1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኦፌኮ በዘንድሮው ምርጫ አይወዳደርም

ረቡዕ፣ የካቲት 24 2013

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦ.ፌ.ኮ) በዘንድሮው 6ኛ ብሔራዊ ምርጫ እንደማይሳተፍ ውሳኔ ላይ መድረሱን አሳወቀ። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እስከ ነገ በተራዘመው የእጩዎች ምዝገባ መርሃ-ግብር ላይም እስካሁን አንድም እጩ አለማስመገቡንም አመልክቷል።

https://p.dw.com/p/3qAFl
Äthiopien Oromo Federalist Congress
ምስል Seyoum Getu/DW

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦ.ፌ.ኮ) በዘንድሮው 6ኛ ብሔራዊ ምርጫ እንደማይሳተፍ ውሳኔ ላይ መድረሱን አሳወቀ። የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ ለዶይቼ ቬለ እንዳረጋገጡት ኦፌኮ በምርጫው ላለመሳተፍ የወሰነው ምርጫውን የሚያስተባብሩ አባላቱ እስር ላይ በመሆናቸውና በርካታ ጽሕፈት ቤቶቹ በመዘጋታቸው ነው። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እስከ ነገ በተራዘመው የእጩዎች ምዝገባ መርሃ-ግብር ላይ እስካሁን አንድም እጩ አለማስመገቡም ከዚሁ ጋር የሚያያዝ መሆኑን አመልክቷል።

ኦፌኮ የተቋቋመው እንደማንኛውም ፓርቲ ተወዳድሮ የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ መሆኑን ትናንት ባወጣው መግለጫ ያሳወቀው ፓርቲው በኃይል ተዘግቷል ያሏቸው ጽ/ቤቶቹ እንዲከፈቱና የታሰሩ አባሎቹ ተፈትተው፣ የምርጫ መርሐ ግብሩ እንዳስፈላጊነቱ ተሻሽሎና የፖለቲካ ምህዳሩ ለሁሉም ዜጎች ተመቻችቶና ከሁሉም በላይ ደግሞ በተሳካ ብሔራዊ መግባባት የታጀበ እንዲሆን እጠይቃለሁ ብሏል። የኦፌኮ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ እንደሚሉትም ፓርቲያቸው ዜጎች ተስፋ የሚጨብጡባት ሀገር ማየትን አጥብቆ ይመኛል። ለዜጎቿ ሁሉ የምትሆን ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ከሚደረገው ሰላማዊ ትግል ጎን እንደሚቆም የገለጸው ኦፌኮ የተረጋጋች ሀገር እንድትፈጠር የሚሠሩ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ተገቢውን ድጋፍ እንዲሰጡትም ጠይቋል። ስለ ኦፌኮ መግለጫ እና ፓርቲው ለኢትዮጵያ ብሔራዊመ ምርጫ ቦርድ ሲያቀርባቸው የነበሩትን ቅሬታዎች በተመለከተ የቦርዱን አስተያየት ለማካተት ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካም ስዩም ጌቱ ከአዲስ አበባ በላከው ዘገባ ጠቅሷል፡፡

ስዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ