1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ እና ስደተኞች

ሐሙስ፣ የካቲት 16 2009

ኢትዮጵያ ከስደተኞች መተላለፊያ ሀገራት አንዷ ናት ። ኢትዮጵያ የሚገኙ የኤርትራ የሶማሊያ እና የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ምኞት ወደ አውሮጳ መሻገር ነው ። በሀገሪቱ ከ800 ሺህ በላይ ስደተኞች ይገኛሉ ። ስደተኞቹ ወደ አውሮጳ ለመሻገር አደገኛውን ጉዞ እንዳይጀምሩ ባሉበት የሥራ እድል እንዲያገኙ የአውሮጳ ህብረት ለኢትዮጵያ ድጋፍ መስጠት ይፈልጋል

https://p.dw.com/p/2Y5SK
Bildergalerie Flüchtlingscamp Tigray in Äthiopien
ምስል Milena Belloni

Integration statt Lagerzwang - MP3-Stereo


አቧራማው መንገድ ዳር ከሚገኘው አነስተኛ ቡና ቤት ሙዚቃ ይሰማል ። በአቅራቢያው ገበያተኞች ሽንኩርት ድንች እና ሀብሀብ የሚሸጥባቸውን ትናንሽ ሱቆች አጨናንቀዋል ። ሌሎች ደግሞ ቀሚስ ካናቴራ እና ጫማዎች ይመለከታሉ ። ክብሮም አነስተኛ ሱቁ ውስጥ የሚገኙትን እቃዎች በመልክ በመልክ ያደራጃል ። በሱቁ ውስጥ ትላልቅ የስፖርት ሻንጣዎች በጀርባ የሚታዘሉ ቦርሳዎች ዘመናይ የወይዛዝርት ቦርሳዎች አሉ በሱቁ ውስጥ ። 
«እቃዎቹን የምገዛው እኔ ራሴ ነኝ ። ወደ ሽሬም ሆነ ሌላ አጎራባች ከተማ መሄድ እችላለሁ ። ብዙ እቃ ከሸጥኩ ለበዓላት ፈቃድ እወስድ እና ወደ አዲስ አበባ ሄጄ ከዚያ ገዝቼ እመጣለሁ ።  »
ክብሮም ኤርትራዊ ነው ። ሀገሩን ጥሎ ከወጣ 8 ዓመት ሊሞላው ነው ። ክብሮም በትግራዩ የማይ አይኒ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ ነው ያለው ። በሌሎች አገራት የስደተኞች መጠለያዎች እንደሚታየው እዚህ የብረት አጥር የለም ትላለች ስደተኞቹ የሚገኙበትን የማይ አይኒን መጠለያ የጎበኘችው ሊንዳ ሽታውደ ። ያነጋገረቻቸው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባልደረባ አቶ ሙሉጌታ ዘውዴ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ስደተኞችን አትጫንም ።
«ኢትዮጵያ ስደተኞችን አንድ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ አትዘጋባቸውም ። ይህ መርህዋ ነው  ። ለምሳሌ ስደተኞች ከመጠለያው ውጭ የሚኖሩ ቤተሰቦች ካሏቸው ከነርሱም ጋር መኖር ከፈለጉ እንፈቅድላቸዋለን ።»
በአሁኑ ጊዜ 30 ሺህ የሚደርሱ ኤርትራውያን የዚህ መርህ ተጠቃሚ ናቸው እንደ 
 አቶ ሙሉጌታ ።ወደፊት ደግሞ ሁሉም ስደተኞች የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል  ።ሀገሪቱ ከኤርትራ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን የመጡ በአጠቃላይ 800 ሺህ ስደተኞችን ተቀብላ ታስተናግዳለች ። የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እንደሚለው 2 ሺህ ኤርትራውያን በየወሩ ወደ ኢትዮጵያ ይሰደዳሉ ። የስደተኞቹም ፍላጎት በሌላ ሦስተኛ ሀገር መስፈር ነው ። ይህ እድል ግን እጅግ ጠባብ ነው ። በዚህ የተነሳም ከስደተኞቹ 10 በመቶው ብዙ ገንዘብ በሚያስወጣው እና በአደገኛው ጉዞ የሱዳንን የሰሃራን እና የሊቢያን በረሃ አቋርጠው በሜዲቴራንያን ባህር በኩል አውሮጳ ለመድረስ ይሞክራሉ ። ማይአይኒ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ የሚኖረው የ28 ዓመቱ ኤርትራዊ አድሀኖም ከአገሩ የተሰደደው ገንዘብ አጠራቅሞ ቤተሰቦቹን ለመርዳት ነበር ። ከ8 ዓመት አንስቶ ግን ሥራም ሆነ ሌላ ተስፋ የለውም ። 
«እዚህ ያሰረኝ  የገንዘብ እጦት ነው ። ገንዘብ ቢኖረኝ ኖሮ ፣ ወደ አውሮጳ ለመሄድ እሞክር ነበረ። ምናልባት ልሞትም እችላለሁ ። ግን ያ ገንዘብ ኖሮኝ ቢሆን ኖሮ የትኝም ይሁን የት ሰርቼ ቤተሰቦቼን መርዳት እችል ነበር ። ስለዚህ እድሉን ካገኘሁ በአፋጣኝ እሄዳለሁ ። »
ኑሮ በማይ አይኒ ተስፋ ላስቆረጣቸው ስደተኞች ህይወት ሲኦል ሆናባቸዋለች ። ሽሬ የሚገኘው የUNHCR ቢሮ እንደሚለው ድርጅታቸው በቂ ገንዘብ ካገኘ ስደተኞች የራሳቸውን ገቢ ሊያገኙ የሚችሉባቸውን መንገዶች ለማጎልበት ይችላል ። በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ መንደሮች ግንባታ የውጭ ባለሀብቶችን ማስገባት የሚፈልገው የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ አማካይነት ለስደተኞች የስራ እድል እንዲገኝ ይፈልጋል ።   የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ባልደረባ አቶ ሙሉጌታ ዘውዴ
«ከስደተኞች የተወሰነው ፐርሰንት ከነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተጠቃሚ መሆን አለባቸው ። ይህም ስደተኞቹ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩበትን ሂደት ለማቀላጠፍ ይረዳል ። ስደተኞች ከህብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው መኖር አለባቸው የሚል እምነት አለን ።» 
በዚሁ መሠረት የኢንዱስትሪ ፓርኩ ከሚፈጥረው የሥራ እድል አንድ ሦስተኛው ለስደተኞች እንዲያዝ ታስቧል ። የአውሮጳ ኢንቬስትመንት ባንክ ለኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ግንባታ የ 200 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለመስጠት ይፈልጋል ። የአውሮጳ ህብረት ለዚሁ ሥራ የሚውል የ50 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ይሰጣል ።»
በአዲስ አበባ የአውሮጳ ህብረት መልዕክተኛ ፍራንቼስኮ ካሬራስ እንደተናገሩት ህብረቱ በዚህ ገንዘብ ስደተኞችን መርዳት ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ ሥራ አጥ ወጣቶች ስራ የመፍጠር ዓላማ አለው ።ከሰሀራ በስተደቡብ ለሚገኙ ሀገራት ታስቦ በተጀመረው ፕሮጀክት ደግሞ 100 ሺህ የሚደርሱ የሥራ እድሎችን ለመፍጠርም ታቅዷል ። ይህ ብቻውን ለስደተኞች መፍትሄ ባይሆንም  እንደ አንድ ጥሩ ጅማሪ ተወስዷል ።

Äthiopien Flüchtlingslager Flüchtlinge aus Eritrea
ምስል Reuters/T. Negeri
Eritrea Kinder im Flüchtlingslager in der Region Tigrai Äthiopien
ምስል Reuters/T. Negeri

ሊንዳ ሽታውደ

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ