1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዕዳ መክፈል ከተሳናቸው ሀገራት ጎራ የተመደበችው ኢትዮጵያ ከቦንድ ባለቤቶች እየተደራደረች ነው

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 17 2016

ፊች ሬቲንግስ ኢትዮጵያ 33 ሚሊዮን ዶላር ወለድ ሳትከፍል መቅረቷ ከተረጋገጠ በኋላ በዓለም ገበያ የተሸጠውን ቦንድ ምድባ ወደ ያልተከፈለ ዝቅ አድርጎታል። መንግሥት እና የኢትዮጵያ ቦንድ ባለቤቶች በወለድ እና ዕዳ አከፋፈል ላይ እየተደራደሩ ነው። የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሁሉም አበዳሪዎች እኩል መስተናገድ አለባቸው በሚል አቋማቸው እንደጸኑ ነው።

https://p.dw.com/p/4ad8G
ፊች ሬቲንግስ
መቀመጫውን በኒው ዮርክ ያደረገው ፊች ሬቲንግስ ኢትዮጵያ 33 ሚሊዮን ዶላር ወለድ ሳትከፍል መቅረቷ ከተረጋገጠ በኋላ በዓለም ገበያ የተሸጠውን ቦንድ ምድባ ወደ "ያልተከፈለ" ዝቅ አድርጎታል።ምስል Michael Gottschalk/photothek.net/picture alliance

ዕዳ መክፈል ከተሳናቸው ሀገራት ጎራ የተመደበችው ኢትዮጵያ ከቦንድ ባለቤቶች እየተደራደረች ነው

ኢትዮጵያ ለቦንድ ባለቤቶች 33 ሚሊዮን ዶላር የወለድ ክፍያ ሳትፈጽም ቀርታ ዕዳ መክፈል ከተሳናቸው ሀገራት ጎራ ብትመደብም ሀገሪቱ ለገባችበት ቅርቃር መፍትሔ ለማበጀት ድርድር እየተደረገ ነው። ታኅሳስ 1 ቀን 2016 መከፈል የነበረበት ወለድ በዩሮ ቦንድ ውል መሠረት የነበረው የ14 ቀናት የእፎይታ ጊዜ አብቅቷል።

ክፍያው ሳይፈጸም ወይም የገንዘብ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት እና የቦንድ ባለቤቶች ከአንዳች ሥምምነት ሳይደርሱ የእፎይታ ጊዜው በማብቃቱ ኢትዮጵያ ከትላንት ማክሰኞ ጀምሮ ዕዳቸውን መክፈል ከተሳናቸው ሀገራት ጎራ ተመድባለች። ኢትዮጵያ ወለድ በቀነ-ገደቡ ሳትከፍል ከቀረች በኋላ በመንግሥት እና በቦንድ ባለቤቶች መካከል የአከፋፈል ሽግሽግ ድርድር እየተደረገ እንደሚገኝ ዩኒቨርሳል ኢንቨስትመንት በተባለ ኩባንያ በኩል የኢትዮጵያ ቦንድ ባለቤት የሆነው ካፒቱሉም አሴት ማኔጅመንት ለዶይቼ ቬለ አረጋግጧል።

መቀመጫውን በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን ያደረገው ካፒቱሉም አሴት ማኔጅመንት ኩባንያ የፈንድ ማኔጀር የሆኑት ቲዎዶር ኪርሽነር የኢትዮጵያ መንግሥት እና የቦንድ ባለቤቶች የየራሳቸውን ምክረ-ሐሳብ እንዳቀረቡ ለዶይቼ ቬለ በኢ-ሜይል በሰጡት ምላሽ ገልጸዋል። “አሁን ባለው ዋጋ ያን ያህል የተራራቁ አይደሉም” ያሉት ኪርሽነር የአከፋፈል ሽግሽግ ላይ የሚደረገው ድርድር ዛምቢያ ካለፈችበት ተመሳሳይ ሒደት በጣም ፈጥኖ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ተስፋቸውን ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።

“33 ሚሊዮን ይቅርና 300 ሚሊዮን የመክፈል አቅም አለን” አቶ አሕመድ ሽዴ

በገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ መሠረት ከጎርጎሮሳዊው 2006 እስከ 2018 ባሉት ዓመታት ብቻ ከቻይና መንግሥት እና የፋይናንስ ተቋማት ኢትዮጵያ 14.83 ቢሊዮን ዶላር ተበድራለች።  የቻይና ብድር ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የውጭ ዕዳ 25 በመቶ ገደማ ድርሻ እንዳለው የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምኅረቱ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ “33 ሚሊዮን [ዶላር] ይቅርና 300 ሚሊዮን [ዶላር] የመክፈል አቅም አለን” ሲሉ መንግሥታቸው ኢትዮጵያ ቦንድ ባለቤቶች ወለድ ያልከፈለው በውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዳልሆነ ተናግረዋል። ምስል Eshete Bekele/DW

በብሔራዊው ባንክ ገዥ ማብራሪያ መሠረት ኢትዮጵያ ካለባት አጠቃላይ የውጭ ዕዳ ከ45 በመቶ በላይ የሚሆነው ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተበደረችው ነው። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ በሸጠችው ቦንድ የተበደረችው አንድ ቢሊዮን ዶላር ሀገሪቱ ካለባት አጠቃላይ ዕዳ ያለው ድርሻ 2 በመቶ ገደማ ነው።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ባለፈው ሣምንት “መክፈል የሚገባንን 2.2 ቢሊዮን ዶላር [ዕዳ] እንዳንከፍል እፎይታ ያገኘንበት ወቅት ላይ ሆነን 33 ሚሊዮን [ዶላር] ይቅርና 300 ሚሊዮን [ዶላር] የመክፈል አቅም አለን” ሲሉ ለብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከፓሪስ ክለብ እና ከቻይና መንግሥት የዕዳ ክፍያ እፎይታ አግኝቷል። በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል የሚደረገው የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ ድርድር በአንጻሩ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ጋር የሚያደርገውን ውይይት ውጤት እየተጠባበቀ ነው።

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ መሠረት ሁሉም አበዳሪዎች ዕኩል ሊስተናገዱ ይገባል የሚል አቋም አላቸው። የባለሥልጣናቱ መከራከሪያ የደሀ ሀገሮችን ዕዳ ለማቃለል ከሦስት ዓመታት በፊት በቡድን 20 ሀገራት የጸደቀ ማዕቀፍ ነው። በማዕቀፉ ከሚሳተፉ አበዳሪዎች የመግባቢያ ሰነድ (MoU) የተፈራረመ ተበዳሪ ሀገር ከሌሎች ኦፊሴላዊ እና የግል አበዳሪዎች ተመሳሳይ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ጥያቄ ማቅረብ ይኖርበታል።

ከኢትዮጵያ ቦንድ ባለቤቶች ጋር ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝ ያረጋገጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ጉዳዩ በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ መርኅ መሠረት መንግሥታቸው ሁሉንም አበዳሪዎች እኩል ለማስተናገድ እየሞከረ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ “መርኅ መገዛት እንዳለባት እና ይኸንንው ተግባራዊ እንደምናደርግ ነግረናቸዋል” ያሉት አቶ አሕመድ “አንዳንዶቹ ተቀብለዋል። አንዳንዶቹ ገና ውይይት ላይ ናቸው” ሲሉ ተደምጠዋል። የገንዘብ ሚኒስትሩ መንግሥታቸው 33 ሚሊዮን ዶላር ወለድ ሳይከፍል የቀረው አበዳሪዎቹን እኩል ለማስተናገድ በሚከተለው መርኅ ሳቢያ “የማዘግየት ጉዳይ እንጂ፤ ያለ መክፈል ጉዳይ እንጂ የdefault ጉዳይ አይደለም” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ ኢትዮጵያ ቦንድ ሸጣ የተበደረችው አንድ ቢሊዮን ዶላር ከሀገሪቱ አጠቃላይ የውጭ ዕዳ ሁለት በመቶ ገደማ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል። ምስል CC BY 2.0/U.S. Institute of Peace

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ ለብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ኢትዮጵያ እንደ ቻይና ከመሰሉ አበዳሪዎቿ እፎይታ ተቀብላ ለዩሮ ቦንድ ባለቤቶች ዕዳ እየከፈለች መዝለቅ እንደማትችል ተናግረዋል።

“በአንድ በኩል ከኦፊሴያል አበዳሪዎች እና ከቻይና አበዳሪዎች የዕዳ ክፍያ እፎይታ አግኝተን ለዩሮ ቦንድ አበዳሪዎች የምንከፍል ከሆነ በአጠቃላይ የዕዳ ሽግሽግ ሥርዓቱን ያናጋዋል” ያሉት አቶ ማሞ “ስለዚህ ሁሉም አበዳሪዎች ዕኩል መታየት አለባቸው” በማለት መንግሥታቸው የሚከተለውን አቋም አብራርተዋል።  

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ እና የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምኅረቱ የሚያቀነቅኑት ሁሉንም አበዳሪዎች ዕኩል የማስተናገድ መርኅ ግን ዛምቢያን አጣብቂኝ ውስጥ የጣለ አካሔድ ነው። ዛምቢያ ዕዳ መክፈል ካቆመች ከሦስት ዓመታት በኋላ ሁሉንም አበዳሪዎቿን ዕኩል የምታስተናግድበት ስልት እስካሁን ማግኘት አልቻለችም።

የዛምቢያ መንግሥት በዓለም አቀፍ ገበያ የሸጠው የ3 ቢሊዮን ዶላር ቦንድ ባለቤት ከሆኑ አበዳሪዎች ጋር ከሥምምነት መድረሱን ያስታወቀው ባለፈው ጥቅምት ወር ነበር። ቻይና እና ጥቂት የፓሪስ ክለብ አበዳሪዎችን ጨምሮ የዛምቢያ ኦፊሴላዊ አበዳሪዎች ግን ሥምምነቱን ባለፈው ወር ውድቅ አድርገውታል።

ሙግታቸው ከዛምቢያ ቦንድ ባለቤቶች ጋር የተፈጸመው እና በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የጸደቀው ሥምምነት ኦፊሴላዊ አበዳሪዎች ለፕሬዝደንት ሐካይንዴ ሒቺሌማ መንግሥት ካቀረቡት የዕዳ እፎይታ ጋር ተመጣጣኝ አይደለም የሚል ነው። የፕሬዝደንት ሒቺሌማ መንግሥት የዛምቢያ ኦፊሴላዊ እና የግል አበዳሪዎች ፊት ለፊት ተገናኝተው የ3 ቢሊዮን ዶላር የአከፋፈል ሽግሽግ ላይ ያላቸውን ልዩነት እንዲፈቱ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።

የዛምቢያ ፕሬዝደንት ሐካይንዴ ሒቼሊማ እና የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኤማኑዌል ማክሮ
ፕሬዝደንት ሐካይንዴ ሒቼሊማ የዛምቢያ የግል እና ኦፊሴላዊ አበዳሪዎች ፊት ለፊት ተገናኝተው በሀገራቸው የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ረገድ የተፈጠረውን ልዩነት እንዲፈቱ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። ምስል Michel Euler/AP Photo/picture alliance

የዛምቢያ ችግር የቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ ደሀ ሀገሮች የበረታባቸውን ብድር ለማቃለል በእርግጥ ኹነኛው ስልት ነወይ የሚል ጥያቄ እንዲነሳ አድርጓል። ለኢትዮጵያም ሆነ ለዛምቢያ ዳጎስ ያለ ብድር በሰጠችው በቻይና እና በኦፊሴል አበዳሪዎች መካከል ያለው ልዩነትም ሒደቱ እንዲጓተት አስተዋጽዖ አበርክቷል።

ሁሉንም አበዳሪዎች ዕኩል የማስተናገድ ፍላጎት ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት የአንድ ቢሊዮን ዶላር ዕዳ እና ወለድ አከፋፈል ላይ ሊደረግ የሚሻውን ሽግሽግ የተመለከተ ምክረ-ሐሳብ ለቦንድ ባለቤቶች አቅርቧል። የገንዘብ ሚኒስቴር 6.625 በመቶ የነበረው የቦንድ ወለድ ወደ 5 በመቶ ዝቅ እንዲል፤ የመጨረሻው አንድ ቢሊዮን ዶላር ብድር ከጎርጎሮሳዊው 2028 እስከ 2033 ባሉት ዓመታት በአምስት ጊዜ ክፍያ እንዲፈጸም የመጀመሪያ ምክረ-ሐሳብ አቅርቦ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።

የኢትዮጵያ ቦንድ ባለቤቶች በወገናቸው የወለድ መጠኑ ባለበት 6.625 በመቶ እንዲቀጥል፤ የመጨረሻው አንድ ቢሊዮን ዶላር ብድር እስከ ጎርጎሮሳዊው 2029 በሁለት ዙር ክፍያ እንዲፈጸም ያቀረቡት ምክረ-ሐሳብ በገንዘብ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ተቀባይነት አላገኘም። የገንዘብ ሚኒስቴር የወለድ መጠኑ 5.5 በመቶ ሆኖ መንግሥት የተበደረው አንድ ቢሊዮን ዶላር እስከ ጎርጎሮሳዊው 2033 ባሉት ዓመታት እንዲከፈል የመጨረሻ ምክረ-ሐሳብ አቅርቧል።

በሁለቱ ወገኖች መካከል ከዚህ ቀደም የተደረጉ ውይይቶች የወለድ መክፈያ ጊዜው እጅግ በተቃረበበት ወቅት የተካሔዱ በመሆናቸው መፍትሔ አላበጁም። የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ የኢትዮጵያ ቦንድ ባለቤቶች የሁለት ዓመታት እፎይታ እንደሌሎች አበዳሪዎች ሊሰጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከግል አበዳሪዎች ቦንድ ሸጦ አንድ ቢሊዮን ዶላር ሲዋስ ገንዘቡ ለኢንዱስትሪ ፓርኮች እና የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ የታቀደ ነበር። የኢንዱስትሪ ፓርኮቹም ይሁኑ በመከላከያ ሚንስቴር ሥር በነበረው የቀድሞው የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ሊገነቡ የታቀዱ የስኳር ፋብሪካዎች ለሀገሪቱ ያተረፉት ዕዳ ብቻ ነው።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ