1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኬንያ፤ የኑሮ ዉድነት ያስነሳዉ ተቃዉሞ

ሰኞ፣ መጋቢት 11 2015

የኬንያ ፖሊስ በሃገሪቱ የሚታየዉን የኑሮ ዉድነት በመቃወም በተጠራ ሰልፍ ቢያንስ አንድ ሰዉ ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት መገደሉ ተሰማ ። ፖሊስ ሰልፉን በአስለቃሽ ጢስ እና ዉኃ በመርጨት በትኗል። ኦዲንጋ የኑሮ ዉድነትና፤ «በተሰረቀ የምርጫ ዉጤት» ስልጣን ላይ የሚገኙትን ፕሬዚዳንት ሩቶን በመቃወም ዜጎች ተቃዉሞዋቸዉን እንዲቀጥሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።

https://p.dw.com/p/4OxEf
Kenia | Anti-Ruto-Proteste in Kisumu
ምስል Musa Naviye/DW

የኬንያ ፖሊስ በሃገሪቱ የሚታየዉን የኑሮ ዉድነት በመቃወም በተጠራ ሰልፍ ቢያንስ አንድ ሰዉ ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት መገደሉ ተሰማ ። ፖሊስ ሰልፉን በአስለቃሽ ጢስ እና ዉኃ በመርጨት በትኗል፤ ከፍተኛ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትንም አስሯል። ዛሬ ሰኞ በታዋቂዉ ተቃዋሚ መሪ ራይላ ኦዲንጋ የተመራዉ የተቃዉሞ ሰልፍ ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ባለፈዉ መስከረም ወር ስልጣን ከያዙ ጀምሮ በሃገሪቱ ጣራ ላይ የደረሰዉን የኑሮ ዉድነት ማስተካከል አልቻሉም ሲል የተጠራ ነበር። በሃገሪቱ በተከሰተዉ ድርቅ እና በመሠረታዊ ነገሮች ላይ በሚታየዉ የዋጋ መናር ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በረሃብ እየተሰቃዩ ነው። ናይሮቢ ላይ ተቃዉሞን የጠሩት የኬንያ የተቃዋሚ መሪ ራይላ ኦዲንጋ በሃገሪቱ «ጣራ የነካዉን » የኑሮ ዉድነትና፤ «በተሰረቀ የምርጫ ዉጤት» ስልጣን ላይ የሚገኙትን ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶን በመቃወም ዜጎች ተቃዉሞዋቸዉን እንዲቀጥሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።  ፖሊስ ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲ የምክር ቤት አባላትን እና አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ከፍተኛ አመራርን ጨምሮ ወደ 20 ወጣት ተቃዋሚ ሰልፈኞችን በቁጥጥር ስር ማድረጉ ተገልጿል። አንድ የኬንያ ተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊ ይህን ተናግረዋል። 
"እየተሰቃየን ነው። ትንሽ የሚባለዉን ስኳር እንኳ ለመግዛት አቅም የለኝም። በአሁኑ ጊዜ ስኳር 40 ሺሊንግ (በግምት 35 ሳንቲም) ሆኗል ። ያለፈዉ መንግስት ቢያንስ ይወደን ነበር ማለት እችላለሁ ። ይህ መንግሥት ግን በግብዞች የተሞላ ነው።  ሩቶ ራሱ እኛን ለማባበል ሃስትለር በሚል ስም ተጠቅሟል ። ሞኞች መስለነዉ ነዉ። አሁን ግን የገባውን ቃል መፈጸም አይችልም።"  
በደቡብ አፍሪቃም በሚታየዉ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ምክንያት ፕሬዚዳንት ሲረል ራማፎሳን ስልጣን እንዲለቁ ሲሉ ተቃዋሚዎች ዛሬ የአደባባይ ተቃዉሞ አሰሙ።   በተቃዉሞ ወቅት መንግሥት ቁልፍ የተባሉ የመሠረተ ልማት ተቋማትን ለመጠበቅ ወታደሮችን መድቧል። የምጣኔ ሀብት ነፃነት ታጋዮች ፓርቲ ቃል አቀባይ ሲናዉ ታምቦ አሁን ላለው ችግር ፕሬዝዳንቱን ተጠያቂ ያደርጋሉ። 
«በደቡብ አፍሪቃ የሕዝባችን፤ ሰቆቃ፣ ከፍተኛ ሥራ አጥነት፣ የስልጣን ዘመኑ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ 1.8 ሚሊዮን ሰዎች ሥራ አጥ የሆኑትን ሲሪል ራማፎሳን ስልጣናቸዉን እንዲለቁ እንጠይቃለን።»

አዜብ ታደሰ 

እሸቴ በቀለ