1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሐምሌ 17 ቀን 2015 ዓ/ም የስፖርት ዝግጅት

ሰኞ፣ ሐምሌ 17 2015

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል የተጎናጸፉባቸው የሩጫ ውድድሮች በተለያዩ የአውሮጳ ከተሞች ተካሂደዋል። ትናንት ለንደን ባስተናገደችው የዳይመንድ ሊግ የሩጫ ውድድሮች በተለይ በርቀቱ ኳክብቶችን ባገናኘው የ5 ሺ ሜትር ውድድር ኢትዮጵያዊቷ ጉዳፍ ጸጋይ አሸናፊ ሆናለች ።

https://p.dw.com/p/4UJtY
Gudaf Tsegay | äthiopische Läuferin Leichtathletik
ምስል Chai v.d. Laage/imago images

የሐምሌ 17 ቀን 2015 ዓ/ም የስፖርት ዝግጅት

በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል የተጎናጸፉባቸው የሩጫ ውድድሮች በተለያዩ የአውሮጳ ከተሞች ተካሂደዋል። ትናንት ለንደን ባስተናገደችው የዳይመንድ ሊግ የሩጫ ውድድሮች በተለይ በርቀቱ ኳክብቶችን ባገናኘው የ5 ሺ ሜትር ውድድር ኢትዮጵያዊቷ ጉዳፍ ጸጋይ አሸናፊ ሆናለች ። ጉዳፍ የራሷን ምርጥ ሰዓት እና የቦታውን ክብረወሰን ባሻሻለችበት ውድድር 14 ደቂቃ ከ12 ሰከንድ የገባችበት ሰዓት ነው። በውድድሩ የኦሪገን የዓለም ሻምፒዮና የ5 ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያ ተሸላሚዋ ብያትሪስ ቺቤት ሁለተኛ ስትሆን ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ኔዘርላንዳዊት ሲፈን ሀሰን ሶስተኛ ወጥታለች። በውድድሩ የመጨረሻዎቹን ሁለት  ዙሮች ስትመራ የነበረችው ሲፈን ሀሰን በመጨረሻ መቶ ሜትር በሁለቱ አትሌቶች ብትቀደመም በርቀቱ የአውሮጳን ክብረ ወሰን ከማሻሻል ግን አላገዳትም ። የገባችበት 14 ደቂቃ ከ19 ሰከንድ ከ45 ማይክሮ ሰከንድ የአውሮጳ ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቦላታል። በውድድሩ ሌላኛዋ ተስፋ የተጣለባት ኢትዮጵያዊት መዲና ኢሳ አራተኛ ስትሆን ከ20 ዓመት በታች ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቦላታል። ውጤቱን ተከትሎ ጉዳፍ ለቡዳፔስት የዓለም ሻምፒዮና ከወዲሁ እንድትጠበቅ አስችሏታል። 
ከዳይመንድ ሊግ ውድድር ሳንወጣ ባለፈው ዓርብ ሞናኮ ፈረንሳይ ውስጥ በተከናወነ የዳይመንድ ሊግ የሩጫ ውድድር በ5000 ሜትር  ኢትዮጵያውያን ወንዶች ተከታታለው በመግባት አሸንፈዋል። የአንድ ሀገር ልጆች ብርቱ ፍልሚያ ባደረጉበት የርቀቱ ውድድር ሀጎድ ገብረህይወት አሸንፏል። ሀጎስ ርቀቱን ለማጠናቀቅ 12:42'18 ወስዶበታል። በሪሁ አረጋዊ እና ጥላሁን ኃይሌ ደግሞ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል። በውጤቱ ኢትዮጵያውያኑ በርቀቱ ለቡዳፔስቱ የዓለም ሻምፒዮና ተስፋ ከወዲሁ ተስፋ ማሳደራቸውን አሳይተዋል። በዕለቱ ከተከናወኑ ውድድሮች ቀልብ ገዝቶ በነበረው የሴቶች አንድ ማይል የሩጫ ውድድር  ኬንያዊቷ ፌይዝ ኪፒገን አዲስ የዓለም ክብረወሰን በማስመዝገብ ጭምር አሸናፊ ስትሆን ከአትሌቲክሱ ማኅበረሰብ አድናቆት ተችሯታል። ኪፒገን ርቀቱን ያጠናቀቀችበት ሰዓትም  4 ደቂቃ ከ7 ሰከንድ ከ64 ማይክሮ ሰከንድ ሆኗል። በውድድሩ ኢትዮጵያዊቷ ፍሬወይኒ ኃይሉ 3ኛ ወጥታለች። የአንድ ማይል ርቀት ክብረወሰን በትውልደ ኢትዮጵያዊት ኔዘርላንዳዊት ሲፈን ሀሰን እጅ የነበረ ሲሆን በጎርጎርሳውያኑ 2019 በተደረገ ውድድር የገባችበት ሰዓት 4:12.33 ነበር። ፌይዝ ኪፒገን የትናንት ምሽቱ ክብረወሰን በአንድ ወር ውስጥ ሶስተኛ ክብረወሰኗ ሆኖ ተመዝግቦላታል። አትሌቷ በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተይዘው የነበሩ የ1500 እና 5000 ሜትር ክብረወሰኖችን የግሏ አድርጋለች።
የኢትዮጵያ የስፖርት ሳይንስ ባለሞያዎች ማህበር ባለፈው ቅዳሜ ጉባኤውን አካሂዷል። ማህበሩ በለይ ስፖርት በሳይንስ ይደገፍ ዘንድ ባለሞያዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እና መብታቸው እንዲከበር የሚያስችል የአቋም መግለጫ አውጥቷል። በእግር ኳስ ዜና በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የዓለም የሴቶች የእግር ኳስ ዋንጫ በአውስትራሊያ እና ኒውዚላንድ የጋራ አስተናጋጅነት ባለፈው ሐሙስ በኒውዚላንድ በይፋ ተጀምሯል። 24 ሃገራትን በስምንት ምድቦች ከፍሎ የሚያፋልመው ውድድሩ ባለፈው ሐሙስ ሲጀመር በምድም አንድ የጥምረት አስተናጋጇ ኒውዚላንድ አውሮጳዊቷን ኖርዌይን በኤደን ፓርክ ገጥማ 1 ለ 0 አሸንፋለች። በምድብ ሁለት በተመሳሳይ የጥምረት አስተናጋጇ አውስትራሊያ አየርላንድ ሪፐብሊክን 1ለ0 አሸንፋለች። ባለፈው አርብ ሶስት የምድብ የመጀመሪያ ዙር ጫወታዎች የተስተናገዱ ሲሆን በምድብ አንድ ስዊዘርላንድ ፊሊጲንስን 2 ለ 0 ፤ አፍሪቃዊቷ ናይጄሪያ ከካናዳ ያለግብ ሲለዪኡ ስፔይን ኮስታሪካን 3 ለ 0 አሸንፏል። ቅዳሜ ቀጥሎ በተደረገው ጫወታ ጃፓን አፍሪቃዊቷን ዛምቢያ በሰፊ የጎል ልዩነት 5 ለ0 ስታሸንፍ ፤ እንግሊዝ ሃይቲን 1 ለ0  ፤ ዴንማርክ ቻይናን 1 ለ 0 እንዲሁም  የአራት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ አሜሪካ ቬየትናምን 3 ለ 0 አሸንፈዋል። በትናንት እሁዱ በተደረጉ ተመሳሳይ የምድብ የመጀመሪያ ዙር ጫወታዎች  ደግሞ በምድብ አምስት ኔዘርላንድ ፖርቹጋልን 1ለ0 በምድብ ስድስት የተደለደሉት ፈረንሳይ እና ጃማይካ ያለ ግብ 0 ለ0 እንዲሁም ስዊዲን ደቡብ አፍሪቃን 2ለ1 በማሸነፍ ተጠናቀዋል። 
የዙር ማጣሪያ ጫወታዎች ዛሬም ቀጥለው የተደረጉ ሲሆን በምድብ 7 ጣልያን አርጀንቲናን 1 ለ0 እንዲሁም በምድብ ስምንት የተደለደለችው ጀርመን አፍሪቃዊቷ ሞሮኮን 6 ለ ምንም ረምርማታለች። በውድድሩ እንደወንዶቹ ሁሉ ሞሮኳዊያኑ እንስቶች ትልቅ ተስፋ ተጥሎባቸው የነበረ ቢሆንም ገና በጠዋቱ አስከፊ ሽንፈት ተከናንበዋል። ኒውዚላንድ እና አውስትራሊያ በጋራ እያስተናገዱ የሚገኘው  የ2023 የዓለም ዋንጫ ለአንድ ወር ይቆያል።  
በሌሎች የእግር ኳስ ዜናዎች በሳምንቲ የመጨረሻ ቀናት ኃያላኑ የአውሮጳ ሊጎች የተለያዩ የወዳጅነት ጫወታዎችን አከናውነዋል። የቅድመ ውድድር የዝግጅት ጊዜአቸውን ወደ አሜሪካ በመጓዝ እያሳለፉ የሚገኙት አርሴናል እና ማንችስተር ዩናይትድ ባለፈው ቅዳሜ ምሽት ያደረጉት የወዳጅነት እና ብርቱ ፉክክር በታየበት ጫወታ ማንችስተር ዩናይትድ 2 ለ 0 አሸንፏል። ሁለቱም ቡድኖች አዳዲስ ፈራሚ ተጫዋቾችን ያሰለፉ ሲሆን አዳዲስ ታክቲኮችን ለመተግበር ሞክረዋል።በተመሳሳይ ፍላዴልፊያ ውስጥ የተገናኙት አስቶን ቪላ እና ኒውካስትል ዩናይትድ 3 አቻ በሆነ ውጤት አጠናቀዋል። 
 በሌላ የወዳጅነት ጫወታ እዚያው ሎስ አንጀለስ አሜሪካ የሚገኙት ሪያል ማድሪድ እና ኤሲ ሚላን ጫወታቸውን አድርገው ከጀርመኑ ቦሩሽያ ዶርትሙንድ እንግሊዛዊውን አጥቂ ዩዴ ቤልንግሃምን ያስፈረመው ማድሪድ 3 ለ 2 አሸንፏል። ከጫወታው በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት የሪያል ማድሪዱ አሰልጣኝ ካርሎ አንጀሎቲ « እንዲህ አይነት ድንቅ ብቃት ያላቸው ተቻዋቾች ጥቂት ናቸው » ሲሉ አሞካሽተውታል። 
ሳይጠበቅ ወደ አሜሪካ ሊግ ያቀናው የቀድሞ የፒኤስ ጂ አጥቂ እና የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን አምበል ሊዮኔል ሜሲ በኢንተር ማያሚ የመጀመሪያ ቀን ተሳትፎው ከእግር ኳስ ማኅበረሰብ አድናቆት የተቸረበትን ጊዜ ማሳለፍ ችሏል።  ባለፈው ቅዳሜ ክሩዝ አዙልን በሊግ ጫወታ የገጠመው ኢንተር ማያሚ ሊዮኔል ሜሲ በ94ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ ማሸነፍ ችሏል። ኢንተር ማያሚ ሜሲ ከመድረሱ አስቀድሞ የሊጉን ጨምሮ ባደረጋቸው 11 ጫወታዎች አንዱንም ማሸነፍ አልቻለም ነበር። ሜሲ ከመድረሱ ማሸነፍ መቻሉ የተጫዋቹን ድንቅ ብቃት አስመስክሮለታል። ጫወታውን የዓለም ሜዳ ቴኒስ ንግስቷን ሴሪና ዊልያምስ እና በአንድ ወቅት የእንግሊዝ የእግር ኳስ ጉብሉን ዴቪድ ቤክሃምን ጨምሮ በርካታ ስመጥር እና ዝነኛ ሰዎች ታድመውበታል። 
የመኪና እሽቅድምድም
ትናንት በተካሄደ የሃንጋሪ ግራንድ ፕሪክስ የመኪና እሽቅድምድም ኔዘርላንዳዊው ቁጥር አንድ ማክስ ፈርስታፐን አሸናፊ ሆናል። ማክስ ውድድሩን ለመቸረስ 1 ሰዓት ከ38 ደቂቃ ከ08 ሰከንድ የፈጀበት ሲሆን ይህም ለ11ና ጊዜ አሸናፊነቱን አስጠብቆ የወጣበት አድርጎታል። በውድድሩ እንግሊዛዊው ቁጥር አራት ላንዶ ኖሪስ ሁለተኛ እንዲሁም ጣሊያናዊው ቁጥር 11 ሰርጂዮ ፔሬስ ሶስተኛ ወጥተዋል። 

Fußball | Leagues Cup | Cruz Azul vs Inter Miami | Messi
ሊዮኔል ሜሲ ለኢንተር ማያሚ የመጀመሪያውን ጎል ካስቆጠረ በኋላ ምስል Lynne Sladky/AP Photo/picture alliance
FIFA Frauen-Weltmeisterschaft 2023: Deutschland - Marokko; 24.07.2023
የሞሮኮ ሴት ብሔራዊ ቡድን ምስል Jones/BEAUTIFUL SPORTS/picture alliance
Australien Melbourne | Frauen WM | Tor für Deutschland
የጀርመን ቭሄራዊ ቡድን አጥቂ ክላራ ቡኤልምስል James Ross/Imago Images
FIFA Frauen Fußball WM Australien und Neuseeland 2023 | Eröffnungsfeier
የ2023 የሴቶች የዓለም ዋንጫ መክፈቻምስል David Rowland/REUTERS
Olympische Spiele Tokio | Faith Kipyegon Siegerin 1500 Meter Frauen
አትሌት ፌዝ ኪፒገን የሶስት ክብረ ወሰኖች ባለቤትምስል JEWEL SAMAD/AFP
Tokio 2020 | 10000m - Sifan Hassan
አትሌት ሲፈን ሀሰን የቶክዮ ኦሎምፒክ 10ሺ ሜትር አሸናፊምስል LUCY NICHOLSON/REUTERS
Olympische Spiele Tokio | Gudaf Tsegay Äthiopien
አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ በቶክዮ ኦሎምፒክ 5 ሺ ሜትር ትንቅንቅ ምስል JAVIER SORIANO/AFP

ታምራት ዲንሳ