1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ፦ግጭት በአራቱም ማእዘናት

ዓርብ፣ መስከረም 12 2010

በኢትዮጵያ በተለያዩ ስፍራዎች የብሔሮች ግጭት ተከስቶ የሰው ሕይወት ጠፍቷል። በርካቶች የግጭቱ መንስዔ በብሔር ላይ የተመሰረተው የፌዴራል ሥርዓት ነው ይላሉ። በኢትዮጵያ የቴሌኮም መገልገያ መሣሪያዎች ምዝገባ ግዴታም አነጋጋሪ ኾኗል።

https://p.dw.com/p/2kV8S
Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

በርካቶች የሞቱበት፥ በሺህ የሚቆጠሩትም የተፈናቀሉበት የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት በሳምንቱ የማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች አብይ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል። ቀደም ሲል በጉጂ እና በቡርጂ ብሔሮች መካከል የነበረው ግጭት ቀዝቀዝ ማለቱ ሲነገር በቅማንት እና በአማራ ተወላጆች መካከል በተቀሰቀሰ ሌላ ግጭት ደግሞ ሰዎች መሞታቸው ተገልጧል። ኢትዮ ቴሌኮም በኢትዮጵያ የቴሌኮም መሣሪያዎች በአጠቃላይ እንዲመዘገቡ የሰጠው ቀነ ገደብም በርካቶችን አነጋግሯል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ሥፍራዎች የተለያዩ ብሔሮች ግጭት ያሳሰባቸው የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ተጠቃሚዎች የግጭቶችን መንሥዔ በመጥቀስ የተለያዩ ትንታኔያቸውን ሰጥተዋል። በርካቶች በሰጡት አስተያየት የሰሞኑ ግጭት ድንገት የተከሰተ እንዳልሆነ፣ ይልቁንስ ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የከረመ መሆኑን ጠቅሰዋል። ለዚህ ሰበቡ ደግሞ ይላሉ አብዛኛዎቹ አስተያየት ሰጪዎች። ለዚህ ሰበቡ በብሔር ላይ የተመሰረተው የፌዴራል ሥርዓት ነው ሲሉ ይሞግታሉ። በሌላ ወገን የቆሙት ደግሞ የለም የብሔር ፌዴራሊዝም ሥርዓቱ በአሁኑ ወቅት ሊኮነን አይገባውም፤ ገና በሙከራ ላይ ነው፤ ጊዜ ሊሰጠው ይገባል ሲሉ ተደምጠዋል። 

በየቦታው የብሔሮች ግጭት፤ የሰዎች ሞት እና መቁሰል ያሳሰበው የፌስቡክ ተጠቃሚ ዮሴፍ ተገኝ፦ «‘ከእንትን ብሔር ይህን ያህል ሲሞቱ ከእንትን ብሔር ደግሞ ይህን ያህል ሞተዋል‘የሚል ዜና በየቦታው ይታያል። በስመአብ!! በቃ አገሬ እንዲህ ሆነች?? ለምን በዚህ ዘመን ፈጠረኝ ግን?» ሲል ምሬት የተቀላቀለበት ጥያቄውን አስፍሯል።

«እራስ ምታት የፈጠረው እኮ ሕገመንስግት ተብየው ነው። አሁን ቡርጂና ጉጂ፤ አማራና አፋር፤ ቅማንትና ጎንደር …እረ ተወኝ ጌታው» ያለው ደግሞ ከኢትዮጵያ በዋትስአፕ አድራሻችን መልእክቱን የላከልን ተከታታያችን ነው። 

Karte von Äthiopien
ምስል DW/E.B. Tekle

ለበርካታ ሰዎች ሞት እና በሺህዎች ለሚቆጠሩት ደግሞ የመፈናቀል ሰበብ የሆነው የኦሮሚያ እና የኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት አሁንም አሳሳቢነቱ አላከተመም። በየቦታው ስለተከሰተው ግችት የዋትስአፕ ተከታታያችን በድምፅ መልእክት ልኮልናል። 

ቀደም ሲል የሶማሌ ክልል በአወዳይ የሞቱ የክልሉ ተወላጆችን ለማሰብ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የሐዘን ቀን ማወጁ ይታወሳል። በተለይ የመስከረም ሁለቱን «የአወዳይ ጭፍጨፋ» በሚል በመሰየም የክልሉ ባንዲራ ዝቅ ብሎ እንደሚውለበለብ ማድረጉ ተገልጧል። 

ሞሐመድ አዩብ በፌስቡክ በሰጠው አስተያየት «ፌዴራሊዝም ስርዓት ችግር ሳይሆን መንግስት ያሉበትን ችግሮች መቅረፍ ማስተካከል አለበት» ይላል። ሞሐመድ በሀገሪቱ አለ ያለው እድገት «የተገነባው በፌዴራል ስርዓት ነው» ሲል አክሏል። በውጭ የሚኖሩ ስደተኞች «70% ለሃገራችሁ ለውጥ እና እድገት አይናችሁ ደም ይለብሳል» ሲልም ጽሑፉን አጠቃሏል።

አማራና ቅማንት ተቀላቅለው በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የተኪያሄደውንና ግጭት የተከተለውን  ሕዝበ-ውሳኔ በተመለከተ ዕውነቱ ለነጻነት በፌስቡክ ባሰፈረው መልእክት፦ «ያለ ህዝብ ፍላጎት ወደ ቅማንት አስተዳደር የተካለሉት 62 ቀበሌዎች ላይም ህዝበ ውሳኔ ይደረግ!» ብሏል።

በትዊተር ተቀራራቢ ሐሳብ የሰነዘረው ሚኪያስ የአዲስ ጋዜጣ ትዊተር መልእክት ላይ በሰጠው አስተያየት፦ «42ቱ ቀበሌዎች መጀመሪያውኑ ያለ ሕዝበ ውሳኔ በምን መስፈርት ነው የቅማንት እራስ ገዝ እንዲሆኑ የተወሰነው? ሙሉ ነዋሪው ቅማንት ስለሆነ ነው?» ሲል ጠይቋል። የአዲስ ጋዜጣ የትዊተር መልእክት፦ የሰው ሕይወት ያስከተለው ግጭት የተከሰተው በቅማንት «የራስ አስተዳደር» ሕዝበ ውሳኔ ምክንያት እንደሆነ በመጥቀስ ቅማንቶች በምርጫው ተጭበርብረናል ሲሉ አማራዎች ደግሞ ህዝበ ውሳኔ ባልተካሄደባቸው በ42 ቀበሌዎች እንዲካሄድ መፈለጋቸውን ይገልጣል። 

በዋትስአፕ ከኢትዮጵያ የደረሰን ሌላ መልእክት እንዲህ ይነበባል።  «በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ሀብሩ ወረዳ ከአፋር ጋር ከባድ ጦርነት ነው የዜና ሽፋን ይኑረው» ይልና በሁለቱም ወገን ሞቱ ያለውን ቁጥር አስፍሯል። ተጨማሪ ከኢትዮጵያ በዋትስአፕ የደረሰን መልእክት ላኪ ነዋሪነቱ በአፋርና አማራ አዋሳኝ አካባቢዎች እንደሆነ ተናግሯል። «እኔ አፋር እና አማራ ክልል የሚታዋስነው ወረዳ /ሀብሩ/ነዋሪ ነኝ። ግጭቱን ለማብረድ የሚወሰደው ርምጃ ለይስሙላ ነው»  ብሏዋል። ​​​​​​​

Äthiopien Stadt Jijiga
ምስል DW/T. Waldyes

«እኔ ያለሁት ግጭቱ ካለበት ቦታ ነው እሳተፋለሁም። ፀቡ የተነሳው በደንበር ጉዳይ ነው። አሁን እርቅም የለም እየተጋደልን ነው። መንግስትም መፍትኄ አላመጣም። ጉዳዩ እየተባባሰ ነው። በስሜን ወሎ ሀብሩ ወረዳ ነው ቁጥር 024 ጃራ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ነው። አዲስ ነገር ካለ እጠቁማቹሀለሁ» በዋትስአፕ የደረሰን መልእክት ነው። ሌላ ከኢትዮጵያ በዋትስአፕ የደረሰን መልእክት የግጭቶች ሰበብ ያለውን ለመጠቃቀስ ይሞክራል። 

እዚህም እዚያም የተጫረው ግጭትና ሞት አሜሪካንንም ያሳሰበ ይመስላል። አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በበኩሉ በምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ስለተከሰተው ግጭት መግለጫ አውጥቷል። ኤምባሲው በኦሮሚያ-ሶማሌ ድንበር የተከሰተውን የጎሳ ግጭት አስመልክቶ መስከረም 9፤ 2010 ዓ.ም. ያወጣውን መግለጫ በርካቶች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተቀባብለውታል። 

«በኦሮሚያ እና ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች በተለይም በሐረርጌ  የጎሳ ግጭትን እና የበርካታ ሰዎችን መፈናቀል አስመልክቶ በሚወጡ አሳሳቢ ዘገባዎች ተረብሸናል፤ ምንም እንኳ ዘገባዎቹ ስለሁኔታው ዝርዝር መረጃ ስለማቅረባቸው ግልጽ ባይሆንም» የሚለው የኤምባሲው መግለጫ፦ «የኢትዮጵያ መንግሥት ግጭቱን ግልጽ በሆነ አካሄድ እንዲያጣራ እና አጥፊዎችን ተጠያቂ እንዲያደርግ እንጠይቃለን፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ፤ ግጭቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲሹ መበረታታት ይኖርባቸዋል» ሲል አክሏል። 

«ኢትዮጵያ ጠንካራ፤ የበለጸገች እና ዴሞክራሲያዊት ሀገር መሆን የምትችለው፤ ግልጽና ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት፤ ግልጽ የመንግሥት አሠራር፤ እንዲሁም የዴሞክራሲ እና የፍትህ ተቋማትን ማጠናከር ስትችል እንደሆነ እናምናለ» ሲልም ነው መግለጫው የሚጠናቀቀው።

«ይህ ሁሉ ግጭት የኢትዮጵያ ህዝብ ከማያቀው ጣጣ ወንድሙን አባቱን እናቱን እህቱን እየተገዳደለ ያለው የገዥው ሰርአት የመልካም አሰተደደረ እጦት፤ ከምንም በላይ የተሰራፋው የሙሥና መግነን ነው። ከምን በላይ የኪራይ ሰብሣቢ ባለሥልጣን መበራከትና የኢትዮጵያ ህዝብ ችግራቸውን ነቅሦ እደያወጣበቸው የሚደረግ ሴራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ መረደት ያለበት ይመሥለኛል» ይላል። በብሔረ እና በድንበር ምክንያትም ኢትዮጵያውያን መጋጨት እንደሌለባቸው አበክሮ ይጠይቃል።
 
በሳምንቱ ሌላኛው መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው የኢትዮ ቴሌኮም መግለጫ ነው።  ኢትዮ ቴሌኮም ቀደም ሲል በሰጠው መግለጫ በሲም ካርድ የሚሠሩ የቴሌኮም መገልገያ መሣሪያዎች ካልተመዘገቡ ከኔትወርክ ውጭ ተደርገው ከመስከረም 8 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት መስጠት እንደማይችሉ ገልጦ ነበር። ይህ የኢትዮ ቴሌኮም መግለጫ በብዙዎች ዘንድ የተለያዩ ጥያቄዎችን አጭሯል።

Äthiopien Addis Abeba Universität Kommunikation Internetsperre
ምስል DW/J. Jeffrey

ገሚሱ መግለጫው የወጣው ሕገወጥነትን ለማስወገድ ነው፤ ከእንግዲህ ስልኮችን የሚሰርቁ ስለሚታወቁ ጥሩ ነው ሲሉ መግለጫውን ደግፈዋል። ገሚሱ ደግሞ የለም ይህ መግለጫ የወጣው ቀድሞም ያለአግባብ ሲበዘብዘን የከረመው ኢትዮ ቴሌኮም ለተጨማሪ ብዝበዛ ሲያመቻቸን ነው ሲሉ ተደምጠዋል። ጉዳዩ ሌላ ነው ሁለነገራችንን ለመቆጣጠር ነው ያሉም አሉ። 

«እነሱ ሀብት ሳያስመዘግቡ እኛን ቀፎ አስመዝግቡ ይሉናል» ኤርሚ ፍሪደም ኢትዮ የሰጠው አጭር አስተያየት ነው። «ደረጃ ያልጠበቁ ስልኮች ሲሸጥ የት ነበር» የአደሬ ደሞ ሌላ እጥር ምጥን ያለ አስተያየት። ሔስ ሰርት በበኩሉ፦ «በሌብነት የዘቀጠው ባለሥልጣን እያለ የእርሱ ንብረት ምንም ሳይባል የኔ ተራ ቀፎ ትመዝገብ ማለት ...እህህህህ» ሲል አማሯል። 

«የተሰጠው ምከንያት ውሽት ነው ትክክለኛው የህዝቡን የቀን በቀን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ነው። ልክ እንደ ሰሜን ኮሪያ» ያለው ደግሞ ሳሚ ታደሰ ነው። አብዱልሃኪም አል ሐበሺ ከሳሚ ጋር ተቀራራቢ አስተያየት አስፍሯል እንዲህ ሲል፦ «በቅርቡ ከአሜሪካን በመጡ የእሥማርት ዲቫይሶች ስለላ አሰልጣኞች አማካኝነት ሥልጠና ወስደው ነባርና ነው ።በቃ ይህንን እየተገበሩ ነው» ብሏል። ብሩክ አስፋው ደግሞ፦ «ይህ ዘዴ ኢሞ ዋትሳፕ የመሳሰሉትን ከማሳጣቱ በተጨማሪ ብዙ ገንዘብ ወጥቶ የተገዙትን ሞባይሎች ከጥቅም ውጭ አድርጓል፡፡ ሕጋዊ ዝርፊያ ነው» ብሏል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ


 

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi ዜና አዘጋጅ፤ መርኃ ግብር መሪ፤ የሳምንታዊ ስፖርት አዘጋጅ ነው፥ በአጭር ፊልም የበርካታ ዓለም አቀፍ ተሸላሚው ማንተጋፍቶት የቪዲዮ ዘገባዎችንም ያዘጋጃል።@manti