1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችየመካከለኛው ምሥራቅ

እውን ሀማስን ሙሉ በሙሉ «ማጥፋት» ይቻላል?

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 4 2016

የእስራኤል መንግሥት በግልፅ ተናግሯል። የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርን ጨምሮ በርካታ የመንግስሥት ከፍተኛ አመራሮች ሃማስ የተባለውን ቡድን «እናጠፋለን» ብለዋል። በአንዳንድ የእስራኤል የቴሌቭዥን ጣቢያዎች «በጋራ እናሸንፋለን» የሚሉ መፈክሮች በየጊዜው ይታያሉ። ግን በእውነቱ ሃማስን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ እና «ማሸነፍ» ይቻል ይሆን?

https://p.dw.com/p/4a6oD
በጦርነት የወደመ ቦታ የእስራኤል ወታደሮች
እስራኤል ሃማስን ለማጥፋት ዝታለች።ምስል Toshiyuki Fukushima/Yomiuri Shimbun/AP Photo/picture alliance

እውን ሀማስን ሙሉ በሙሉ «ማጥፋት» ይቻላል?

የሀማስ ታጣዊዎች መስከረም 26 ቀን 2016 በእስራኤል ላይ ጥቃት ከሰነዘሩ ጊዜ አንስቶ እስራኤል የሁለት ሚሊዮን ፍልስጤማውያን መኖርያ የሆነው የጋዛ ሰርጥ ላይ የአየር ጥቃት እያደረሰች ነው። በጀርመን፣ በአውሮፓ ሕብረት፣ በአሜሪካ እና በሌሎች ሃገራትም በአሸባሪነት የተፈረጀው ሃማስ ጋር የእስራኤል መንግሥት የሚያደርገው የምድር ውግያ ወደ ጋዛ የምግብ፣ ውሃ እና የኃይል አቅርቦት እንዳይደርስ አደናቅፏል። 
ይኽ በእንዲህ እንዳለ፤ ሃማስን ጨርሶ ለማስወገድ እንደማይቻል የሚናገሩት አብዛኞቹ ተንታኞች፤ ዋናው ምክንያት ሃማስ ከታጣቂ ድርጅት በላይ በመሆኑ እንደሆነ ይናገራሉ። «እስራኤል ሀማስን በጦር ውጊያ ለማሸነፍ የወሰደችው ርምጃ ትርጉም የለሽ ነው። ወታደሩ የተቻለውን ያህል ሊታገል ይችላል። አመራሩን ሊያስወግድ፣ የሚሳኤል ማስወንጨፊያ ቦታዎችን ሊያወድም ይችላል ነገር ግን የሃማስን ርዕዮተ ዓለም ሊያስወግድ አይችልም።" ይላሉ ሲቢሊን የተሰኘ ዓለም አቀፍ ስለላ እና የአደጋ ስጋት ትንተና የሚያደርገው ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት አማካሪ ጀስቲን ክሩምፕ።  
በጀርመን አለም አቀፍ እና የደህንነት ጉዳዮች ተቋም የመካከለኛው ምሥራቅ አማካሪ የሆኑት ሌላው ተንታኝ ጊዶ እሽታይንበርግ በቅርቡ ለዶይቸ ቬለ እንደገለፁት፣ አብዛኞቹን የሀማስ ተዋጊዎችን ማጥፋት ቢቻልም ቡድኑን ግን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ የማይሳካ ነው። 


« ጦርነቱ ካበቃ በኋላ እስራኤልን ጨርሶ መዋጋት እንዳይችል አድርጎ ማስወገድ በእኔ እምነት የማይቻል ነው። ምክንያቱም ሃማስ ማለት  ከ20,000 እስከ 30,000 የሚገመቱ ተዋጊዎች ያሉት ቡድን ብቻ ሳይሆን በጋዛ ሰርጥ ብዙ ደጋፊዎች ያሉት ማኅበራዊ ንቅናቄ ነው። ስለሆነም ጦርነቱ ካበቃ በኋላም ያለው የወደፊት ችግር ይህ ነው።»
ከጎርጎሮሳዊው 2007 አንስቶ የጋዛ ሰርጥ በሃማስ ቁጥጥር ስር ይገኛል የሚሉት የፖለቲካ ተንታኝ  እሽታይንበርግ ይህም «ዳዋህ» በመባል የሚታወቅ የማኅበራዊ ንቅናቄ እንደወለደ ያስረዳሉ። ይህ የሲቪል ስብስብም ከ80,000 እስከ 90,000 አባላት አሉት ተብሎ ይታመናል ሲሉ ሽታይንበርግ አክለው ለዶይቸ ቬለ አስረድተዋል።
ዳዋህ ማለት «ጥሪ» ወይም «ግብዣ» እንደማለት ሲሆን ይህም አንድ አይነት አመለካከት ወይም ሀሳብ ካላቸው ሰዎች ጋር ማኅበራዊ ትስስር እንዲኖራቸው መጋበዝ ወይም መጥራት እንደሆነ ኦክስፎርድ ዲክሽነሪ ኦፍ ኢስላም ያስረዳል።

የቆሰለ ሰው የያዙ ሰዎች ጋዛ ውስጥ
በጋዛ በሲቪል ዜጎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት እየጨመረ በመምጣቱ እስራኤል ግቦቿን በተሻለ መልኩ እንድትገልጽ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጫና ውስጥ ገብታለችምስል Mohammed Dahman/AP Photo/picture alliance

ሀማስን በውጊያ የማሸነፍ የእስራኤል አቅም

እስራኤል በዓለም ላይ ጠንካራ ጦር ካላቸው ሃገራት አንዷ ናት። የሃገራትን የጦር ኃይል አቅም በሚመዝነው ግሎባል ፋየርፓወር ዓመታዊ መዘርዝር መሰረትም እስራኤል ከ145 ሃገራት 18ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ለንፅፅር ጀርመን 25ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። የስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ተቋም እንደሚለው ባለፈው ዓመት እስራኤል 4.5 በመቶ የሚሆን የሀገር ውስጥ ገቢዋን ለመከላከያ ወጪ አውላለች። ይህ ከዩናይትድ ስቴትስ ወይም ከጀርመን የበለጠ ነው። ሁለቱ ሃገራት እንደ ቅደም ተከተላቸው 3.5 እና 1.4 በመቶ ወጪ ማድረጋቸው ተመዝግቧል።

ስለዚህ እስራኤል ሃማስን ለመዋጋት እና መሪዎቹን ለማደን የሚያስችል አቅም አላት። ቁጥሩን በገለልተኛ ወገን ባይረጋገጥም የእስራኤል መንግሥት በቅርቡ ይፋ እንዳደረገው ከ5,000 እስከ 7,000 የሚደርሱ የሃማስ ተዋጊዎችን ገድያለሁ ብሏል።

ሽምቅ ተዋጊ ድርጅቶችን ለማሸነፍ ያለው ፈተና


በተመሳሳይ ጊዜ ከዚህ ቀደም ከሽምቅ ተዋጊ ድርጅቶች ጋር የተደረጉ ውጊያዎች ቀላል እንዳልነበሩ ማሳያ ምሳሌዎች አሉ።  ለአብነት ያህል ዩናይትድ ስቴትስ በአፍጋኒስታን ከሚገኘው ታሊባን ቡድን እና ኢራቅ ውስጥ ካሉ አማፂ ቡድኖችን  ለመዋጋት ያደረገችውን ጥረት ማንሳት ይቻላል። በርግጥ በአንዳንድ ሁኔታዎች የአማፂ ቡድኑን አቅምን ማዳከም የተቻለ ቢሆንም ቡድኑ እንደገና ፅንፈኛ በሆነ መልኩ ብቅ የሚልበት አጋጣሚ ታይቷል። ለምሳሌነትም ከአልቃይዳ በኋላ የመጣው እና ራሱን «እስላማዊ መንግሥት» የሚለውን ቡድን መጥቀስ ይቻላል።

ዓለም አቀፍ ስለላ እና የአደጋ ስጋት ትንተና የሚያደርገው ሲቢሊን የተሰኘው ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት አማካሪ ጀስቲን ክሩምፕ ጋዛ ውስጥ እየደረሰ ባለው ጥቃት እና በሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ችግር ላይ የወደቁት ነዋሪዎች ገሚሱ በሃማስ ላይ ጥላቻ ሊያድርበት ቢችልም ገሚሱ መደገፉ አይቀርም። በዚህ መሀል በእስራኤል ላይ ቂም የያዙት ወገኖች በሚወስዱት እርምጃ ጥቃቱ ተባብሶ ይቀጥላል ባይ ናቸው።  «አንዳንድ የጋዛ ነዋሪዎች ለሃማስ ጀርባቸውን ቢሰጡም ገሚሱ ሀማስን መደገፍ ይጀምራሉ። በርግጠኝነት እስራኤል የወሰደችው ርምጃ ያበሳጫቸዋል። ስለሆነም ትልቅ ለውጥ ከሌለ በስተቀር ከዚህ ቀደም እንዳየነው አይነት የጥቃት ዑደት ይፈጥራል።»

ካትሪን ሻኤር /ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሠ