1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከጦርነት ጉሰማ እስከ «ለሰላም» እጅ መጨባበጥ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 24 2015

መቶ ሺህዎችን ለህልፈት፤ ለአካል ጉዳት ዳርጎ፣ ሚሊዮኖችን ከቤት ንብረታቸው ያፈናቀለው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የማታ ማታ በተፋላሚ ወገኖች መካከል የሰላም ስምምነት ተደርሶ ያበቃ መስሏል። ከፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ ትናንት የተላለፈው እና የተፋላሚ ወገን ተወካዮችን እጅ ያጨባበጠው ትዕይንት በእርግጥ ለኢትዮጵያውያን እጅን በአፍ ያስጫነ ነበር ።

https://p.dw.com/p/4J1vo
Pretoria | Waffenstillstandsabkommen für Äthiopien
ምስል SIPHIWE SIBEKO/REUTERS

ሁለተኛ ዓመቱን ያስቆጠረው ጦርነት እና የተደረሰው የሰላም ስምምነት

መቶ ሺህዎችን ለህልፈት፤ ለአካል ጉዳት ዳርጎ፣ ሚሊዮኖችን ከቤት ንብረታቸው ያፈናቀለው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የማታ ማታ በተፋላሚ ወገኖች መካከል የሰላም ስምምነት ተደርሶ ያበቃ መስሏል። ከፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ ትናንት ምሽት በቀጥታ ስርጭት የተላለፈው እና የተፋላሚ ወገን ተወካዮችን እጅ ያጨባበጠው ትዕይንት በእርግጥ ለኢትዮጵያውያን እጅን በአፍ ያስጫነ ነበር ። ይህ ሁሉ የሆነው ደግሞ በእልህ ፣ ጥላቻ አልፎም በብቀላ ተሞልቶ ለሸምጋይ ገላጋይ እንዳስቸገረ የቀጠለው ጦርነት ሁለት ዓመታትን ሊደፍን በዋዜማው መሆኑ በእርግጥ የተለየ መገጣጠም ፈጥሯል። ሃይማኖት ተቋማት የሰላም ጥሪ፤ በምዕራብ ኢትዮጵያ የዜጎች ጭፍጨፋ፤ በአማራ ከተሞች የሰዓት እላፊ
ሰላም ጤና ይስጥልን አድማጮቻችን  በዚህ ልዩ ዝግጅታችንም በሁነቶች አይገመቴነት የተሞላውን አስከፊ ጦርነት፤ ግጭት ከመቅስቀሱ ዋዜማ አንስቶ እስከ «ለሰላም መጨባበጥ » የነበሩትን ዋና ዋና ሁነቶችን መለስ ብለን እንቃኛለን ። ታምራት ዲንሳ ነኝ ፤ አብራችሁኝ ቆዩ።
በአፍሪቃ የቅርብ ጊዜ የጦርነት ታሪክ እጅጉን አስከፊው ተብሎ ሊጠቀስ እንደሚችል የሚነገርለት የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በተለይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ/ም  ምሽት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ  በብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው ያደረጉት ንግግር በብዙዎች ዘንድ በሆነ ሰዓት ሊፈነዳ ይችላል ተብሎ በስጋት ይጠበቅ የነበረው ግጭት መቀስቀሱን ያረጋገጠ ነበር። 
« ላለፉት 20 ዓመታት በቀበሮ ምሽግ ውስጥ በመሆን ሀገሬ ፣ ወገኔ ህዝቤ ብሎ በብዙ ሺዎች መሰዋዕትነት ከፍሎ ፤ ቆስሎ ፣ ደምቶ ፣ ደክሞ ሀገሩ እና ህዝቡን የታደገው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዛሬ ምሽት ከመቀሌ ጀምሮ በበርካታ ስፍራዎች በከሃዲ ኃይሎች እና ባደራጁት ኃይል ጥቃት ተፈጽሞበታል። »
ከዚህ ቀድሞ ብሎ ነበር የኢህአዴግ ቃል አቃባይ እና የቀድሞ ታጋይ ሴኮ ቱሬ ጌታቸው በትግራይ ቴሌቪዥን ቀርበው በትግራይ ክልል ላይ የተጋረጠውን ስጋት ለመስበር በሰሜን ዕዝ ላይ እርምጃ መወሰዱን የሚያሳይ አስተያየት የሰጡት።
«የሰሜን ዕዝን ከተባበሩት እጃችንን አናነሳም ካሉት የዕዙ አባላት ጋር በመተባበር እና ሊተባበሩ ፈቃደኛ ያልሆኑትን ደግሞ በኃይል ተልዕኳቸውን እንዳይወጡ በማድረግ የተደረገ እንቅስቃሴ ነው። በጣም ፈጣን የሆነ እርምጃ ነው የተወሰደው በ45 ደቂቃ ውስጥ ዕዙን በሙሉ መቆጣጠር የተቻለበት ነው።  »
ጠቅላይ ሚንትር ዐቢይ በመቀጠል ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ/ም «ክደት ተፈጽሞበታል» ላሉት የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት ጥቃት ምላሽ የሚሆን እርሳቸው «ሕግ ማስከበር» ያሉትን ወታደራዊ ዘመቻ ትዕዛዝ ሰጡ ።ስለ ሰላም ድርድሩ የፖለቲካ ተንታኝ አስተያየት
ጥቅምት 25 ቀን 2013 ምሽት በሰሜን ዕዝ ላይ ተፈጸመ የተባለውን ጥቃት ተከትሎ ጦርነቱ እንደተጀመረ ቢነገርም ፤ ከዚሁ ዕለት በፊትም ቢሆን በፌዴራል መንግስቱ እና በህወሃት መካከል የነበረው ውጥረት በሆነ ጊዜ ላይ ጦርነቱ ሊፈነዳ እንደሚችል አመላካች ነበር።  ጋዜጠኛ ቴድሮስ አስፋው በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በደቡብ አፍሪካ ከሚካሔደው የሰላም ንግግር ምን ይጠብቃሉ?
«ለውጡን የመሩት  አካላቶች ወይም ወደ ፊት የመጡት ሰዎች እና በሌሎቹ በተለይ  ደግሞ ህወሃት በሚመራው አካል መካከል ልዩነት ነው የተፈጠረው ።  ልዩነቱ ምንድነው ባስቀመጥነው አቅጣጫ መሰረት አይደለም ይሄ ለውጥ  እየሄደ ያለው እንዲያውም ካስቀመጥነው አቅጣጫ ውጭ መሄድ ጀምሯል የሚል ቅሬታ ማንሳት ጀመሩ፤ እና ለኔ ጦርነቱ የተጀመረው የዚያን ጊዜ ነው ፤ ይሄንን በንግግር መፍታት እየቻሉ ባለማድረጋቸው። 
በትግራይ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል መምህር የነበረው ጋዜጠኛ ወልደጊዮርጊስ በበኩሉ ጦርነቱ የተቀሰቀሰበትን ጊዜ እና ምክንያት እንዲህ ይገልጻል።
«ብልጽግና ኢህአዴግን ሲያፈርስ  ህወሃት ከእኔ ጋር ካልሆነ ወደሚልንትርክ ውስጥ ገባ ። እንግዲህ በአንድ ሀገር ውስጥ የተለያዩ ፓርቲዎች በጥምረት ስልጣን ይዘው መቆየት ይችላሉ ። ግን እኛጋ ካልሆናችሁ እናጠፋችኋለን የሚል ነገር ተጀመረ በፓርቲ ደረጃ ስናስበው በኢሕአዴግ ውስጥ የነበረውን ግጭት ማለት ነው። »
የሆነ ሆኖ በመነጋገር ልዩነትን ማጥበብ ጊዜው አለፈበት ። የማይቀረው አስከፊ ጊዜም ደረሰ። ጦርነቱ በትግራይ ክልል የተለያዩ ግንባሮች ተጠናክሮ መቀጠሉ በስፋት መዘገብ ቀጠለ። በዚህ መሃል ግን የኤርትራ ወታደሮች በጦርነቱ ተሳታፊ ሆነዋል የሚሉ ክሶች ከትግራይ ኃይሎች በኩል ይቀርብ ጀመረ። የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥታት ግን በቀረበው ክስ ላይ ለወራት ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ አልሰጡም። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ግጭት እንዲቆም የሚያሳስቡ መልዕክቶችን ያስተላልፍ ጀመር።  ጦርነቱ በተጀመረ በሦስተኛው ሳምንት የፌዴራሉ መንግሥት የመቀሌ ከተማን መቆጣጠሩ ተዘገበ። ስለ ደቡብ አፍሪቃው «የሰላም ንግግር» ምን ይታወቃል?
ከዳንሻ እስከ ሁመራ ፤ ከሁመራ እስከ ሽረ አክሱም አድዋ መቀሌ  ፤ ከቆቦ አላማጣ ማይጨው መቀሌ ፤ ከአዲግራት ውቅሮ መቀሌ የሦስቱ ሳምንታት ጦርነት ከመገናኛ ብዙኃን ዘገባ እና ከኢንተርኔት ግንኙነት አለመኖር ጋር ተያይዞ ከሁለቱም ወገኖች ምን ያህል ተዋጊዎች እንዳለቁ ምን ያህል ሰላማዊ ሰዎች እንደተገደሉ በወቅቱ ለማወቅ እጅጉን አዳጋች ነበር።  
ቀን ቀንን እየተካ ሲሄድ ለዓይን የዘገንኑ ለጆሮ የሚከብዱ መረጃዎች ከትግራይ ምድር መውጣት ጀመሩ። ይህንኑ ተከትሎ በሁለቱም ወገኖች ላይ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የጅምላ ግድያን ጨምሮ የሰብአዊ መብት ጥሰት ዘገባዎች ይቀርቡባቸው ጀመረ። ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ/ም ምሽት ከጦርነቱ ጋር ምንም ግንኙነት በሌላቸው ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጭፍጨፋ መፈጸሙን አምንስቲ ኢንተርናሽናል ኅዳር 4 ቀን 2013 ዓ/ም አስታወቀ። አምነስቲ በመግለጫው ምስክሮችን ጠቅሶ የህወሃት ታማኝ ኃይሎች ድርጊቱን ሳይፈጽሙ እንዳልቀሩ አመልክቷል። 
የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል የካቲት 2013 ዓ/ም ባወጣው ሌላ መግለጫ ደግሞ በዚያው በኅዳር ወር በጥንታዊቷ የአክሱም ከተማ የኤርትራ ወታደሮች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች መግደላቸውን አመለከተ። በተመሳሳይ ማህበረዴጎ በተባለች ስፍራ ያልታጠቁ ሰዎችን በጅምላ ሲገደሉ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማኅበራዊ መገናኛው ታየ።
በመቀጥል የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንቶኒ ብሊንከን ትግራይ ውስጥ «የዘር ማጽዳት » እየተከናወነ ነው ፤የሚል ንግግር አደረጉ ። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የበለጠ ጆሮ መስጠት ጀመረ። ግጭት እንዲቆም እና ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጩ የሚወተውቱ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችም በዚያው ልክ ጨመሩ። 
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥታት ፤ የኤርትራ ወታደሮች ትግራይ ውስጥ በጦርነቱ ስለመሳተፋቸው ከመናገር ለወራት ከቆዩ በኋላ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በመጋቢት ወር 2013 ዓ/ም  ለመጀመሪያ ጊዜ ይህንኑ አመላከቱ። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የኤርትራ ወታደሮች ከሰሜን ኢትዮጵያ ለቀው እንዲወጡ መወትወቱን ቀጠለ። 
 
አዲስ ምዕራፍ አይገመቴ ኹነት። በሰኔ ወር 2013 ዓ/ም የተደረገውን አጠቃላይ ምርጫ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ፓርቲ ብልጽግና ማሸነፉ ይፋ ተደረገ። ነገር ግን የምርጫ ውጤት ታውቆ በቀናት ልዩነት የፌዴራል መንግሥቱ « በትግራይ ክልል ለእርሻ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር »በሚል የተናጠል ተኩስ አቁም አድርጎ የትግራይን ክልል ለቆ መውጣቱን አስታወቀ። በእርግጥም ይህ  አልተጠበቀም ነበር። የህወሃት ኃይሎች ከምዕራባዊ የትግራይ ክፍል ውጭ ቀሪውን ክፍል መልሰው በኃይል የበላይነት መቆጣጠራቸውን አስታወቁ። 
መቀሌን የተቆጣጠሩት የህወሃት ኃይሎች፤ ወደ ደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫዎች ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች ወረራ ፈጸሙ ። ጦርነቱ ገፍቶ ሰሜን ሸዋ በመድረሱ አዲስ አበባ በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ልትገባ ነው የሚለው ግምት በጎላበት ወቅት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ጦር ግንባር የመዝመታቸው ዜና ተሰማ ፤ ኅዳር 2014 ዓ/ም ።
በዚሁ ጊዜ ከደቡብ ወሎ እስከ ሰሜን ወሎ ላሊበላ ድረስ ያሉ ከተሞች በድጋሚ በፌዴራሉ መንግሥት የጥምር ኃይሎች ስር ገቡ። የህወሃት ተዋጊዎች በበኩላቸው ታኅሳስ 2014 ዓ/ም የአማራ እና አፋር ክልሎችን ለቀው መውጣታቸውን አስታወቁ። 
መጋቢት 2014 ዓ/ም የፌዴራል መንግሥቱ እና የህወሃት ኃይሎች  «የሰብአዊ እርዳታን ተደራሽ ለማድረግ » በሚል የተናጥል የተኩስ አቁም ማድረጋቸውን አወጁ። ይህ ከፊል ሰላም ግን ለአምስት ወራት ብቻ ነበር መዝለቅ የቻለው ። 
ሌላ የጦርነት ምዕራፍ ፤ ነሐሴ 2014 ዓ/ም በድጋሚ በተቀሰቀሰ ግጭት  የትግራይ ኃይሎች የሰሜን ወሎዋን የቆቦ ከተማ መቆጣጠራቸው ተሰማ። ቀጠለ ፤ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ኃይሎች በጥምረት ጥቃት መክፈታቸውን ህወሃት አስታወቀ። ጦርነቱ አይሎም የፌዴራል መንግሥቱ ጥምር ኃይል የአላማጣ እና ኮረም እና ሽራሮ ከተሞችን ጨምሮ መቆጣጠሩ ተነገረ።  ጥቅምት 8 ቀን 2015 ዓ/ም ። አዲሱ ዉጊያና የዲፕሎማሲዉ ጥረት
ጦርነቱ ቀጥሏል፤ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም በዲፕሎማሲያዊ መንገድም ሆነ በሌላ አማራጭ ውጊያውን ማስቆም አዳጋች ሆኖበታል። የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጉዳይ ብቻ 15 ጊዜ ተሰባስቦ አንዱንም ጊዜ ከስምምነት መድረስ አለመቻሉ ጦርነቱ ምን ያህል በተወሳሰበ ሁኔታ እየተከናወነ እንደነበር አንድ ማሳያ ሊሆን እንደሚችል የሚናገሩ አሉ። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ማሳሰቢያ
እንደዚያም ሆኖ ግን በመሃል አንድ ተስፋ የሚሰጥ ነገር ተፈጠረ። በአፍሪቃ ኅብረት ጥላ ስር ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የሰላም ንግግር ለማድረግ የሚያስችል ፍላጎት ከሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ተሰማ። ጥቅምት 6 ቀን 2015 ዓ/ም። ይህም በሎጀስቲክ ምክንያት በሚል አንዴ ከተሰናከለ በኋላ የማታ ማታ ተፋላሚ ወገኖች ሰላም ለማውረድ ዝግጁነታቸውን በድጋሚ አስታወቁ። 9 ቀናት የፈጀው ዝጉ የሰላም ንግግር በመጨረሻ ተስፋ ሰጭ ውሳኔ ወለደ። የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት ልዑካን ስለሰላም በይፋ ተፈራረሙ። እጅ ለእጅም ተጨባበጡ ። ገና በማለዳው እናት፣ አባቶች፤ የሃይማኖት አባቶች፤  የሀገር ሽማግሌዎች የተማጸኑለት ሰላም አሁን መልስ ያገኘ መሰለ። መብሰሉ ላይቀርም ማገዶ ፈጀ። 
በደቡብ አፍሪቃው የሰላም ስምምነት ሕወሃት በሂደት በቀናት ውስጥ ትጥቅ እንዲፈታ ብሎም ጦሩን ለማዋሃድ ተስማምቷል። የመከላከያ ሠራዊትም ትጥቅ ትግራይን የመቆጣጠር ኃላፊነት ተጥሎበታል። ይህም መሠረታዊ ከሚባሉት የስምምነቱ ውጤቶች አንዱ ነው። ሁለቱም ወገኖች ዋናውን የስምምነት ሰነድ በተፈራረሙበት ወቅት ለተፈጻሚነቱ እንደሚጥሩ አረጋግጠዋል። 
ስምምነቱን ከኢትዮጵያውያን ባሻገር የተለያዩ ሃገራት በደስታ ተቀብለውታል። የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን «በኢትዮጵያ የፌደራል መንግሥት እና በህወሃት መካከል የመሳሪያ አፈ ሙዝ ዝም በማሰኘት ግጭትን ለማስቆም የደረሱትን ስምምነት በደስታ እንቀበላለን ።» ብለዋል። 
ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ከስምምነት የተሻገረ ተግባራዊ ምላሽ ይሻሉ፤ በሰላም ወጥተው መግባት ዋነኛው ነው። ጥላቻ ፣ ቁርሾ እና በቀልን የሚያስረሳ ሰላም ወርዶ በመላው ኢትዮጵያ የተናፈቀው አዲስ ቀን እንዲመጣም የተደረሰውን ስምምነት ተግባራዊነትን ይጠበቃል። እኔ በዚሁ ላብቃ ቸር ያሰማን። 

Pretoria | Waffenstillstandsabkommen für Äthiopien
በደቡብ አፍሪቃው የሰላም ንግግር ተደራዳሪ ወገኖች እና አሸማጋዮችምስል PHILL MAGAKOE/AFP
Symbolbild Tigray Konflikt
በጦርነቱ ውስጥ ጥቃት የደረሰበት ታንክምስል Tiksa Negeri /REUTERS
USA | UN Sicherheitsrat in New York zur Lage in Äthiopien
የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እየመከረ ምስል Manuel Elias/Xinhua/picture alliance
Maxar Satelittenbilder Grenze Äthiopien Eritrea Aufmarsch Militär
በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ድንበር የወታደራዊ እንቅስቃሴ የሚያሳይ የሳተላይት ምስል ምስል MAXAR/REUTERS
Äthiopien | Premierminister nimmt an Offensive gegen Rebellentruppen Teil
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ግንባር በዘመቱበት ወቅትምስል Ethiopian Prime Minister's Office//AA/picture alliance
Äthiopien | Tigray Soldaten in Mekelle
የህወሃት ኃይሎች የመቀሌ ከተማን መልሰው ሲቆጣጠሩምስል Million Haile Selassie/DW
Äthiopien  | Bürgerkrieg
በጦርነቱ ውስጥ ጥቃት የደረሰበት ወታደራዊ ተሽከርካሪምስል Minasse Wondimu Hailu/AA/picture alliance
Äthiopien | Luftangriffe in Tigray
በጦርነቱ ውስጥ ጥቃት የደረሰበት ሰላማዊ ሰውምስል REUTERS
Wahluhr der regierenden EPRDF auf dem Meskel Square in Addis Abeba
የኢህአዴግ ዓርማ ምስል DW
Äthiopien ehrt seine Polizeikräfte
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድምስል Michael Tewelde/XinHua/dpa/picture alliance

ታምራት ዲንሳ

ሸዋዬ ለገሰ