1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ በነዳጅ የሚሠሩ መኪኖችን በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለመተካት ዝግጁ ነች?

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ጥር 22 2016

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት በነዳጅ የሚሠሩ አውቶሞቢሎች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ መወሰኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ ተናግረዋል። የነዳጅ ወጪ እና የከባቢ አየር ብክለትን ለመቀነስ የተላለፈው ውሳኔ በርካታ ጥያቄዎች የሚነሱበት ነው። በእርግጥ ኢትዮጵያ ፊቷን ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለማዞር ዝግጁ ነች?

https://p.dw.com/p/4btPD
አዲስ አበባ ጋዜቦ አካባቢ
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ “ማንኛውም የቤት አውቶሞቢል የኤሌክትሪክ ካልሆነ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ መንግሥት ውሳኔ አስተላልፏል” ሲሉ ተናግረዋል። ምስል Eshete Bekele/DW

ኢትዮጵያ በነዳጅ የሚሠሩ መኪኖችን በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለመተካት ዝግጁ ነች?

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ ይፋ ያደረጉት እና በነዳጅ የሚሠሩ የቤት አውቶሞቢሎች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ የሚከለክለው የመንግሥት ውሳኔ በተሽከርካሪ ገበያው ሥጋት እና ግራ መጋባት ፈጥሯል። ዶክተር ዓለሙ ውሳኔውን የገለጹት ጥር 20 ቀን 2016 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ-ልማት እና የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ፊት ቀርበው የመሥሪያ ቤታቸውን የ6 ወራት የሥራ አፈጻጸም ባቀረቡበት ወቅት ነው።

“ማንኛውም የቤት አውቶሞቢል የኤሌክትሪክ ካልሆነ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ መንግሥት ውሳኔ አስተላልፏል” ሲሉ ዶክተር ዓለሙ ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ተናግረዋል። መንግሥት ውሳኔውን ካሳለፈባቸው ምክንያቶች አንዱ የኢትዮጵያን የነዳጅ ወጪ ለመቀነስ ነው። ሀገሪቱ በ2015 ነዳጅ ለመሸመት 4.1 ቢሊዮን ዶላር ወጪ አድርጋለች። ይኸ ከዕቃዎች የወጪ ንግድ ካገኘችው ገቢ በ500 ሚሊዮን ዶላር ገደማ የላቀ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ላሳለፈው ውሳኔ ሁለተኛ ገፊ ምክንያት በተሽከርካሪዎች አማካኝነት የሚደርሰውን የአየር ብክለት መቀነስ ነው። “አዳዲስ ወደ ሀገር ቤት የሚገቡ፤ ሀገር ውስጥ የሚገጣጠሙም የኤሌክትሪክ ብቻ እንዲሆኑ አቅጣጫ ተቀምጧል” ያሉት ዶክተር ዓለሙ ውሳኔው የአየር ብክለትን በመቀነስ ረገድ “የሚያመጣው ለውጥ አለ” ሲሉ ተደምጠዋል።

ወደ ኢትዮጵያ ከሚገቡ ተሽከርካሪዎች አብዛኛዎቹ ለግለሰቦች ጥቅም የሚሰጡ መሆናቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሩ “እነዚህን መቀነስ ማለት በአየር ብክለት ላይ የሚደርሰውን ተጽዕኖ በእጅጉ ይቀንሳል” ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ያሳለፈውን ውሳኔ የተመለከተ መመሪያ እስካሁን ይፋ አልተደረገም። የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ የሕግ አማካሪ አቶ ዋሲሁን አባተ “በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች አገር ውስጥ እንዳደይገቡ” የሚከለክል ውሳኔ አለመኖሩን እንደተናገሩ ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።

በጉዳዩ ላይ ዶይቼ ቬለ ከኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር እና ከጉምሩክ ኮሚሽን ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልሰመረም።

አዲስ አበባ ብሔራዊ ቴዓትር
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ መወሰኑን ያስታወቀው የነዳጅ ወጪ እና የአየር ብክለትን ለመቀነስ በሚል ነው። ምስል Eshete Bekele/DW

ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የመኪና ነጋዴዎች እንደሚሉት የመንግሥት አካሔድ ቀድሞም የውጭ ምንዛሪ እጥረትን በመሳሰሉ ምክያቶች የተወደደው የተሽከርካሪ ዋጋ የበለጠ እንዲጨምር የሚያደርግ ነው። በአዲስ አበባ የተሽከርካሪ ንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩት አቶ መሳይ መታፈሪያ ከ1.4 ሚሊዮን ብር እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር ይሸጡ የነበሩ “ትናንሽ መኪኖች” ዋጋ በእጥፍ ጨምሮ ሦስት ሚሊዮን ብር ገደማ መድረሱን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

“በፊት በ500 መቶ ሺሕ ብር እና በ600 ሺሕ ብር መኪና ይገዛ ነበረ” የሚሉ ሌላ የተሽከርካሪ ነጋዴ በአሁኑ ወቅት በተመሳሳይ የገንዘብ መጠን መግዛት የሚቻለው ከ35 እስከ 40 ዓመታት ያገለገሉትን እንደሆነ በመጥቀስ በገበያው የታየውን ልዩነት ያስረዳሉ።

በኢትዮጵያ ተሽከርካሪ የሚገጣጥሙ ኩባንያዎች ቢኖሩም ገበያው በዋንኛነት ከሌሎች ሀገራት በሚገቡ መኪኖች ላይ ጥገኛ ነው። ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ጉልበት እና የአገልግሎት ጊዜያቸውን መሠረት በማድረግ የተለያየ ኤክሳይዝ ታክስ ይከፈልባቸዋል። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የመኪና ነጋዴ በገበያ ለሽያጭ የሚቀርቡት ተሽከርካሪዎች በአብዛኛው የኤሌክትሪክ መሆናቸውን ያስረዳሉ።

“መኪና ለመግዛት ስትወጣ በኢትዮጵያ ገበያ የምታገኘው የኤሌክትሪክ መኪና ነው። ስለዚህ መኪና እንዲኖርህ ከፈለክ ግዴታ ትገዛለህ። ያለበለዚያ ከሰው ላይ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችን ነው የምትገዛው” የሚሉት ነጋዴ ዋጋውም ቢሆን መወደዱን ተናግረዋል። “የሰዉ አቅም እና የገበያው ሁኔታ በጣም ተራርቋል” የሚሉት ነጋዴ ዝቅተኛው የኤሌክትሪክ መኪና የመሸጫ ዋጋ ሁለት ሚሊዮን ብር እንደሆነ ተናግረዋል።

ዋጋቸው እጅግ ውድ ቢሆንም በአዲስ አበባ የመኪና መሸጫ መደብሮች የቴስላ ቅንጡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ባለፉት ዓመታት መታየት ጀምረዋል። የጀርመኑ ፎልክስ ቫገን እና የቻይና የኤሌክሪክ መኪኖችን በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ማየትም እምብዛም እንግዳ አይደለም።

አዲስ አበባ ቤተል አካባቢ
የኢትዮጵያ መንግሥት ፊቱን ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለማዞር መወሰኑን ቢገልጽም ሀገሪቱ ገና የኃይል መሙያ ጣቢያዎች የሏትም። ምስል Eshete Bekele/DW

የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ማዘንበሉን የታዘቡት ነጋዴ ግን “ለገዢው አይደለም እኛ መኪና ላይ የኖርን ሰዎች ይኸን ግዙ ብሎ ለሰው ለማማከር በቂ እውቀት የለንም። ይኼን ቴክኖሎጂ ለሰዉ ለማስተማር ብዙ ነገር ያስፈልጋል” ሲሉ ሽግግሩ እንዲህ በቀላሉ እንደማይከወን ያላቸውን እምነት ይገልጻሉ።

አቶ መሳይ በበኩላቸው መንግሥት ውሳኔውን ከማሳለፉ በፊት “ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ የኤሌክትሪክ መኪኖች ደረጃ ማውጣት ያስፈልገው ነበር” የሚል አቋም አላቸው። በመኪና ንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ መሳይ “እንደ ኃይል መሙያ ጣቢያ የመሳሰሉ መሠረተ-ልማቶች መንግሥት ቀድሞ ማዘጋጀት ነበረበት። አሁን ያ ሁሉ ባልተሟላበት ስለሆነ የመጣው ትንሽ አስቸጋሪ አድርጎታል” ሲሉ ተናግረዋል።

ከሊቲየም በተሠራ ባትሪ የሚንቀሳቀሱት የኤሌክሪክ ተሽከርካሪዎች እንደ ነዳጅ ማደያ ሁሉ የኃይል መሙያ ጣቢያ ያስፈልጋቸዋል። ኦን ኢነርጂ የተባለው አማካሪ ኩባንያ ተባባሪ መሥራች እና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ፍላጎት ተስፋዬ ኢትዮጵያ በነዳጅ ከሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ለመላቀቅ ለምታደርገው ጥረት “ተጨማሪ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ያስፈልጋል” ሲሉ ይናገራሉ።

የፎልክስ ቫገን የኤሌክትሪክ መኪና
የፎልክስ ቫገን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በአዲስ አበባ አውራ ጎዳናዎች በብዛት መታየት ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ምስል Reuters/M. Rietschel

የተሽከርካሪዎቹ እንቅስቃሴ በከተሞች ብቻ የተገደበ እንኳ ቢሆን “ምን ያክል ያልተቋረጠ የኤሌክትሪክ አቅርቦት አለ? አንድ መኪና መሀል ላይ ኃይል መሙላት ቢፈልግ ኤሌክትሪክ ከሌለ ይቆማል” የሚሉት ፍላጎት በመደበኛው የኤሌክትሪክ አቅርቦት ላይ የሚያሳድረው ጫና ሊጤን ይገባል የሚል አቋም አላቸው።  

ከሁለት ዓመታት በፊት የዓለም ባንክ ይፋ ያደረገው ሰነድ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኘው 54 በመቶ ገደማ ብቻ እንደሆነ ያሳያል። በነዳጅ ከሚሠሩ መኪኖች ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚደረገውን ሽግግር በተመለከተ የሚተላለፍ ውሳኔ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን ጉዳዩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና ውኃ እና ኢነርጂ የመሳሰሉ መሥሪያ ቤቶች ሊያሳትፍ እንደሚገባ ፍላጎት ይሞግታሉ።

የተቋማቱ ዓመታዊ እና የ2030 ዕቅዶች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚያስፈልጋቸውን ኃይል ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ እንዳልሆነ የሚናገሩት የኦን ኢነርጂ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሽግግሩ ባደጉት ሀገሮች እንደሚታየው ደረጃ በደረጃ ሊሆን እንደሚገባ ይመክራሉ። “መሠረተ-ልማቱ አልተዘጋጀም። ሌሎች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችም ይኸን ለማድረግ ዝግጁ አይመስሉኝም” የሚሉት የኤሌክትሪክ ምኅንድስና ባለሙያዋ “ጅማሮው ጥሩ ነው። ነገር ግን ተግባራዊ ወደ ማድረግ የምንመጣበት ሰዓት አሁን አይደለም” ሲሉ ይመክራሉ።

በዚህ ዘገባ ላይ ከኢትዮጵያ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ተጨማሪ ማብራሪያ ለማካተት የተደረገው ጥረት አልተሳካም።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ