1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከኪረሙ ከተማ 50 ሺሕ ተፈናቃዮች ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን የምሥራቅ ወለጋ ዞን ገለጸ

ሰኞ፣ ግንቦት 12 2016

በኦሮሚያ ክልል ኪረሙ ከተማ የነበሩ 50 ሺሕ ተፈናቃዮች ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን የምሥራቅ ወለጋ ዞን አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳኜ ለቺሳ ለዶይቼ ቬለ ተናገሩ። ተፈናቃዮቹ ከሁለት ዓመታት በፊት በግጭት ከኪረሙ ቀበሌዎች ወደ ከተማዋ የሸሹ ናቸው። የተመለሱ ተፈናቃዮች የመኖሪያ ቤት እና የሰብአዊ ድጋፍ እጥረት ገጥሟቸዋል።

https://p.dw.com/p/4g4gx
ምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ
የኪረሙ ከተማ ከተለያዩ የወረዳው ቀበሌዎች የተፈናቀሉ ዜጎች መጠለያ ሆና ቆይታለች። ምስል Privat

ከኪረሙ ከተማ 50 ሺሕ ተፈናቃዮች ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን የምሥራቅ ወለጋ ዞን ገለጸ

በምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ ተጠልለው የነበሩ 50ሺ የሚጠጉ ተፈናቃዮችን ወደ ቀድሞ ቀያቸው መመለሱን የዞኑ አደጋ ስጋት ስራ አመራር (ቦሳ ጎኖፋ) ጽህፈት ቤት አስታወቀ። ወደ ቀያቸው የተመለሱ ዜጎች ለ2 ዓመት ያህል 19 ከሚደርሱ የገጠር ቀበሌዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት ተፈናቅለው በወረዳው ከተማ ውስጥ ተጠልለው የነበሩ ናቸው ተብሏ።

የዞኑ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳኜ ላቺሳ በአሁኑ ወቅት በወረዳው በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ የሚገኝ ተፈናቃይ የለም ብለዋል፡፡ ወደ ቤታቸው የተመለሉ ዜጎችም ሰብአዊ ድጋፍ ችግር በስፋት እንዳለ ተናግረዋል፡፡

በወረዳው 50ሺ የሚጠጉ ሰዎች ተመልሰዋል

በ2014 ዓ.ም በኪረሙ በተከሰተው የሠላም እጦት ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው ቆይተዋል፡፡ የምስራቅ ወለጋ ዞን አደጋ ስጋት ስራ አመራር (ቡሳ ጎኖፋ) ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳኜ ላቺሳ ኪረሙ ወረዳን ጨምሮ 16 ከሚደርሱ የዞኑ ወረዳዎች ውስጥ 119ሺ ዜጎች በዚህ ዓመት በመጠለያ እንደነበሩ አብራርተዋል።

“ሠላም ከሌለ ኮርማም ቢታረድ አይጣፍጥም” በምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ የሚገኙ ተፈናቃይ

ከዚህም መካከል ኪረሙ ወረዳ ውስጥ ከሁሉም ወረዳዎች በላይ ብዙ የተፈናቀሉ ሰዎች እንደነበሩ ተናግረዋል። እስከ ባለፈው ሳምንት አርብ ድረስ 50ሺ የሚጠጉ በኪረሙ ወረዳ ከተማ የነበሩ ዜጎች ወደ ቀድሞ ቤታቸው መመለሳቸውን እና ቤታቸው ለወደመባቸው ሰዎች የቤት መስሪያ ቁሳቀስ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

የወለጋ ተፈናቃዮች በአማራ ክልል
በወለጋ በተቀሰቀሱ ግጭቶች በርካታ ተፈናቃዮች ወደ አማራ ክልል ሸሽተዋልምስል Alemnew Mekonnen/DW

“16 በሚደርሱ ወረዳዎች ተጠልለው የነበሩትን ሁሉንም ሰዎች እየመለስን እንገኛለን። በኪረሙ ወደ 50ሺ የሚጠጋ ህዝብ ነው የተፈናለው፣ በአሁኑ ወቅትም ህዝቡን በሁሉም አቅጣጫ ወደ ቤቱ መልሰናል” ያሉት አቶ ዳኜ “ያለው ሁኔታ ወደ መረጋጋት መጥቷል። የሰላም ኮንፈረስን ከህዝቡና ከአጎራባች ከሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጋርም ውይይት እያደረግን ነው፡፡ አሁን እየሰራን ያለነው ህዝቡን እንዴት ወደ ምርት ማስገባት አለብን በሚለው ላይ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

 የወለጋ ተፈናቃዮች ሮሮ

ከኪረሙ ወረዳ ሶምቦ ከሚባል አካባቢ ተፈናቅለው ሁለት ዓመት ያህል በኪረሙ ወረዳ ከተማ ውስጥ የነበሩት ነዋሪ ወደ ቤታቸው መመለሳቸው ገልጸው በአካባቢው በነበረው የጸጥታ ችግር ከገጠራማ አካባቢዎች መኖሪያ ቤቶች በብዛት ወድመው እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

“የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቤታው እየተመለሱ ነው፡፡ ነገር ግን መኖሪያ ቤት እጥረት አለ፡፡ ቤት በብዛት ታቃጥለዋል፡፡ ድጋፍም በቂ አይደለም ሲመጣም በጣም ትንሽ ነው አይዳረስም ህይወት ለማቆየት  ብቻ ነው” ሲሉ ከተመለሱ በኋላ የገጠማቸውን ችግር አብራርተዋል።  

በኦሮሚያ ክልል በታጣቂዎች የተቃጠለ ተሽከርካሪ
በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሱ ፖለቲካዊ ግጭቶች ብርቱ ሰብአዊ እና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ አስከትለዋል። ምስል Private

ሌላ ወደ ቤታቸው የመለሱ ነዋሪም እንደዚሁ የመኖሪያ ቤት ችግር እና ሰብአዊ ድጋፍ ችግር እንዳለ በመግለጽ የእሳቸው መኖሪያ ቤት መቃጠሉን ተናግረዋል። “የሚሰጠው ዕርዳታ አልተደራሰም። ለቤት መስሪያ ቆርቆሮም መስጠት ተጀምሮ ነበር። እሱም አልተዳረሰም ብዙ ቤት ነው የተቃጠለው” ሲሉ ሁለተኛው ተመላሽ ተፈናቃዮች የገጠማቸውን ችግር አብራርተዋል።

 ኪራሙ ወረዳ ሰዎች ተገደሉ፣ ከብቶች ተዘረፉ

ከነዋሪዎች የተነሳው የሰብአዊ ድጋፍ እጥረትን አስመልክቶ የዞኑ ቡሳ ጎኖፍ ኃላፊ አቶ ዳኜ ላቺሳ እንደተናገሩት በዚህ ዓመት ለኪረሙ ወረዳ ብቻ 10ሺ ኩንታል ድጋፍ መቅረቡን ገልጸዋል። “ቢያንስ 10 ሺ ኩንታል ለኪረሙ ቀርቧል። ድጋፉ ሙሉ በሙሉ የተፈናቀሉ ሰዎችን ፍላጎት አሟልቷል የሚል ሀሳብ የለንም ነገር ግን በተቻለ መጠን ከሁሉም ወረዳ በተሻለ መልኩ ለኪረሙ ድጋፍ አድርገናል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። 

ከምስራቅ ወለጋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ተፈናቀለው በዞኑ ውስጥ ተጠልለው ከነበሩት በተጨማሪ ወደ አማራ ክልል ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች ወደ ዞኑ ስቡ ስሬ፣አኖ እና ባኮ የተባሉ አካባቢዎች መመለሳቸውን የዞኑ ቡሳ ጎኖፋ ቢሮ አመልክተዋል።

ነጋሳ ደሳለኝ
እሸቴ በቀለ