በድሬደዋ የተካሄደው የሃይማኖት ምክር ቤት ጉባኤ
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 14 2017ማስታወቂያ
በሰላም ጉባኤው የተለያዩ ሃይማኖት መሪዎች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ በድሬደዋ የሚገኙ የተለያዩ እምነት ተከታዮች ተገኝተዋል። ከትናንት በስተያ በድሬደዋ ስታድየም በተካሄደ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ወደ ሰላም የተመለሱትን በማመስገን አሁንም በትጥቅ ትግል ውስጥ ለሚገኙት የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።
«ወደ መደራደር እና እርቀ ሰላም መተው በፍቃዳቸው ወደ ሕዝባችን የተቀላቀሉትን ልጆቻችንን እናመሰግናለን» ያሉት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት ፕሬዝዳንት የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት የበላይ ጠባቂ ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ ለተቀሩት ጥሪ አቅርበዋል።
ሼህ ሀጂ ኢብራሂም መንግሥት በበኩሉ ከጫካ የተመለሱትን እንዲንከባከብና መልሶ ማቋቋሚያ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከድሬደዋ ሃይማኖት ተቋማት ጋር በጋራ ባዘጋጁት በዚህ ጉባኤ የተለያዩ እምነት ተከታዮች የታደሙ ሲሆን የተለያዩ የሃይማኖት መሪዎች የሰላምን አስፈላጊነት የተመለከቱ መልዕክቶች ተላልፈዋል። ጉባኤው በቀጣይ በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች አካሂደዋለው ያለው መሰል ሀገር አቀፍ የሰላም ጉባኤ በኦሮሚያ ክልል እንደሚዘጋጅ ታውቋል።
መሳይ ተክሌ
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ