1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ዐሥራ አራቱ ፏፏቴዎች»ን ምን ነካቸው?

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 4 2012

​​​​​​​በምሥራቅ አፍሪቃ በተለይ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ ሰሞኑን የተከሰተውና ሊከሰት ይችላል የተባለው ብርቱ ዝናብ ከሚያስከትለው የጎርፍ አደጋ ባሻገር ድርቅ ይዞ ሊመጣ እንደሚችልም ባለሞያዎች እየተናገሩ ነው።  የጎርፍ መጥለቅለቁ እና ተከትሎት የሚመጣው ድርቅ ሰበቡ ምን ይኾን?

https://p.dw.com/p/3UloK
ምስል picture-alliance/dpa/A. Gebert

የአፍሪቃ ብቻ ጥረት በአንድ እጅ እንደማጨብጨብ ነው

ደቡብ ማዕከላዊ ኬንያ ውስጥ በምትገኘው የቲካ አነስተኛ ከተማ፦ «ዐሥራ አራቱ ፏፏቴዎች» ወደ ጎን ተደርድረው ቁልቁል ሲወረወሩ የሚፈጥሩትን ድምጽ እያጣጣሙ የተፈጥሮ ውበትን ማድነቅ የብዙዎች ምርጫ ነው። እነዚያ አረፋ እየደፈቁ የሚወረወሩ ውብ ፏፏቴዎች ግን ባለፉት ሳምንታት ለረዥም ጊዜያት በወረደው ብርቱ ዝናብ የተነሳ መልካቸው ወደ ቡናማ ደራሽ ጎርፍነት ተቀይሯል።  በሚያጓራው ደራሽ ጎርፍ መሀል ከወንዙ ዳርቻ ተገምሶ በተነጠለ ቁራሽ መሬት ላይ አንድ ወጣት ዓሣ አጥማጅ ነፍሱን ለማዳን ይጣጣራል። የወጣቱ ዕጣ ፈንታ በመጥፎ አልተደመደመም። አንዲት የፖሊስ ነፍስ አድን ሄሊኮፕተር ደርሳ ከጎርፉ መሀል አውጥታዋለች። 

ለሌሎች ግን ርዳታው እጅግ ዘግይቷል። ኬንያ ውስጥ በቅርቡ በተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ በትንሹ 120 ሰዎች ሞተዋል። የምሥራቅ አፍሪቃዊቷ አነስተኛ፣ ሞቃታማ ሀገር ጅቡቲ ውስጥ ደግሞ በኅዳር አጋማሽ በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ የወረደው ዶፍ ዝናብ ላለፉት ኹለት ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ነበር። 250.000 ነዋሪዎች በድንገተኛው ዝናብ ተጠቂ ኾነዋል።  ኡጋንዳ ውስጥም በተለያዩ ቦታዎች ያለማቋረጥ ለረዥም ጊዜ የወረደው ዝናብ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።

ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሰሜን ምዕራብ ግዛት በአጠቃላይ ማለት ይቻላል በጎርፍ ተጥለቅልቋል። በርካታ መኖሪያ ቤቶች፤ ትምህርት ቤቶች፣  አብያተ-ክርስቲያን እና የንግድ መደብሮች በጎርፍ ሙሉ በሙሉ ወድመዋል። የአካባቢው ሚንሥትር ማሪያ ቴሬሳ ቤቴ ጎርፉ ስጋት መደቀኑን ተናግረዋል።

Uganda Überschwemmungen
ምስል picture-alliance/ZumaS. Hayden

«ጎርፉ ውስጥ በተቀየጠ ዐይነ-ምድር የተነሳ ተላላፊ በሽታዎች ሊዛመቱ ይችላሉ። አንዳች ወረርሽኝም ያሰጋናል»  የጀርመን መዲና ቤርሊን አቅራቢያ በምትገኘው ፖስትዳም ከተማ ውስጥ ባለው የከባቢ አየር ተጽዕኖ ጥናት ተቋም የምሥራቅ አፍሪቃ ጉዳዮች ባለሞያ የኾኑት ኪራ ቪንከ፦ «የተከሰተው ያልተለመደ አይነት የአየር ጠባይ ሳይኾን፤ ብርቱ የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው ነው ባይ ናቸው።

«ነገሩ እንዲህ ነው፤ በቃ አየሩ ይሞቃል። ሞቃታማ አየር ደግሞ ብዙ ርጥበት እና ብዙ ዝናብ መያዙ አይቀርም። ያ ማለት ደግሞ፦ ብርቱ ዶፍ ያስከትላል ማለት ነው።   ምሥራቅ አፍሪቃ ውስጥ የተከሰተው  እንዲህ ያለ ነገር ነው። በምሥራቅ አፍሪቃ በአጠቃላይ ብርቱው ዝናብ እየጨመረ መምጣቱ የሚጠበቅ  ነው።»

የአየ ንብረቱ ተቀይሮ ሙቀቱ በጨመረ ቁጥር የጎርፍ መጥለቅለቁ ይቀጥላል። የጎርፍ መጥለቅለቁን ተከትሎ የተራዘመ ድርቅም ያሰጋል።  በምሥራቅ አፍሪቃ የሶማሊያ፤ ኬንያ እና ኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች አኹን የሚታየውም የአየር መዛባቱ ውጤት ነው።

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ አካባቢዎች የመኸር ሰብል በመሰብሰብ ላይ የሚገኙ ገበሬዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ከሚያስከትለዉ አደጋ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የብሔራዊ ሜትዮሮሎጂ ኤጀንሲ ሰሞኑን እያስጠነቀቀ ነው። የብሔራዊ ሜትዮሮሎጂ ኤጀንሲ የሚትሮሎጂ ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ኃላፊ ወ/ሮ ጫሊ ደበሌ ወቅቱን ካልጠበቀው ዝናብ ስለሚኖረው አሉታዊ ተጽዕኖ ለዶይቼ ቬለ (DW) ቀጣዩን ተናግረው ነበር።

Afrika Weizen Mädchen Ernte
ምስል picture alliance / Gavin Hellier/Robert Harding

«ሰሜናዊ የሀገሪቱ አጋማሽ የምንላቸው [አካባቢዎች] የመኸር እህል በመሰብሰብ ላይ ናቸው። የደረቁ ሰብሎች አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖርባቸዋል። ስለዚህ ቶሎ ቶሎ መሰብሰብ እንደሚገባቸው እያመላከትን ነው። እንዲሁም ደግሞ አጭደው ሳይከመር ቁጭ ያደረጉት ካለ እሱም የመበስበስ ኹኔታ ሊያጋጥመው ይችላል። የተከመረውም ደግሞ በደንብ ካልከመሩት ውኃ ሊገባበት ስለሚችል እሱም ችግር ይኖራል። በአውድማ ላይ እየወቁ ላሉትም አሉታዊ ተጽዕኖ ነው የሚኖረው።»

ዓለም አቀፍ ተቋማት እንደሚያስጠነቅቁት ከኾነ በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ የቤት እንስሳት እና ከብቶች በድርቁ በብርቱ ተጎጂዎች ይኾናሉ። የሚራቡ ሰዎች በርክተው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የሚማጸኑ ሊኾኑ ይችላሉ። ኦክስፋም የተሰኘው የርዳታ ድርጅት እንደሚለው ከኾነ፦ በኢትዮጵያ ወቅት እየጠበቀ የሚከሰተው ድርቅ ሰበቡ ይኸው የአየር ንብረት መዛባት ነው።

ኃያል የሚባለው የአየር ንብረት ለውጥ በሚያስከትለው ዳፋ የተነሳ ወትሮም ቀውስ ውስጥ ከነበሩ የአፍሪቃ ሃገራት ስደተኛ መጉረፉ እንደማይቀር የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR) ስጋቱን ከወዲሁ ገልጧል። የአየር ንብረት ለውጡ በዚህ መልኩ የሚቀጥል ከኾነ ከድርቅ እና ረሐቡ ሽሽት ወደፊት የአፍሪቃ ስደተኞች መበራከታቸው ላይቀር ይችላል ብሏል የዓለም አቀፍ ድርጅቱ። ስደተኞቹ መዳረሻቸው የሚያደርጉትም የተሻለ የሚሉት ጎረቤት ሃገርን አለያም አውሮጳን ሊኾን ይችላል። 

በአንዳንድ የአፍሪቃ ሃገራት የከባቢ አየር ለውጥን በተመለከተ የተነደፉ ፕሮጀክቶች አሉ። ለአብነት ያኽል ኢትዮጵያ ውስጥ ደኖችን መልሶ የማልማት እንቅስቃሴ ተጀምሯል። በዚህ ፕሮጀክት መሰረት አራት ቢሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉ ነው የሚነገረው። ምን ያኽሉ ጸድቀው፤ ምን ያኽሉ ላይስ ክትትል ይደረግባቸዋል የሚለው ሌላ ጉዳይ ኾኖ ማለት ነው። በእርግጥ የአየር ንብረት ለውጡን ለመቀነስ የአፍሪቃውያን ትግል ብቻውን የተፈለገውን ያኽል ውጤት ላያመጣ ይችላል። ስለዚህም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል ይላሉ የከባቢ አየር ባለሞያዋ ኪራ ቪንከ።

Deutschland | Kohlekraftwerk Hohenhameln
ምስል picture-alliance/dpa/J. Stratenschulte

«በኢንዱስትሪ የበለጸጉት ሃገራት ወደ ከባቢ አየር የምንለቀውን በካይ ጋዝ የግድ መቀነስ ይኖርብናል»

በአፍሪቃም ኾነ በዓለም ዙሪያ የተሻለ የአየር ንብረት እንዲኖር ዋናው ነገር ኹሉም በያለበት ስለ ከባቢ አየር ያለውን ግንዛቤ ማጎልመስ ነው። የአፍሪቃ ብቻ ጥረት በአንድ እጅ እንደማጨብጨብ ነው።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

 

 

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi ዜና አዘጋጅ፤ መርኃ ግብር መሪ፤ የሳምንታዊ ስፖርት አዘጋጅ ነው፥ በአጭር ፊልም የበርካታ ዓለም አቀፍ ተሸላሚው ማንተጋፍቶት የቪዲዮ ዘገባዎችንም ያዘጋጃል።@manti