የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የ30 ዓመታት ጉዞ
ሐሙስ፣ መጋቢት 26 2016
ትናንት መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም. በኦሮሞ ባህል ማዕከል የተከፈተው አውደ ርዕይ እስከ ነገ መጋቢት 27 ቀን 2016 ኣ.ም. የሚቀጥል የሦስት ቀናት አውደ ርዕይ ነው። አውደ ርዕዩ በ30 ዓመታት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የተሰሩ ሥራዎችን ለማሳየትና ለመዘከር የታሰበ መሆኑ ተገልጿል።
የ30 ዓመታት ጉዞ አውደ ርዕይ ውጥን
በመክፈቻው መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ሰኣዳ አብዱራሃማን የክልሉ መንግሥት ማኅበረሰቡ ያለውን እምቅ እሴት በመመለስ የሁሉም ተሳትፎ ያለበት ልማት ተደራሽ እንዲሆን እንደሚሠራ ጠቁመዋል። በዚህም የሚነሱ ህዝባዊ ጥያቄዎችን በመመለስ በቂ መሰረተ ልማት ያለው ህዝብ ለመፍጠር መንግሥታቸው ተፈጥሮአዊና ሰው ሠራሽ ፈተናዎችን እየተሻገረ መሆኑን አመልክተው የሚታይ ያሉት ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። «የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከምስረታው ጀምሮ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች እየተሻገረ ነው ዛሬ የደረሰው። ለዚህም ለድል የሚያበቃ የፖለቲካ ስልት መጠቀም ግድ ነበርና በዚያው ነው ወደ አዲስ ምዕራፍ መምጣት የተቻለው። ባለፉት አምስት ዓመታትም የነበርንበትን ስኬቶች እና ፈተና መነሻ በማድረግ የህዝባዊ ትግሉ ዓላማን ከግብ ለማድረስ በቁርጠኝነት እየሠራን ነው፡፡ በመሆኑም በደም የተገኘውን ድል በላብ ለመደገፍ የብልጽግና ጉዞ እቅድ አውጥተን በፍጥነት እየሠራን እንገኛለን» ነው ያሉት። በአውደ ርዕዩ ላይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ቢሮዎች እና ተቋማት ምርቶቻቸውን አሰናድተው ለእይታ አቅርበዋል።
ያልተመለሱ የተባሉ የዓመታት ጥያቄዎች
ይህ የክልሉ መንግሥት የ30 ዓመታት ጉዞ በሚል ተሰናድቶ ለእይታ የቀረበውም በክልሉ አሁንም ሰፋፊ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ጥያቄዎች አነሱት የተባለው ግጭት መደምደሚያ ባላገኘበት ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ በሆነው የኦሮሞፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) በአመራርነት የሚሰሩት ፖለቲከኛ ሙላቱ ገመቹ በ30 ዓመቱ የክልሉ ጉዞ የተመለሱ የኦሮሞ ጥያቄ ቢኖሩም እስካሁንም ያልተመለሱ በርከት ይላሉ ብለዋል። የአዲስ አበባ በኦሮሚያ ስር የመተዳደር እና ነጻና ገለልተኛ ምርጫን አድርጎ ህዝቡ በመረጠው ወገን የመተዳደር ፍላጎት ገና የሚቀረው ነው በሚልም ሃሳባቸውን አብራርተዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በፊናቸው አልተመለሱም ከተባሉ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄዎች አንዱ የኦሮምኛ ቋንቋን የፌዴራል መንግሥት ቋንቋ የማድረግ ሂደቱ የተጀመረ መሆኑን ሲያነሱ ይደመጣል።
ሥዩም ጌቱ
ሸዋዬ ለገሠ
እሸቴ በቀለ