1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉይይት፣ የኢትዮጵያና የሶማሊላንድ ስምምነት፣ ድጋፍ፣ተቃዉሞና ዉግዘቱ

እሑድ፣ ጥር 19 2016

በዓባይ ወንዝ ዉኃ አጠቃቀም ሰበብ ከኢትዮጵያ ጋር የምትወዛገበዉ ግብፅ ደግሞ ለዉጊያም እየተጋበዘች ነዉ።የግብፅ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሳሚሕ ሽኩሪ ኢትዮጵያን «የአካባቢዉ ያለመረጋጋት ምንጭ» በማለት ወንጅለዋታል።የሐገሪቱ ፕሬዝደንት የቀድሞዉ ፊልድ ማርሻል አብዱልፈታሕ አልሲሲ በበኩላቸዉ ሶማሊያና ደሕንነቷ ላደጋ ከተጋለጠ ግብፅ ጣልቃ ለመግባት

https://p.dw.com/p/4bjcC
ስምምነቱ ከፀና ኢትዮጵያ በርበራ አጠገብ 20 ኪሎ ሜትር ወደብ ለ50 ዓመት በሊዝ ትኮናተራለች
የሶማሊላንድ ትልቁ ወደብ-በርበራ።በስምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያ በርበራ አጠገብ 20 ኪሎሜትር ወደብ ትኮናተራለችምስል Yannick Tylle/picture alliance

ዉይይት፣ የኢትዮጵያና የሶማሊላንድ ስምምነት፣ ድጋፍ፣ተቃዉሞና ዉግዘቱ

 

የኢትዮጵያ መንግስት እራሷን የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ ብላ ከምትጠራዉ ነገር ግን ዓለም አቀፍ የሐገረ-መንግስትነት እዉቅና ከሌላት ሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመ ወር ሊደፍን ሳምንት ቀረዉ።ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት እንደተባለዉ ባንድ ወር ጊዜ ዉስጥ ይፀናል።

ስምምነቱ ከፀና ኢትዮጵያ 20 ኪሎሜትር የሚረዝም የሶማሊላንድ የባሕር በርን ለንግድና ለወታደራዊ አገልግሎት ለ50 ዓመት በሊዝ ትኮናተራለች።ሶማሊላንድ ባንፃሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድና ቴሌኮሙኒከሽንን ከመሳሰሉ ኩባንዮች ድርሻ ይኖራላታል።

የሶማሊላንድ ባለስልጣናትና ሌሎች ወገኖች እንደሚሉት ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ የሐገረ-መንግስትነት ዕዉቅና ትሰጣለች።የኢትዮጵያ መንግስት የኮሚኑኬሽን አገልግሎት በእንግሊዝኛ ባሰራጨዉ መግለጫ «የመግባቢያ ስምምነቱ  ሶማሊላንዶች ከሌሎች ሐገራት ሊያገኙት የማይችሉትን ድጋፍና ሽርክና እንዲያገኙ የሚያስችል፣ ለረጅም ጊዜ ጥያቄያቸዉ መልስ የሚሰጥ» በማለት አልፎታል።

ስምምነቱ ከሐገር ዉስጥ «ለምን አሁን?» ከሚል ጥያቄና ጥንቃቄ፣ አንዳዴም ማሳሰቢያ ጋር ድጋፍ ሲያስገኝ ከዉጪ ተቃዉሞ ገጥሞታል።ይሁንና የቀድሞዋ የሶማሊላንድ ቅኝ ገዢ የብሪታንያ ምክር ቤት ባለፈዉ ሳምንት በጉዳዩ ላይ በተነጋገረበት ወቅት አሌክዛንደር ስታፎርድ የተባሉ እንደራሴ ብሪታንያ «የኢትዮጵያን አብነት ተከትላ» ለሶማሊላንድ የሐገረ-መንግስትነት እዉቅና የመስጠት ሒደትን እንድትጀምር አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገዉን ስምምነት በመደገፍ የተደረገ ሰልፍ
የኢትዮጵያ መንግስት ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገዉን ስምምነት በመደገፍ ድሬዳዋ ዉስጥ ከተደረገዉ ሰልፍ በከፊልምስል Mesay Tekelu/DW

ከዚሕ ዉጪ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአዉሮጳ ሕብረት፣ የአፍሪቃ ሕብረት፣ ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያን የመሳሰሉ ማሕበራትና መንግስታት «የሶማሊያን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነትን እንደግፋለን» በማለት ተቃዉሟቸዉን ገልፀዉ፣ በስምምነቱ ምክንያት አፍሪቃ ቀንድ ላይ ተፈጠረ ያሉት ዉጥረት እንዳይባባስ አደራ ብለዋል።

የሶማሊያ ፌደራዊ ሪፐብሊክ መንግስት ባለስልጣናትና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ኢትዮጵያን ከማዉገዝ፣ ባደባባይ ሰልፍ ከማስወገዝ አልፈዉ ሌሎች መንግስታትን በኢትዮጵያ አንፃር ለማሳደም እየተጣጣሩ ነዉ።የኢጋድ መሪዎች በጉዳዩ ላይ ሲነጋገሩ፣ሶማሊያ አባል የሆነችበት የአረብ ሊግ ከኢጋድ ጉባኤ ቀደም ብሎ የኢትዮጵያን ርምጃ አዉግዟል።

በዓባይ ወንዝ ዉኃ አጠቃቀም ሰበብ ከኢትዮጵያ ጋር የምትወዛገበዉ ግብፅ ደግሞ ለዉጊያም እየተጋበዘች ነዉ።የግብፅ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሳሚሕ ሽኩሪ ኢትዮጵያን «የአካባቢዉ ያለመረጋጋት ምንጭ» በማለት ወንጅለዋታል።የሐገሪቱ ፕሬዝደንት የቀድሞዉ ፊልድ ማርሻል አብዱልፈታሕ አልሲሲ በበኩላቸዉ ሶማሊያና ደሕንነቷ ላደጋ ከተጋለጠ ግብፅ ጣልቃ ለመግባት አታመነታም።»በማለት ዝተዋል።

ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የግብፅን ዛቻ አጣጥለዉ ነቅፈዉታል።ግብፅም በሌሎች ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት እንደ ሊቢያ፣ ሱዳንና ጋዛን በመሳሰሉ የቅርብ ጎረቤቶቿ ያለዉን እልቂትና ግጭት ለማስቆም እንድትጥር መክረዋታል።በዛሬዉ ዉይይታችን የዉጥረቱን ደረጃ፣ የጎሉቱን ነጥቦችና መፍትሔያቸዉን ባጫጭሩ እንቃኛለን።

የኢትዮጵያ መንግስት ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገዉን ስምምነት በመደገፍ የተደረገ ሰልፍ
የኢትዮጵያ መንግስት ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገዉን ስምምነት በመደገፍ ድሬዳዋ ዉስጥ ከተደረገዉ ሰልፍ በከፊልምስል Mesay Tekelu/DW

ሶስት እንግዶች አሉን

1.አቶ አብዱረሕማን ሰዒድ-----የአፍሪቃ ቀንድና የመካከለኛዉ ምሥራቅ የፖለቲካተንታኝ

2.Dr. ሲሳይ መንግስቴ------በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰብአዊ መብትና የሕገ መንግስት ፕሮፌሰርና የፖለቲካ ተንታኝ

3. Dr. ኢስማኤል ጎርሴ-----የአፍሪቃ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኝ

 

ነጋሽ መሐመድ