1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመሬት መንቀጥቀጥ በፈንታሌ

ሥዩም ጌቱ
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 15 2017

አብደላ የተባሉ ሌላው አስተያየት ሰጪ የአዋሽ ከተማ ነዋሪ በተደጋገመው የመሬት መንቀጥቀጥ ማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ የስነልቦና ጫና እየደረሰ ነው ባይ ናቸው፡፡ “የስነልቦና ችግር እያመጣብን ነው፡፡ ሰው ሁሉ ውጪ እያደረ ነው፡፡ አሁን ላይ ከመንቀጥቀጥም አልፎ እያዘለለን ነው ብለዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4oYH8
Fluss Awash - Äthiopien
ምስል Seyoum Getu/DW

የመሬት መንቀጥቀጥ በፈንታሌ

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ በተለይም መታሃራ ከተማ ዙሪያ እና አዋሳኝ የአፋር ክልል በትናንትናው እለት ከፍተኛ የመሬት መንቀጠቀት እንደነበር የአከባቢው ነዋሪዎች አስታወቁ፡፡
በትናንትናው እለት በተለይም ማታ አከባቢ በሬክተርስኬል 4.9 የተለካ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱም ተመዝግቧል፡፡
የመሬት መንቀጥቀጡ ቤቶችን ከመሰነጣጠቅ እስከ ተራራ መናድ እና የኤሌክትሪክ ምሶሶዎች መውደቅ አደጋም አስከትሏል ነው የተባለው፡፡
መስፍን መርጊያ የተባሉ የመታሃራ ከተማ አስተያየት ሰጪ የትናንቱ ርዕደ መሬት እጅጉን አስፈሪ ነው ይላሉ፡፡ «ቀኑን ሙሉ መሬት ስትዘፍን ዋለች» የሚሉት አስተያየት ሰጪው የመታሃራ ነዋሪ በተለያዩ በፈንታሌ ወረዳ በተለያዩ አከባቢዎች የመብራት ምሶሶ ወድቆ አደጋ ከመፍጠር እስከ የፈንታሌ ተራራ መናድ መመልከታቸውን አስረድተዋል፡፡
“ከሚገባው በላይ ሬክተር ስኬሉ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ወላ ቆሜ ጥሎኝ ነበር፡፡ ትናንት የፈንታሌ ጋራው ላይ ከፍተኛ ጭስ መሳይ አቧራ ይታይ ነበር፡፡ በሁለት አቅጣጫ ነው ተራራው ላይ ጭስ የታየው፡፡ ወድቆ እሳት የፈጠረው ፖልም በዚያው አቅራቢያ ነው፡፡ ለአምስተኛ ጊዜ ነው ትናንት ከፍተኛ መንቀጥቀጥ ያስተዋልኩትና ከፈንታሌ ተራራው ደግሞ ከፍተኛ የፍንዳታ ድምጽ ተሰምቷል፡፡ በሁለት በኩልም የተደረመሰ መስሏል” ብለዋል፡፡
የመሬት መንቀጥቀጡ ልኬት
ከመተሐራ ከተማ አቅራቢያ 13 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ቦታ ትናንት ሰኞ ምሽት በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረቱ አዲስ አበባ ድረስ መሰማቱንና በሬክተር ስኬል 4.9 የተመዘገበ መሆኑን የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ መስሪያ ቤት አስታውቋል።  
የትናንቱ የመሬት መንቀጥቀጥ ሃያ አራት ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በአካባቢው ለሁለተኛ ጊዜ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ እሁድ ለሊት 10 ሰዓት ከ13 ደቂቃ አካባቢ ከአዋሽ ከተማ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለ ስፍራም ተከስቶ እንደነበርም ተመልክቷል፡፡
የእሁድ ለሊቱ የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 4.6 የሚለካ እንደሆነና የትናንቱ ሰኞ ታህሳስ 14 ቀን 2017 ምሽት 4ሰዓት ከ40 የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ፤ በሬክተር ስኬል 4.9 ነው።
የመታሃራ ከተማ ነዋሪው አቶ መስፍን እንደሚሉትም፤ “ማታ መብራ ጠፋ ወዲያው፡፡ በከተማዋ ከንቲባም አስቀድሞ አደጋ ከሚፈጠርበት ርቃችሁ ውጪ ሁኑ ተብሎ የጥንቃቄ መልእክት ታውጆ ነበርና ህዝቡ ውጪ ነው ያደረው፡፡ መንቀጥቀጡ ከባድ ስለነበር እስከማቅለሽለሽ ስሜት ይሰማን ነበር” ብለዋል፡፡
በመሬት መንቀጥቀጡ የማህበረሰቡ ሥጋት
አብደላ የተባሉ ሌላው አስተያየት ሰጪ የአዋሽ ከተማ ነዋሪ በፊናቸው በተደጋገመው የመሬት መንቀጥቀጥማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ የስነልቦና ጫና እየደረሰ ነው ባይ ናቸው፡፡  “የስነልቦና ችግር እያመጣብን ነው፡፡ ሰው ሁሉ ውጪ እያደረ ነው፡፡ አሁን ላይ ከመንቀጥቀጥም አልፎ እያዘለለን ነው፡፡ ያው ጭንቀት ስለሆነ ያስጨንቃል እንጂ በአንድ ጊዜ ሶስት አራት ሰከንድ ነው የሚቆየው፡፡ ግን በቀን አስር ጊዜ ሊደጋገም ይችላል፡፡ የማታው ደግሞ በጣም የተለየ ነው፡፡ እንደ ውሻ ያሉ እንስሳት ሁሉ እየተረበሹ ነበር፡፡ ቤቶች ተሰነጣጥቋል፡፡ ወደ ተራራው ደግሞ የባሰበት ነው፡፡ ሁለት ሰዎች ተቀራርበው ብያወሩ እስከመጋጨት የሚደርስ ከባድ መንቀጥቀጥ አለ፡፡ እና መንግስት ትኩረት አድርጎ ቢያስጠናው ባይ ነኝ” ብለዋል፡፡
የባለሙያ አስተያየት
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስና ሳይንስ የምርምር ተቋም የሶስሞሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ፤ የመሬት መንቀጥቀጥ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፈሰር አታላይ አየለ ባለፈው መስከረምና ጥቅምት አከባቢ ፈንታለ ዙሪያ ረዘም ላለ ጊዜ የነበረው የመሬት መንቀጥቀት ተረጋግቶ ከቆየ በኋላ ከስድስት ቀናት በፊት እንደገና መነሳቱን ገልጸዋል፡፡ “አሁን ትናንት የተመዘገበው 4.9 ከፍተኛው ነው፡፡ ፈንታሌ እሳተገሞራ አከባቢ ነው የተፈጠረው፡፡ መታሃራ አከባቢ ሰዎች በታም እየተሰማቸው ነበር” ብለዋል፡፡ “አሁንም እንቅስቃሴው የመለኪያ መሳሪያ ላይ መቀጠሉን ያሳያል” የሚሉት ባለሙያው እንደ ከዚህ ቀደሙ ይረጋጋል ወይም የአለት ፍሰት ሊያስከትል ይችላል የሚለው ግን ገና አልታወቀም ብለዋል፡፡
ፈንታሌ ተራራ ላይ ስለተሰማው ድምጽና የተስተዋለውን ጭስ መሳይ አቧራ በተመለከተም ፕሮፈሰር አታላይ፤ ናዳ ስላለ እሳቱ ከየት እንደመጣ ለጊዜው አለመታወቁን ገልጸዋል፡፡ የሆነ ሆኖም በአይነ ቁራኛ በመከታተል ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ማህበረሰቡ በተለይም ፎቆች አከባቢ ጠንከር ያለ ጥንቃቄ በመውሰድ የሚሰባበሩ እቃዎችም ካሉ መሬት ማስቀመጡ ይበጃል ብለዋል፡፡  
ሥዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ኂሩት መለሰ