የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አስቸኳይ ሀገራዊ ጥሪ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 2 2015የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዛሬ ነሐሴ 2 ቀን 2015 ዓ. ም ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ በኢትዮጵያ "የሚታዩ ግጭቶች በአስቸኳይ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ቆመው የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ አሉን የሚሏቸውን ልዩነቶች ወይም ጥያቄዎች በጠረንጴዛ ተቀምጠው በምክክር እንዲፈቱ" ሲል አስቸኳይ ያለውን ሀገራዊ ጥሪ አቅርቧል። ኮሚሽኑ "በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች እየታዩ ያሉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች የኮሚሽኑን ሥራ አዳጋች እያደረጉት ይገኛሉ" ሲል በመግለጫው አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ልዩነቶች እና አለመግባባቶችን በንግግር እና በምክክር መፍታት ሲገባ በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ወገኖች እየተወሰዱ ያሉ ያላቸው የኃይል እርምጃዎች የኢትዮጵያን ደህንነት እና ህልውና በመፈታተን ላይ ይገኛሉ ብሏል።
አለመግባባቶችን በንግግር እና በምክክር መፍታት ሲገባ በተለያዩ የኢትዮጵያ ዳርቻዎች "በተለያዩ ወገኖች" እየተወሰዱ ያሉ ያላቸው የኃይል እርምጃዎች የሀገሪቱን ደህንነት እና ህልውና በመፈታተን ላይ መሆናቸውን ያስታወቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን የተቋቋመበትን ኃላፊነት ለመወጣት በአምስት ክልሎች እና አንድ ከተማ አስተዳደር የተሳታፊዎችን ልየታ እያከናወነ መሆኑን ጠቅሶ ወደ ቀሪ ሰባት ክልሎች እና አንድ ከተማ መስተዳደር በመሄድ አጀንዳ ለመሰብሰብ ዝግጅት ላይ ቢሆንም በሀገሪቱ "እየታዩ ያሉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች" ሥራውን አዳጋች እያደረጉት ይገኛል ብሏል።
የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የቀርበው አስቸኳይ ጥሪ ተግባራዊ እንዲሆን ኮሚሽኑ ባለድርሻ አካላትን በማቀራረብ የልዩነት አጀንዳዎችን ሰብስቦ ለማወያየት እና ለማመካከር አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች የሰላም መታጣት ችግሮች አሉ ያለው ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የኮሚሽኑ ምክር ቤት ነሐሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ልዩ ስብሰባ በመላው ኢትዮጵያ የሚታዩ ግጭቶች በአስቸኳይ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ቆመው ችግሮች በምክክር እንዲፈቱ ድምዳሜ ላይ በመድረሱ መሆኑን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ኂሩት ገብረሥላሴ ገልፀዋል።
የሥራ ኃላፊዎቹ ይህንን ጥሪ አሁን ለምን እንዳቀረቡ ተጠይቀው የቀረበው አስቸኳይ ጥሪ አሁን በአማራ ክልል የተፈጠረው ሰሞነኛው ግጭት ብቻ መነሻ ሆኖት እንዳልሆነ ገልፀዋል። በተለይ ተፋላሚ ኃይላት ለምክክር ጥሪያችሁን ቢቀበሉ ለመነጋገር ቢፈቅዱ ምን ያህል ዋስትና ትሰጣላችሁ ? ተብሎ ለቀረበ ጥያቄም "አስፈላጊው ጥንቃቄ ይወሰዳል" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ግጭቶች እና የሰዎች ሞት እንዲቆም ለዚህኛው ጥሪ ቅድሚያ የመስጠቱን ተገቢነት ኮሚሽኑ እንዳመነበት ያብራሩት ኮሚሽነሮቹ በኦሮሚያ ክልል ተጀምሮ የነበረው ድርድር እንዲቀጥል ፣ በትግራይ ክልል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ተግባራዊነቱ እንዲፋጠን እና አሁን በአማራ ክልል ያለው ችግርም የሚረግብበትን መፍትሔ ለማምጣት ሁኔታዎችን እንደሚያመቻቹ እና "ማነጋገር ያለብንን ሁሉ እናነጋግራለን" ሲሉም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን "አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ አሳሳቢ ነው" ሲልም ለጥሪው አፋጣኝ ምላሽ ከሁሉም ወገን ጠይቋል።
እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ