ ገልፀዋል ። ቤታቸው የፈረሰባቸው ሰዎች ግን ይህ ሲሆን ያወያያቸው እንደሌለ ፣ ማስጠንቀቂያም ቀድሞ እንዳልደረሳቸው እና ካሳም እንደማያገኙ በሐዘን ገልፀዋል ።

በሌላ በኩል ኢሰመጉም ሆነ በጋራ መግለጫ ያወጡት ሦስቱ የፖለቲካ ፖርቲዎች መንግሥት ለቦረና ድርቅ የሚሰጠውን ምላሽ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል ።  ቦረና እና አካባቢው ላይ በድርቁ ለተጎዱት ዜጎች ድጋፍ ይዞ ለመድረስ ግለሰቦች ፣ ድርጅቶችና የመንግሥት ተቋማት ርብርብ እያደረጉ ሲሆን የኦሮሚያ ክልልም የድጋፍ ጥሪ አሰምቷል ።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ