1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሕግ እና ፍትሕኢትዮጵያ

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች: እየተባባሰ ስለመጣው የሴት ልጅ ጥቃት ወጣቶች ምን ይላሉ?

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 18 2017

ይህ የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚፈፀም የሴቶች ጥቃት መንስዔና መፍትሄው ላይ ያተኩራል። አብዛኛውን ጊዜ ጥቃቱ ሲፈጸም የአንድ ሰሞን ጉዳይ ሆኖ ይወራል። ከዛ በኋላ ጉዳዩ የት ደረሰ? ተጎጂዎቹ ፍትህ አግኝተዋል ወይ? ብሎ ሲጠየቅ እንብዛም አንሰማም» ሲሉ ሁለት እንግዶቻችን ይተቻሉ።

https://p.dw.com/p/4nyPS
በሀዋሳ ከተማ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆኑት ወጣት ሄለን አማረ እና ወጣት ሶሊያና አያሌው ከዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች ዘጋቢ ሊሻን ዳኜ ጋር
በሀዋሳ ከተማ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆኑት ወጣት ሄለን አማረ እና ወጣት ሶሊያና አያሌው ከዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች ዘጋቢ ሊሻን ዳኜ ጋርምስል S. Wegayehu/DW

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች: እየተባባሰ ስለመጣው የሴት ልጅ ጥቃት ወጣቶች ምን ይላሉ?

በሀዋሳ ከተማ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆኑት ወጣት ሄለን አማረ እና ወጣት ሶሊያና አያሌው በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣው  የሴቶች ጥቃት መንስዔና መፍትሄው ላይ የየራሳቸውን ሀሳብ ሰንዝረዋል ፡፡ ወጣት ሶሊያና ጥቃቱ ሊባባስ የቻለው ሴቶችን ለማክበርና መብታቸውን ለመጠበቅ የሚያስችል የሰለጠነ ማህበረሰብ አለመኖሩ ነው ብላ ታምናለች  ፡፡
ወጣት ሄለን በበኩሏ የሴቶች ጥቃት ሠልጥነዋል በሚባሉት አገራትም የሚስተዋል ችግር መሆኑን በመጥቀስ ጉዳዩ ከሥልጣኔ ጋር ግንኙነት እንደሌለው ትናገራለች  ፡፡ ይልቁንም ሁሉንም ያሳተፈ ጥረት አለመኖሩ ፣ ወንዶች የበላይ ናቸው ብሎ የማመን እንዲሁም ጠንካራ የህግ ቅጣት አለመኖር ለችግሩ መባባስ ምክንያት መሆናቸውን ነው ወጣት ሄለን የገለጸችው ፡፡
ጥቃቱን ለመቀነስ እና ለመከላከል በድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ ፈጣንና በቂ የፍርድ ውሳኔ መስጠት እንደሚገባ የሚጠቁሙት ወጣት ሄለንና ሶሊያና  “ አብዛኛውን ጊዜ ጥቃቱ ሲፈጸም የአንድ ሰሞን ጉዳይ ሆኖ ይወራል ፡፡ ከዛ በኋላ ጉዳዩ የት ደረሰ ? ተጎጂዎቹ ፍትህ አግኝተዋል ወይ ? በድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይስ ምን ፍርድ ተሰጠ ? ብሎ ሲጠየቅ አይሰማም ፡፡ ይህም ጥቃቱ እንዲባባስ ተጨማሪ ምክንያት ሆኖ ይስተዋላል “ ብለዋል ፡፡

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች : የሴት ልጅ አለባበስ ከፆታዊ ጥቃት ያድናል?

የፆታዊ ጥቃት ሰለባዎች
የትግራይ ሴቶች አሶሼትድ ባደረገው ጥናት በአንድ አመት ውስጥ በሴቶች ላይ ከ740 በላይ የሚሆኑ ጾታዊ ጥቃቶች ተመዝግበዋል ምስል Million Hailesilassie/DW


በሴቶች ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ጥቃት ለመከላከል አሁን የተጀመረው ትምህርታዊ ቅስቀሳ እና ግንዛቤን የማስፋት ሥራዎች መጠናከር እንዳለባቸው ወጣቶቹ ይናገራሉ። የቅስቀሳ ዘመቻው ጥሩ ቢሆንም አሁን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እንደሚታየው ከሆነ ግን ጉዳዩ የሴቶች ብቻ ሳይሆን ወንዶችንም ማሳተፍ እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ወጣቶቹ “  ወንዶችን የጥቃት መከላከል ዘመቻው አካል በማድረግ ከማካተትና ከማሳተፍ ይልቅ በጥቅሉ ደፋሪ አድርጎ የመመልከት ንግግሮች በተለይ በአንዳንድ ራሳቸውን ፌሚኒስት ነን ብለው በሚጠሩ ቡድኖች በስፋት እየተስተዋለ እንደሚገኙም ይጠቅሳሉ  ፡፡ ይህም ወንዶች ላይ መጥፎ ሥዕል እንዲኖር የሚያደርግ ነው። ወንድ አባትም፣ ወንድምም ልጅም ነው። ወንዶችን  ከሴቶች እኩል ከጎናችን በማሰለፍ ከተጠቂዎች ጎን እንዲቆሙ በማድረግ ጥቃት አድራሽ የሆኑ ወንዶችን ማውገዝና ለፍትህ ማቅረብ ይገባል “  ብለዋል ፡፡

#ዝምታሰባሪአዳጊሴቶች #GirlzOffMute

ሊሻን ዳኜ / ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ልደት አበበ