1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወጣት ስራ አጥነት

ዓርብ፣ መጋቢት 18 2012

በሀገሪቱ የስራ አጥነት ችግርን መፍታት የሚለው አጀንዳ አዲስ ሆኖ አያውቅም ፤ እየሰራን ነው የሚለውም እንዲሁ ፡፡ውጤቱ እና ይልቁንም የለውጥ ጉዞው ሲመራበት እና ሲደገፍ የነበረበት ስራው ነው አጠያያቂ ፡፡

https://p.dw.com/p/3a7ot
Afrika junge Männer arbeitslos
ምስል Imago/photothek/T. Imo

ወጣት ስራ አጥነት

በኢትዮጵያ በየዓመቱ ሁለት ሚሊየን በላይ ዕድሜያቸው ለስራ የደረሱና ስራ የሚፈልጉ ወጣቶች ወደ ስራ ገበያው ይመጣሉ ፤ ሀገሪቱ የምትፈጥረው የስራ ዕድል ግን አንድ ሚሊየን ያክል ብቻ መሆኑን - በቅርብ የተቋቋመው የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን መረጃ ይጠቁማል ፡፡ 
በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ሰሞኑን አንድ መድረክ ተካሂዷል ፡፡ በሀገሪቱ የስራ ፈላጊው አሀዝ እና የሚፈጠረው የስራ ዕድል ቁጥሩ አለመጣጣም ፣ ስራውን በባለቤትነት አቀናጅቶ የሚከውን አለመኖር የተከናወነውም የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አለመቻል ተዳምረው የስራ አጥነት ችግር በኢትዮጵያ አሁን የደረሰበት ደረጃ አስከፊ ከአስከፊም በላይ መሆኑ ተመላክቷል ፡፡ ጤና ይስጥልኝ አድማጮች በዕለቱ ዝግጅት ሰሞኑን በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በስራ አጥነት ችግር እና መፍትሄ ዙርያ የተካሄደውን መድረክ መነሻ አድርገን ስለ ጉዳዩ እንዳስሳለን መልካም ቆይታ ፡፡ 
ወ/ሮ አለምፀሀይ ደርሶልኝ በስራ ዕድል ፈጠራ ኮምሽን የአዳዲስ ስራ ዕድሎች እና ፕሮጀክቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በዚህ የውይይተ መድረክ ያቀረቡት መረጃ ነበር፡፡ 
የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ከዩኒቨርሲቲው ኢንደስትሪ ሊንኬጅ እና ኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ጋር በመተባበበር የተዘጋጀው ሀገር አቀፍ መድረክ ከስራ አጥነት ጋር የተያያዙ በርካታ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበውበታል ፤ ከነዚህ መካከል ቀደም ባሉት አመታት በሀገሪቱ የተቋቋሙት ኢንተርፕራይዞች ያሉበትን ደረጃ የተመለከተው ይገኝበታል ፡፡ ጥናቱን ያቀረቡት በዩኒቨርሲው የምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል መመህር የሆኑት ዶ/ር ሞላ አለማየሁ ነበሩ ፡፡ 
በሀገሪቱ የስራ አጥነት ችግርን መፍታት የሚለው አጀንዳ አዲስ ሆኖ አያውቅም ፤ እየሰራን ነው የሚለውም እንዲሁ ፡፡ውጤቱ እና ይልቁንም የለውጥ ጉዞው ሲመራበት እና ሲደገፍ የነበረበት ስራው ነው አጠያያቂ ፡፡ ዶ/ር ሞላ እነዚህ በአንድ ወቅት አጀንዳነት ወደ ስራ ዓለም እንዲገቡ የተደረጉ ኢንተርፕራይዞች በተለያዩ አካላት ሲሰጣቸው የነበረው ስልጠናም ቢሆን ችግር የነበረበት እንደሆን ባቀረቡት ጥናት አመላክተዋል ፡፡ 
እንዲህ ያለ የስልጠና ፍላጎት መለያየት ቢነሳም በኢንተርፕረነርሺፕ ላይ የሚሰጥ ስልጠና ወጣቱ ያሉ ምቹ ሁኔታዎችን መገንዘብ እንዲችል እና እንዲጠቀም ያግዛል ፤ ይህን ለማድረግ ምቹ ሁኔታዎች መፍጠር ያስፈልጋል ያሉት ሌላኛው ጥናት አቅራቢ ዶ/ር ምትኩ ናቸው ፡፡ 
በሀገሪቱ የስራ አጥነት ችግሩ ሰለባ ከሆኑት መካከል በዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶች ይገኙበታል ፡፡በዩኒቨርሲቲው የውይይት መድረክ እንደቀረበው ከአጠቃላይ የስራ አጥነት መጠን ሃያ በመቶ ድርሻውን የሚይዙት አነኝሁ ተመራቂ ተማሪዎች ስራ ላለማግኘት የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም ፤ የስራ ዕድል ፈጠራ ኮምሽን ባቀረበው መረጃ መሰረት ግን ተመራቂ ተማሪዎቹ ወደ ስራ ዓለም ለመግባት ያሉባቸው ክፍተቶች አሉ፡፡ 
አሁን የሚታየው የስራ አጥ ቁጥር በተቀናጀ መልኩ መፍትሄ ካለተበጀለት የሚያስከትለው ነገር አስከፊ ነው የሚሉት ዶ/ር ምትኩ አሁን በስፋት እየታየ ላለው ችግር መፍትሄ ያሉትን እንደሚከተለው አቅርበዋል ፡፡ 
የፌደራሉ የሰራ ፈጠራ ኮምሽን ከተቋቋመ ጊዜ አንስቶ ከሰራቸው ስራዎች ቀዳሚው የሀገሪቱን የስራ አጥነት ችግር እና መፍትሄ እንዴትነትን መነሻ ያደረገ ሀገራዊ የአስር አመት ዕቅድ መዘጋጀቱ ነው ያሉት የኮምሽኑ ሓላፊ ወ/ሮ ዓለምፀሓይ በመገባደድ ላይ ባለው 2012 ዓ.ም ለሶስት ሚሊየን ዜጎች የስራ ዕድል የመፍጠር ዕቅድ ተይዞ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ተሳክቷል ባይ ናቸው ፡፡ 
ኮምሽኑ ዛሬ ጀምሮ እያደረግኩት ነው የሚለው ጥረት በብዙ የተቀናጀ ጥረት ይሳካል የሚል እምነቱ ከፍተኛ ነው ፡፡በየትኛውም ሁቴታ ስራ ማግኘት ፈተና የሆነባቸው ወጣቶች የሚጠብቁት ነገር ብዙ መሆኑ ግን ፈተና ሳይሆን አይቀርም ፡፡በዚህ ዙርያ ያነጋገርኩት ወጣት ተከታዩን አስተያየት ሰቷል ፡፡ 
በዚህ የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ መድረክ መንግስትን ፣ የግሉን ዘርፍ እና ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ በሚመለከታቸው አካላት በተቀናጀ መንገድ ሊሰሩ ይገባል የተባሉ መፍትሔዎች ቀርበዋል ፡፡ በዩኒቨርሲቲ ረገድ ለየት ያሉ ሀሳቦች እና ፈጠራዎች ዳብረው ወደ ስራ ፈጠራ እንዲሽጋገሩ የሚያግዝ ማዕከል በእንግሊዝኛው አጠራር " ቢዝነስ ኢንኩቤሽን ሴንተር " በሀረማያ ዩኒቨርሲቲና አንዳንድ ተቋማት መጀመሩተነስቷል ፡፡ 
በሀገሪቱ የተንሰራፋውን ስራ አጥነት መቅረፍ አዳዲስ አስተሳሰቦችን ስራ ላይ ከማዋል ጀምሮ የፖሊሲ ማሻሻዎችን ጭምር ማድረግ የሚጠይቅ ነው ያሉት የኮምሽኑ ኃላፊ ወ/ሮ ዓለምፀሀይ አዳዲስ የህግ ማዕቀፎችን በስራ ላይ ለማዋል እየተሰራ ነው ብለዋል ፡፡ 
ስራ ፈላጊው እና የስራ ዕድሉ ያለበት አካል ያለብዙ እንግልት በቴክኖሎጂ መረብ የሚገናኙበትን ዘመናዊ አሰራር መተግበርን ጨምሮ አዳዲስ እሳቤዎችን ተጠቅሞ ሰራ ላይ በማዋል ለውጥ ለማምጣት እየሰራሁ ነው ብላል - የስራ ዕድል ፈጠራ ኮምሽን ፡፡ 
በእርግጥ መንግስት በየጊዜው ከመናገር በዘለል የሚፈለገውን እና ወቅቱ የሚጠይቀውን ያክል ውጤት አላመጣበትም የሚባለው የስራ አጥነት ችግርን መቅረፍ ስራ በቀጣይ አዲስ በተቋቋመው የስራ ፈጠራ ኮምሽን እና የሚመለከታቸው አካላት የተቀናጀ ጥረት ይቀረፍ ይሆን ? ስለውጤታማነቱ መላሹ ቀጣዩ ጊዜ ነው ፡፡ 

Junge Menschen in Äthiopien
ምስል picture-alliance/ dpa
Afrika junge Männer arbeitslos
ምስል Imago/photothek/T. Imo

መሳይ ተክሉ

ኂሩት መለሰ