ኢትዮጵያ በአፍሪቃ ጨዋታዎች ተጨማሪ ወርቅ አገኘች
ረቡዕ፣ መጋቢት 11 2016ጋና አክራ ውስጥ በሚከናወነው የአፍሪቃ ጨዋታዎች የኢትዮጵያ ቡድን እንደተጠበቀው ተጨማሪ የወርቅ ሜዳሊያ አገኘ ። ዛሬ ጠዋት በተከናወነው የ20 ኪሎ ሜትር የወንዶች የርምጃ ፉክክር በአትሌት ምስጋና ዋቁማ ኢትዮጵያ ወርቅ አግኝታለች ። በተመሳሳይ የሴቶች የርምጃ ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ስንታየሁ ማስሬ ብር ሜዳልያ አስገኝታለች ።ዛሬ የተገኙትን ሜዳሊያዎች ጨምሮ ኢትዮጵያ በሜዳሊያ ሰንጠረዥ ደረጃዋ ወደ 10ኛ ከፍ ብሏል ። እስከ ሰኞ ከሰአት ድረስ የኢትዮጵያ ቡድን በሜዳሊያ ሰንጠረዥ 26ኛ ነበር ።
ከኢትዮጵያ ቡድን ከበላይ ሞሮኮ በአምስት ወርቅ፤ ኤርትራ በስድስት ወርቅ 9ኛ እና 8ኛ ላይ ይገኛሉ ። የኢትዮጵያ ቡድን እስካሁን አምስት የወርቅ፤ 3 የብር እና 1 የነሐስ ሜዳሊያ አግኝቷል ። የወርቅ ሜዳሊያ በተጨማሪ ያስገኙት፦ ንብረት መላክ በ10,000 ሜትር ወንዶች፤ በ3000 ሜትር መሰናከል ወንዶች ፉክክር ፍሬው ደቢሳ ናቸው ። በሴቶች የ5000 ሜትር ፉክክር መዲና ኢሳ እና በሴቶች 800 ሜትር ጽጌ ዱጉማ ተጨማሪ ወርቅ አስገኝተዋል ።
የኢትዮጵያ ቡድን ዛሬ ከሰአት በሚኖረው የሴቶች የጦር ውርወራ የፍጻሜ ፉክክር አትሌት የሺወርቅ አንማው እና ድንገቴ አዶላን ለተጨማሪ ሜዳሊያ ያወዳድራል ። ከሰአት በሚኖረው የ3000 ሜትር የሴቶች መሰናከል ሩጫ ውድድርም አትሌት ዓለማየሁ ወለተጂ፤ አትሌት ሎሚ ሙለታ እና አትሌት ፍሬሕይወት ገሠሠ ለሜዳሊያ ይጠበቃሉ ። ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ኬቻማን ዖጁሉ እና በቀለ ጂሎ የሚፎካከሩበት የሦስት ጊዜ መስፈንጠር ዝላይ የፍጻሜ ፉክክርም ዛሬ ከሰአት ይካሄዳል ። በወንዶች 800 ሜትር የፍጻሜ ፉክክር አትሌት ዮሐንስ ተፈራ ዛሬ ከሰአት ለሜዳሊያ ይፎካከራል ። የሴቶች እና የወንዶች የአራት አትሌቶች የ100 ሜትር የዱላ ቅብብል ፉክክርም ዛሬ ይከናወናል ። በ400 ሜትር የተሳተፈው የወንዶች ቡድን ከግማሽ ፍጻሜው ውድድር ማለፍ ሳይችል ቀርቷል ። የመጋቢት 9 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሁለተኛ ሳምንቱን ባስቆጠረው እና የተለያዩ የስፖርት ዘርፎችን በሚያካትተው የአፍሪቃ ጨዋታዎች ግብጽ አሁንም በበላይነት ትመራለች ። ግብጽ እስካሁን 92 የወርቅ፤ 40 የብር እና 33 የነሐስ በድምሩ 165 ሜዳሊያዎችን ሰብስባለች ። ናይጄሪያ 31 የወርቅ፤ 22 የብር እንዲሁም 32 የነሐስ በድምሩ 85 ሜዳሊያዎችን ሰብስባ የሁለተኛ ደረጃ ይዛለች ። ደቡብ አፍሪቃ በ27 የወርቅ፤ በ29 የብር እና በ38 የነሐስ በድምሩ 94 ሜዳሊያ የሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ።
የኤርትራ ቡድን 6 የወርቅ፤ 2 የብር እና 5 የነሐስ በድምሩ 13ሜዳሊያዎችን ሰብስቦ ከአንድ እስከ ዐሥር ካሉት ሃገራት ተርታ በመሰለፍ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። የፊታችን ቅዳሜ በሚጠናቀቀው የአፍሪቃ ጨዋታዎች፦ እግር ኳስ፤ የእጅ ኳስ፤ ነጻ ትግል፤ ባድሜንተን፤ የውኃ ዋና፤ ጁዶ፤ ቴኳንዶ፤ ብስክሌት፤ ቴኒስን ጨምሮ በ23 የስፖርት ዘርፎች ግጥሚያዎች ይኖራሉ ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ታምራት ዲንሳ