1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች: በአፍላ እድሜ ላይ ያሉ ሴቶች ለምን ራሳቸውን ያጠፋሉ?

መሳይ ተክሉ
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 11 2017

«በአፍላ እድሜ ላይ ያሉ ሴቶች ለምን ራሳቸውን ያጠፋሉ? » በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የድሬደዋ የዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች ዝግጅት ዘጋቢ ብሌን ድልአርጋቸው ከሁለት ወጣት ሴት ልጆች ጋር ስለ ምክንያት እና መፍትሄ ሊሆኑ በሚችሉ ሀሳቦች ላይ ተወያይታለች። በጉዳዮ ላይ የባለሞያ አስተያየትም ተካቷል።

https://p.dw.com/p/4oBV7
የዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች ዝግጅት ዘጋቢ ብሌን ድልአርጋቸው፤ ከ9ኛ ክፍል ተማሪ  ቅድስት ጋዲሳ እና የ11ኛ ክፍል ተማሪዋ መብሪት ወላይ ጋር
የዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች ዝግጅት ዘጋቢ ብሌን ድልአርጋቸው፤ ከ9ኛ ክፍል ተማሪ ቅድስት ጋዲሳ እና የ11ኛ ክፍል ተማሪዋ መብሪት ወላይ ጋርምስል M. Teklu/DW

አሁን አሁን ድሬደዋን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በአፍላ እድሜ ላይ የሚገኙ ወጣት ሴቶች ራሳቸውን አጠፉ ሲባል ማድመጥ እየተለመደ መጥቷል።  ምክንያቶች እና የድርጊቱን መስፋፋት ለመከላከል መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ የመፍትሄ ሀሳቦች ላይ ከሁለት ወጣት ሴት ልጆች ጋር ውይይት ያደረገችው የድሬደዋ የዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች ዝግጅት ዘጋቢ ብሌን ድልአርጋቸው ናት።

የ9ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ቅድስት ጋዲሳ እና የ11ኛ ክፍል ተማሪዋ መብሪት ወላይ በአፍላ እድሜ ላይ የሚገኙ ወጣት ሴት ልጆች ራሳቸውን እንዲያጠፉ ሊገፋፉ የሚችሉ ምክንያቶች እና መፍትሄውን ትኩረት ባደረገው ውይይት ተሳታፊዎች ናቸው።

ከቤተሰብ ጋር የሚፈጠር አለመግባባት አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል የምትለው ቅድስት ይህንን ተከትሎ አንዳንዶች ራሴን ብቻ አዳምጣለሁ በሚል ሰበብ ከቤት በሚወጡበት ጊዜ እርግዝናን ጨምሮ ሌሎች የሚገጥሟቸው ፈተናዎች ራስ የማጥፋት ውሳኔ እንዲወስኑ ሊያደርግ እንደሚችል ገልፃለች።

ሌላኛዋ የውይይቱ ተሳታፊ መብሪት በትምህርት የሚፈለገው ውጤት ሳይመጣ ሲቀር ወይም በፍቅር ግንኙነት ያሰቡት ዓይነት ምላሽ ሳይገኝ ሲቀር አልያም ከቤተሰብ ጋር የሚፈጠር ግጭት በአፍላ እድሜ ላይ ለሚገኙት ሴት ራስን ማጥፋት መፍትሄ መስሎ ሊታያቸው እንደሚችል ጠቁማለች።

በየትኞቹም ገፊ ምክንያቶች የሚፈፀም ራስን የማጥፋት ድርጊት ዓላማዋን በማጨናገፍ ተጎጂ የሚያደርገው ራሷን ወጣቷን መሆኑን ያነሱት ቅድስት እና መብሪት ስሜታዊ ከመሆን መጠበቅ አስፈላጊ ነው ይላሉ።

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች: በአፍላ እድሜ ላይ ያሉ ሴቶች ለምን ራሳቸውን ያጠፋሉ?

ወላጆች ከልጆች ጋር ቀርቦ በግልፅ መነጋገር ፣ መወያየትን ማዳበር እንዲሁም የጓደኛ አመራረጥ ላይ ትኩረት መስጠት እና ሌሎች ሀሳቦች ጎጂ ከሆነው ራስን የማጥፋት ድርጊት ለመጠበቅ መፍትሄ ሊሆኑ እንደሚችሉ በውይይቱ ተነስቷል ።

በርእሰ ጉዳዩ ላይ ሞያዊ አስተያየት የሰጡን በድልጮራ ሪፈራል ሆስፒታል የስነ ልቦና ህክምና ባለሞያ የሆኑት ዶ/ር ፂሆን አለሙ ራስን የማጥፋት ሙከራ ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ እንደሚበዛ ገልፀዋል። ስለሆነም ዶ/ር ፂሆን ምክንያቱ ማጤን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ራስን ለማጥፋት ዋንኛ መንስኤ ለሆነው ድብርት መፍትሄ መስጠት እንዲሁም ራስን ስለማጥፋት በግልፅ መወያየት እንደሚያስፈልግም አክለው ገልፀዋል። 

#ዝምታሰባሪአዳጊሴቶች #GirlzOffMute


ብሌን ድልአርጋቸው/መሳይ ተክሉ
ልደት አበበ