1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሐሙስ ታኅሣሥ 3 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የዓለም ዜና

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 3 2017

*በቱርክ ፕሬዝዳንት ረቺብ ጣይብ ኤርዶኻን አሸማጋይነት አንካራ ውስጥኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በመካከላቸው የተፈጠረውን ውዝግብ ለለመፍታት «ቴክኒካዊ ውይይት» ለማድረግ መስማማታቸው ተገለጠ ። *ከአንድ ዓመት የእስር ጊዜ በኋላ ባለፈው ሳምንት የተለቀቁት የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደዓ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ከማረሚያ ቤት ውጪ በራሳቸው ፍርድ ቤት ቀረቡ ። *የራስ ገዟ ሶማሊላንድ አዲስ ፕሬዚደንት አብዲራሕማን ሞሐመድ አብዱላሂ ዛሬ ሀርጌሳ ውስጥ ቃለ መሐላ ፈጸሙ ። *ሣዑዲ ዓረቢያ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2034 የዓለም ዋንጫን ለማስተናገድ ተመረጠች ።

https://p.dw.com/p/4o4zD

አንካራ፥ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ «ቴክኒካዊ ውይይት» ለማድረግ  ተስማሙ

በሶማሊላንድ ጉዳይ የተቃቃሩት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ  ቱርክ አንካራ ውስጥ ያደረጉትን ስምምነት «ያለምንም መዘግየት» ተግባራዊ እንዲያደርጉ የአፍሪቃ ኅብረት ዛሬ አሳሰበ ። በቱርክ ፕሬዝዳንት ረቺብ ጣይብ ኤርዶኻን አሸማጋይነት አንካራ ውስጥ የተነጋገሩት ሁለቱ ሃገራት በመካከላቸው የተፈጠረውን ውዝግብ ለለመፍታት «ቴክኒካዊ ውይይት» ለማድረግ መስማማታቸውም ተገልጧል ። የቱርክ ፕሬዝዳንት ኤርዶኻን ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐመድ ትናንት ረቡዕ በተናጠል ከተነጋገሩ በኋላ መግለጫውን ዛሬ የሰጡት ። ለንደን የሚገኙት የአፍሪቃ ቀንድ ጉዳዮች ተንታኝ አቶ አብዱራህማን ሠይድ ስለ ቴክኒካዊው ስምምነት ቀጣዩን ብለዋል ።

«ስምምነቱ በኢትዮጵያ በኩል የሶማሊያ ሉዓላዊ ግዛት ማክበር እንዳለባት ተቀብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ። እናም ይሄ ዋናው መግቢያ ነበር ። ምክንያቱም ይኼን የሶማሊያ ፕሬዚደንት እንደ[ ቅድመ ሁኔታ] ነበር ሲያስቀምጡት የቆዩት ። ምክንያቱም ከሶማሊላንድ ጋር የተደረገው ስምምነት የሶማሊያን ሉዓላዊ ግዛት የማያከብር ነው ሲሉ ነው የቆዩት ባለፈው ዓመት ።»

በጋራ መግለጫው መሠረት ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ቱርክ በመጪው የካቲት ወር ውይይት ለማድረግ ከሥምምነት መድረሳቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል ።

አአ፥ታዬ ደንደኣ ከእስር ውጪ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀረቡ

ከአንድ ዓመት የእስር ጊዜ በኋላ ባለፈው ሳምንት የተለቀቁት የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደዓ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ከማረሚያ ቤት ውጪ በራሳቸው ፍርድ ቤት ቀርበዋል ። አቶ ታዬ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የቀረቡት ፍርድ ቤቱ እንዲከላከሉት የበየነባቸው «ፍቃድ የሌለው የጦር መሣሪያ ይዘው ተገኝተዋል» የሚለውን የክስ ሂደት ለመከላከል ነው ። ፍርድ ቤቱ ቀሪዎቹን ሦስት ምስክሮችን ለመስማት ነበር ለዛሬ የቀጠረው ። ይሁንና ዛሬ ለመከከላከያ ምስክርነት ይመጣሉ ተብለው ከተጠበቁት ሦስት ምስክሮች ማለትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እና የከተማ ልማት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ አንዳቸውም አልቀረቡም ። ችሎቱ ዛሬ ሲሰየም ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ውጪ አገር በመሆናቸው በዛሬው ችሎት ላይ መቅረብ እንዳልቻሉ በጽሑፍ በተላከው ደብዳቤ ከማሳወቃቸው ውጪ ቀሪዎቹ ሁለት ምስክሮች ለምን እንዳልቀረቡ አልተብራራም ። በዚሁ ላይ ሐሳብ ያቀረቡት የአቃቤ ሕግ ተወካይ፤ ቀደም ሲል በእስር ላይ የነበሩት አቶ ታዬ አሁን ከእስር በመለቀቃቸው ለተከላካይ ምስክሮቻቸው በራሳቸው ትእዛዝ እንዲያደርሱ ቢጠይቁም፤ «ምስክሮቹ ከፍተኛ የመንግስት ባላሥልጣናት በመሆናቸው ይህ አይሆንም» በማለት አስተያየቱን ውድቅ ያደረገው ፍርድ ቤቱ ትእዛዙን በድጋሜ እጽፋለሁ በማለት ተለዋጭ የቀጠሮውን ቀን ለየካቲት 6 ቀን» 2017 ዓ.ም ይዟል ሲል ሥዩም ጌቱ ከአዲስ አበባ ዘግቧል ።

ሐርጌሳ፥የራስ ገዟ ሶማሊላንድ አዲስ ፕሬዚደንት ቃለ መሐላ ፈጸሙ

የራስ ገዟ ሶማሊላንድ አዲስ ፕሬዚደንት አብዲራሕማን ሞሐመድ አብዱላሂ ዛሬ ሀርጌሳ ውስጥ ቃለ መሐላ ፈጸሙ ። ምንም እንኳን እስካሁን ዕውቅና ባታገንም ራሷን እንደ ሉዓላዊ ሀገር ቆጥራ የምትንቀሳቀሰው የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ  ፕሬዚደንቷን የመረጠችው በምርጫ ሒደት ነው ። ቃላ መሐላው የተፈጸመው በሶማሊላንድ ጉዳይ የተካረሩት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርክ አሸማጋይነት አንካራ ውስጥ «በቴክኒካዊ ጉዳዮች ለመነጋገር» ከተስማሙ ከአንድ ቀን በኋላ መሆኑን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል ።

ካርቱም፥ የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ሱዳን ጦር መሣሪያ ላከች መባሉን አስተባበለች

የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ለሱዳን የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጦር መሣሪያ ታቀብላለች የሚለውን ውንጀላ አስተባበለች ። በቻድ በኩል ጦር መሣሪያ ታቀብላለች በሚል በተመድ የቀረበውን ክስ የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች  ውድቅ አድርጋለች ። የተመድ ባለሞያዎች ጦርነቱ ሱዳን ውስጥ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ወደ ዐሥር ዙር  የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች የአውሮፕላን ጭነቶች ሱዳን መግባታቸውን ተናግረዋል ። በሱዳን በጦር ሠራዊቱ እና በፈጥኖ ደራሹ ውጊያ በርካቶች ለሞት እና ስደት ተዳርገዋል ።

ደማስቆ፥ የቡድን 7 አገራት  (G7) መሪዎች ለሶሪያ ሽግግር ድጋፍ እንደሚያደርጉ ዐሳወቁ

በሶርያ ሁሉን አካታች ለሆነ ሒደት ድጋፍ እንደሚያደርጉ በኤኮኖሚ የበለጸጉ የቡድን 7 አገራት  (G7) መሪዎች ዐሳወቁ ።  አገራቱ በመግለጫቸውም ሶሪያ ውስጥ «ታማኝ፣ ሁሉን አካታች እና እጅግ ምሥጢራዊ ያልሆነ መንግሥታዊ አገዛዝን ለማስፈን ለሚደረገው የሽግግር ሒደት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን» ብለዋል ።  ጀርመንም ፍላጎቷ ተመሳሳይ መሆኑን መራኄ መንግሥት ዖላፍ ሾልትስ ገልጠዋል ። የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር አንቶኒ ብሊንከን በበኩላቸው በሶሪያ ላለው ሽግግር ድጋፍ ለማድረግ ዛሬ ዮርዳኖስ መግባታቸው ታውቋል ።  አንቶኒ ብሊንከን ሶርያ ውስጥ ስለ በሽር ኧል አሳድ ውድቀት እና የአማጺያን ድል መንስዔውን ተጠይቀው ለጋዜጠኞች ሲመልሱ በርካታ ሰበቦች ቢኖሩም ሁለት ነገሮችን መመልከት ያሻናል ብለዋል ።

«በመጀመሪያ ደረጃ የሶሪያ መንግሥት የውጭ ኹነኛ ደጋፊዎች፦ ሒዝቦላህ፣ ኢራን፣ ሩስያ ቢያንስ ትኩረታቸው ተዛብቷል ራሳቸው በፈጠሩት እንዲሁም እኛም እንዲባባስ ባደረግንባቸው ችግር አንዳንዶቹ ሊፈረካከሱ ደርሰዋል በሁለተኛ ደረጃ፦ አገሪቱን በአንድነት ለማሰባሰብ በሚደረገው ጥረት የአሳድ አገሪቱን እንዲያ መቀመቅ ውስጥ አስገብቶም በማንኛውም አይነት ፖለቲካዊ ውይይት አልሳተፍም የማለቱ ግትርነት ነው ሲመስለኝ ውድቀቱ ብሎ የጀመረበት ነው »

አንቶኒ ብሊንከን ከዮርዳኖስ ንጉሥ አብዱላህ ጋር ዛሬ በሶሪያ ጉዳይ ተነጋግረዋል ። ቱርክ ውስጥም ከመሪዎች ጋር የሚወያዩት አንቶኒ ብሊንከን እንደ የG7 አባል ሃገራት በፖለቲካዊ ሒደቱ ድጋፍ ለማድረግ አገራቸው ዝግጁ መሆኗን ዐሳውቀዋል ።  የG7 አባል ሃገራት የሶሪያ የግዛት አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ አንድነት እንዲጠበቅ ጽኑእ ፍላጎታቸው መሆኑንም ይፋ አድርገዋል ። የG7 አባል ሃገራት ብሪታንያ፣ ካናዳ፣ ፈረንሣይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓን እና ዩናይትድ ስቴትስን ያካትታል ።

ዙሪክ፥ ሣዑዲ ዓረቢያ የ2034 የዓለም ዋንጫን ለማስተናገድ ተመረጠች

ሣዑዲ ዓረቢያ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2034 የዓለም ዋንጫን ለማስተናገድ ተመረጠች ።  ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (FIFA)ብቸኛዋ ተወዳዳሪ ሣዑዲ ዓረቢያ ከዐሥር ዓመት በኋላ የዓለም ዋንጫን እንድታስተናግድ ትናንት ዙሪክ ውስጥ ፕሬዚደንቱ ጊያኒ ኢንፋንቲኖ በአካል በተገኙበት የበይነ-መረብ ስብሰባ መርጧታል ። በሰብአዊ መብቶች እና ዴሞክራሲ ረገድ በርካታ ትችቶች የሚቀርቡባት ሣዑዲ ዓረቢያ አስተናጋጅ እንድትሆን በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር መወሰኑ ከወዲሁ ትችት እና ነቀፌታም አስተጋብቷል ። አንዳንድ በውጭ አገር የሚኖሩ የሣዑዲ ዓረቢያ የመብት ተሟጋቾች በዓለም ዋንጫ ወቅት ሣዑዲን የሚጎበኙ አገራት የሚመለከቱት በአገሪቱ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ አይሆንም ሲሉ ከወዲሁ ዐስጠንቅቃዋል ። ፊፋ እና የሣዑዲ መንግሥት የ2034 የዓለም ዋንጫን ማዘጋጀቱ ተጨማሪ ነጻነት እና የሴቶች መብት እንዲጎለብት ይረዳል ብለዋል ። የ2030 የዓለም ዋንጫ ደግሞ በሦስት አኅጉራት እንዲከናወን ትናንት ተወስኗል ። በዚህም መሠረት፦ ሞሮኮ፣ ስፔን እና ፖርቹጋል ። የ2030 የዓለም ዋንጫን በጋራ እንዲያሰናዱ ተወስኗል ። የዓለም ዋንጫ 100ኛ ዓመት በማስመልከት የሚደረጉ ጨዋታዎች ደግሞ አርጀንቲና፣ ፓራጓይ እና ዑራጓይ ውስጥም እንዲካሄድ ውሳኔ ተላልፏል ። 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።