1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያ የቀጠለው የጸጥታ ስጋት

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 19 2016

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አከባቢዎች የጸጥታ ስጋት ቀጥሏል፡፡በክልሉ በነቀምቴ ከተማ አንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲን የአገረ ስብከቱ አገልጋይ በጩቤ ተወግተው መገደላቸው ተሰምቷል፡፡

https://p.dw.com/p/4aiOU
ኦሮሚያ ሀረርጌ
ኦሮሚያ ሀረርጌ መልክአ ምድር በከፊልምስል Seyoum Getu/DW

በኦሮሚያ የቀጠለው የጸጥታ ስጋት


በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አከባቢዎች በሚፈጠሩ የፀጥታ መደፍረሶች አለመረጋጋቱ መቀጠሉ እየተነገረ ነው፡፡ከትናንት በስቲያ እሮብ ሌሊት . ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው የቱሉ ቦሎ ከተማ አቅራቢያዋ አዋሽ ቡኔ በምትባል ስፍራ የታጠቁ አካላት ጥቃት ከፍተው ስድስት ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸው ተነግሯል፡፡በእለቱ የተከሰተውን የተሽርካሪዎች ቃጠሎ ተከትሎ ወደ ደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ አከባቢ የሚወስደው አውራ መንገድ ላይ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴም ተስተጓጉሎ እንደነበር ተነግሯል፡፡በሌላ በኩል ትናንት ጠዋት በምስራቅ ወለጋ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ነቀምቴ ከተማ አንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲን የአገረ ስብከቱ አገልጋይ ማንነታቸው ለጊዜው አልታወቀም በተባሉ ሰዎች በጩቤ ተወግተው መገደላቸው ተሰምቷል፡፡

በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን መንገደኞችን ያስተጓጎለው የተሸከርካሪዎች ቃጠሎ


ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን እንዳንጠቅስ ጠይቀው አስተያየታቸውን የሰጡን የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በቾ ወረዳ ነዋሪ በወረዳው አዋሽ ቡኔ በምትባል ስፍራ ከትናንት በስቲያ እሮብ ከሌሊቱ አራት ሰዓት ገደማ ጀምሮ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በተከፈተ ጥቃት ቢያንስ ስድስት ተሽከርካሪዎች ተቃጥለው ሌሎች ላይ የተለያዩ ጉዳቶች ደርሷል ብለዋል፡፡
አስተያየት ሰጪው አስቀድሞም በአከባቢው ተደጋግሞ በሚፈጠር የጸጥታ ስጋቶች እንደነበሩ አመልክተው በእለቱ የተፈጠረው ክስተት ግን በመንገደኞች እንቅስቀሴ ላይም አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩን ጠቅሰዋል፡፡ “በጥቃቱ ብዙ መኪና ተጎድቷል፡፡ መንገድ ዘግተውም ነው የሄዱት፡፡ ወደ ስድስት መኪና ተቃጥሎ ሌሎችም ተጎድቷል፡፡ ከዚህ የተነሳ ከትናንት በስቲያ እና ትናንት ከቀን ውጪ እንቅስቃሴም ተገቷል፡፡”

ኦሮሚያ ክልል
በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አከባቢዎች የጸጥታ ስጋት መቀጠሉ እየተነገረ ነው። ምስል Seyoum Getu/DW


ክስተቱ በአከባቢው ያጠላው የጸጥታ ስጋት
አስተያየት ሰጪው የከባቢ ነዋሪ በስጋቱ የተነሳ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴም መቀነሱን አስረድተዋል፡፡ በሌሊት ደግሞ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች በዚህ ሁለት ቀናት ሙሉ በሙሉ መገታቱን አስረድተዋል፡፡ “አረ በጣም ቀንሷል አንቅስቃሴው፡፡ ከርቀት እንደ ጅማ ካሉ አከባቢዎች የሚመጣ እነጂ እዚህ አከባቢ በተሌም የህዝብ መኪና እንቅስቃሴ ቀንሷል፡፡ የተቃጠሉ መኪኖችም እስካሁን ዳር ዳር አውትተውአቸው በዚያው አሉ፡፡”
አስተያየት ሰጪ የአከባቢው ነዋሪ አክለውም እስካሁንም የተረጋጋ የጸጥታ ሁኔታ በአከባቢው እንደማይስተዋል አመልክተዋል፡፡ “ዛሬ ራሱ በቀንም ውጊያ ነበር በዚሁ አዋሽ ቡኔ አከባቢ፡፡

እስከ ቀኑ አምስት ሰዓት ድረስ በዚህ ከተማ ላይ ሆነን የተኩስ ድምጽ አልፎ አልፎ እንሰማለን፡፡ የተኩስ ልውውጥ አለ” ብለውናል፡፡
ከአዲስ አበባ ወደ ወሊሶ በሚወስደው መንገድ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ስር 70 ኪ.ም. አከባቢ ርቃ የምትገኘው አዋሽ ቡኔ ከተማ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በወጣው የከተሞች መዋቅር በቱሉ ቦሎ ከተማ ስር ተጠቃላ ነው የምትተዳደረው፡፡
በአከባቢው ደረሰ የተባለውን ይህን የጸጥታ ሁኔታ በተመለከተ በመንስኤና መፍትሄው ላይ የመንግስት ባለስልጣናት አስተያየት ለማካተት የተደረገው ሙከሪያ ለዛሬ አልሰመረም፡፡ ለዞኑ ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አብዶ፣ ለኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ እና ለፌዴራል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ የእጅ ስልካቸው ላይ ደውለን ምላሻቸውን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

ነቀምት ከተማ
ነቀምት ከተማምስል Negasa Desalegn/DW


በነቀምቴ ከተማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አገልጋይ መገደል
በሌላ በኩል ትናንት ጠዋት ሁለት ሰዓት ገደማ በነቀምቴ ከተማ የሚኖሩ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት ነቀምቴ ከተማ አገልጋይ ወደ ቢሮያቸው እያመሩ ሳሉ በጩቤ ተወግተው መገደላቸው ተሰምቷል። ለደህንነታቸው ሲባል ማንነታቸውን እንዳንጠቅስና ድምጻቸውን እንዳንጠቀም ጠይቀው አስተያየተቻው የሰጡን የከተማዋ ነዋሪ፤ መምህር ለማ ፋንታሁን የተባሉ የአገረ ስብከቱ የሂሳብና በጀት ክፍል ኃላፊ የተገደሉት “ማንነታቸው ባልታወቁ” አካላት በጩቤ ተወግተው ነው ብለዋል፡፡

እንደ አስተያየት ሰጪው ጥቃቱ ከደረሰባቸው በኋላ ሕይወታቸውን ለማትረፍ ወደ ነቀምቴ ሪፈራል ሆስፒታል ብወሰዱም ለ3 ሰዓታት የሕክምና እርዳታ ሲደረግላቸው ቆይተው ማዳን ባለመቻሉ ህይወታቸው አልፈዋል።

ስለ ግድያው የተጠየቁት የነቀምት ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ሻሎ ገለታ ግድያው መፈጸሙን ለዶይቼ ቬለ አረጋግተው በግድያው የተጠረጠሩ በቁትጥር ስር መዋላቸውናን ጉዳዩ የምርመራ ሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ “አሁን ግድያው ከፖለቲካ ግድያ ጋር ይያያዝ አይያያዝ የታወቀ ነገር የለም፡፡ ተወግተው ነው የተገደሉት፡፡ አሁን ወንጀሉን እየመረመርን ስለሆነ አንድ ሁለት ቀናት ብትታገሱን፡፡ አሁን ይህ ነው ማለት አልችልም በምርመራ እስክንለይ ድረስ፡፡ በዚሁ ሰበብ በቁጥጥር ስር የዋሉም አሉ” ነው ያሉት፡፡

መምህር ለማ ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት ነበሩ ተብሏል። በነቀምቴ ከተማ ፖለቲከኞችን ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት በግለሰቦች ላይ የተፈጸሙ ግድያዎች ከዚህ በፊትም መዘገባቸው ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት እና በኦሮሚያ መንግስትን የሚወጋው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ ራሱን የሚጠራውና መንግስት ሸነ ያለው ታጣቂ ቡድን መካከል በቅርቡ ታንዛንያ ውስጥ የተደረገው ሰላማዊ ስምምነት መክሸፉን ተከትሎ በክልሉ ሰፋፊ ወታደራዊ ፊልሚያዎች መቀጠላቸው በሁለቱም ወገኖች ተደጋግሞ ይነገራል፡፡

ሥዩም ጌቴ
ፀሀይ ጫኔ
ሂሩት መለሠ