የመስፍን ስንብት፤ የፖሊስ ሰልፍ፤ የመቐለና አዲስ አበባ ፍጥጫ
ዓርብ፣ መስከረም 22 2013ኢትዮጵያ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን በ90 አመታቸው ተሰናበተች። መስፍን በኮሮና ታመው በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በሕክምና ሲረዱ ከቆዩ በኋላ ባለፈው መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። በርካታ ኢትዮጵያውያን ፌስቡክ እና ትዊተርን በመሳሰሉ ማኅበራዊ ድረ ገፆች በመስፍን ከዚህ ዓለም በሞት መለየት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።
ርዕሰ-ብሔር ሣህለ ወርቅ ዘውዴ "በሀገራችን የፓለቲካ ምህዳር አንጋፋ ቦታ የነበራቸው፤ ሃሳባቸውን ካለ ምንም ይሉኝታና ፍርሃት በመግለጽ የምናውቃቸው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ከዚህ ዓለም በሞት ስለተለዩን በጣም አዝኛለሁ" ብለዋል። ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው በመስፍን ሞት ሐዘናቸውን ለመግለጽ ባሰፈሩት አጭር መልዕክት "የሐሳብ ልዕልና ምልክት፤ የሰላማዊ ትግል አርዓያ፣ ላመኑበት ነገር እስከ መጨረሻቸው ሞጋች፣ ላመኑበት እውነት ብቻ የሚቆሙ" ሲሉ ገልጸዋቸዋል።
መስፍን በሙያቸው የጂኦግራፊ ፕሮፌሰር ይሁኑ እንጂ በፖለቲካ ተሳትፏቸው እና ትችቶቻቸው የበለጠ ተቀባይነት አግኝተው ላቅ ያለ ሚና ተጫውተዋል። የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር በቀስተ ደመና፣ ቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ ኋላም በአንድነት ፓርቲ ምሥረታ እና እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራር የነበሩት አቶ ሙሼ ሰሙ መስፍንን ከ1984 ዓ.ም. ገደማ ጀምሮ እንደሚያውቋቸው በግል የፌስቡክ ገፃቸው አስፍረዋል። "ፕሮፌሰር መስፍን እስከ ዛሬ ድረስ ከኢዴፓ ጋር አብሮ የዘለቀውን እና ከጅማሮው ለኢዴፓ ግንባታ ትልቅ አስተዋጽዖ ያበረከተውን የለንደን ድጋፍ ሰጭ ኮሚቴ ከኢዴፓ ጋር ማስተዋወቃቸውን ጠቅሼ አለማለፉ ንፉግ ያደርገኛል" ያሉት ሙሼ ውይይታቸው ሙግታቸውንም አስታውሰዋል።
በ1997 ዓ.ም. ከተካሔደው ምርጫ ዋዜማ በቅንጅት መስራች ስብሰባዎች ኢዴፓን ወክለው ሲገኙ ከመስፍን መገናኘታቸውን ያስታወሱት ሙሼ "የቅንጅት ስብሰባ ሁሌ የተራዘመና የሚያስመሽ ስለነበር ፕሮፌሰር መኪና በማይዙበት ጊዜ ከሃያ ሁለት፣ ፒያሳ ቤታቸው ድረስ የመሸኘትና በሀገራችን ጉዳይ ላይ የመወያየት ሰፊ እድል አግኝቼ ነበር። በዛን ጊዜ በብዙ ሀገራዊ፣ ሕዝባዊና ሞራላዊ ጉዳዮች ላይ የመወያየት፣ መሳ ለመሳ የመናበብ፣ በልዩነት የመነታረክና አልፎ ተርፎም በጉዳዮች ልዩነት ጠንከር ያልን ጊዜ ደግሞ የታላቅነት ተግሳጻቸውንና ወቀሳ፣ አልፎ ተርፎም ቁጣቸውን አጣጥሜበታለሁ። ከነውጣ ወረዱም ቢሆን፣ በዚያ ሂደት ብዙ ተምሬበታለሁ" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት እንዲቋቋም ሐሳብ ካመነጩ እና ውጥኑን ተግባራዊ ካደረጉ መካከል አንዱ መስፍን ነበሩ። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ሕልፈታቸው ከተሰማ በኋላ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ባሰራጨው የሐዘን መግለጫ "ፕሮፌሰር መስፍን ዘመናቸውን ሁሉ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ የሕግ ልዕልና እና የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ለፍተዋል" ብሏል።
"ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በኢትዮጵያ ካሉት ታላላቅ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች አንዱ ሆነው በታሪክ ሲታወሱ ይኖራሉ" ያለው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ "ለበርካታ አስርት አመታት የማይናወጥ ቁርጠኝነት የተሞላበት ሕይወት ከመኖራቸው ባሻገር ብዙውን ጊዜ እስራትን የሚጨምር ከባድ ዋጋ ከፍለዋል" በማለት ከፍ ያለ ሚና እንደነበራቸው ዘክሯል።
መስፍን ዕድሜያቸው 90 ደርሶ እንኳ በፌስቡክ በተከታታይ ሐሳባቸውን ያካፍሉ ነበር። በመስከረም ወር ብቻ በስማቸው በተከፈተ የፌስቡክ ገፃቸው አራት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጽሁፎች አጋርተዋል። መስከረም 7 ቀን 2013 ዓ.ም. በጻፉት አጭር ጽሁፍ "ስንጋደል የሚከለክለን ወይም የሚገላግለን የለም፤ ቤቶቻችን ሲፈርሱና የሰው ልጅ በየመንገዱ በፕላስቲክ እየተጠለለ ሲኖር አቤት የሚባልበት የለም፤ ልጃገረዶች ታፍነው ተወስደው ወላጆች ሲጨነቁ አለሁላችሁ የሚል የለም" በማለት ምሳሌ እየጠቀሱ የኢትዮጵያ ነባራ ሁኔታ ተስፋ እንዳስቆረጣቸው ጠቆም አድርገው ነበር።
በዚሁ የፌስቡክ ገፃቸው "ዛሬም እንደትናንት" የተባለ በነሐሴ 2012 ዓ.ም. የታተመ መጽሐፋቸውን የፊት ሽፋን አጋርተው ነበር። ከዚህ ቀደም "የክህደት ቁልቁለት" እንዲሁም "አዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ" የተባሉትን ጨምሮ በርከት ያሉ አነጋጋሪ መጻሕፍት ለንባብ አብቅተዋል።
መስፍን የተጽዕኖ ፈጣሪነታቸውን ያክል አወዛጋቢ አስተያየቶችም ይሰጡ ነበር። ለዚህ ቴዲ አማራ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ የጻፉት መልዕክት ማስረጃ ይሆናል። "መስፍን ወልደማርያም ኖሮ ኖሮ ዛሬ አረፈ። አማራ የለም ሲል በአደባባይ የተሳለቀው ሰውዬ አሁን እሱ የለም። አማራ ግን አለ። ለማንኛውም ነብስ ይማር" ብለዋል ቴዲ አማራ።
የሕግ መምህሩ ዶክተር ሔኖክ ገቢሳ "ኋላ ቀር የፖለቲካ አቋም ቢኖርዎም ሐሳብዎን ለመግለጽ የነበርዎ ድፍረት ለብዝኃነት ሲባል ሊከበር ይገባል" ሲሉ በሰላም እንዲያርፉ በተመኙበት አጭር የትዊተር ጽሁፍ ስለ መስፍን ያላቸውን አተያይ አስፍረዋል። ሌላ ባሪ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ በበኩላቸው "መስፍን ወልደማርያም ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሰብዓዊ መብቶች ጥብቅና አልቆሙም። በኢትዮጵያ ፖለቲካ አወዛጋቢ ሰው ነበሩ። በሰላም እንዲያርፉ ተዋቸው። ነገር ግን ለአስርት አመታት ጥሩ ካልነበረ ሰው ጀግና አትፍጠሩ" በማለት ሌሎች "የኔታ" እያሉ በሚያሞካሿቸው ሰው ተክለ ስብዕና የተለየ አተያይ እንዳላቸው አስፍረዋል።
ጋዜጠኛ ስታሊን ገብረስላሴ ደግሞ "ባንድ ወቅት ዛሬ ከዚህ አለም በሞት የተለዩት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ''መለስ ዜናዊ የወያኔ ከ4 ኪሎ መውጣት ሳያይ መሞቱ እጅግ ይቆጨኛል'' ሲሉ በቅርብ ወዳጆቻቸው ጭምር ተወቅሰዋል። እንደዛ ባይሉ ጥሩ ነበር። ሁሉም በየተራ ይሄዳል። ታሪኩ ግን ይቀራል። ፕሮፌሰሩም አረፉ፤ ነብስ ይማር" ሲል በግል የፌስቡክ ገጹ አስተያየቱን አስፍሯል።
የፌድራል ፖሊስ-ወታደራዊ ሰልፍ
አዲሱን መለዮ የለበሱ፤ አድማ መበተኛ ጭስ መተኮሻ መሳሪያዎች የታጠቁ፤ ራሳቸውን ከጉዳት መከላከያ መሳሪያዎች ያነገቡ የፌድራል ፖሊስ አባላት በዚህ ሳምንት በጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፊት ያሳዩት ሰልፍ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተለያየ ትርጉም ተሰጥቶታል። ከሰልፈኞቹ መካከል ክላሽንኮቭ የታጠቁልዩ ልዩ የጦር መሳያዎች ያነገቡ አነፍናፊ ውሾች የሚጎትቱ፤ ፈረስ የሚጋልቡ የፌድራል ፖሊስ አባላት እና ፈንጂ አምካኞች ጭምር ነበሩበት።
ተድላ ሙንዬ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ሰልፉ ከታየ በኋላ "በጸጥታ አስከባሪዎቻችን ኮርቺያለሁ" ብለዋል። መብራሕቱ ከለሌ የተባሉ ሌላ የፌስቡክ ተጠቃሚ "በምሥራቅ አፍሪካ እንደመኖራችን ራስህን ማጠናከር በጣም አስፈላጊ ነው። ስራና ሰሪ ኣላጣንም። በመንደር ረባሾች ነው ሁሌ ወደ ኋላ የምንጓተተው" የሚል አስተያየት አስፍረዋል።
ያያ ኪያ "ፌደራል ፖሊስ አስተማማኝ ህዝባዊ ሰራዊት ነው። ዛሬ ብለያችሁም አብሬ በነበርኩበት ጊዜ ሕግና ስርአቱን ተከትላቹ እንደምትሰሩ አውቃለሁኝ" የሚል አስተያየት አስፍረዋል።
አንዱዓለም ታደሰ "የበለጸገች ኢትዮጵያን አሳያለሁ ያለን መንግስት ወደ ሰርከስ ኢትዮጵያ እየተለወጠ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። በአንድ ወር ሁለተኛ የአደባባይ የወታደር ትርኢት። የሰሜን ኮሪያው ኪም ሁላ "ይህንንስ እኔም አላሰብኩት" የሚል ይመስለኛል!! ...ግን ብንነጋገር አይሻልም?" የሚል አስተያየት ጽፈዋል። ሚካኤል ጆርጌ "የሰው ልጅ ጭንቅላቱ ካልተቀየረ ልብሱ ቢቀየር በየቀኑ ባዶ ነው" በማለት የደንብ ለብስ ቅያሬ ብቻ ለውጥ እንደማያመጣ ገልጸዋል።
አብዲ ቦሪ ደግሞ "የፖሊስ ሰልፍ ማካሔዱ ለምን እንዳስፈለገ አልገባኝም። ነው ወይስ ትግራይ የተደረገውን እየደገሙ ነው?" ሲሉ ጠይቀዋል። ከዚህ ቀደም በትግራይ ክልል የተለያዩ ከተሞች የጸጥታ አስከባሪዎች ተመሳሳይ ሰልፎች ማድረጋቸው አይዘነጋም። በአዲስ አበባም ተመሳሳይ ወታደራዊ ሰልፍ ተካሒዶ ነበር።
የአዲስ አበባ እና የመቐለ ፍጥጫ
ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመሩት የፌድራል መንግሥት እና ባለፈው ጳጉሜ አራት ከተካሔደ ምርጫ በኋላ የተመሠረተው የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የገቡበት ውጥንቅጥ በመጪው መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ወደ አዲስ ምዕራፍ ይሸጋገራል።
የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ ከመስከረም 25 በኋላ የምኒስትሮች ምክር ቤት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የጠቅላይ ምኒስትሩ ሥልጣኖች ሕጋዊ አይሆኑም ሲሉ ለትግራይ ብዙኃን መገናኛ ኤጀንሲ ተናግረዋል። አቶ አስመላሽ የጠቀሷቸው ሥልጣኖች በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ምርጫ ባለመካሔዱ ምክንያት ሕገ መንግሥት ተተርጉሞ በፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲራዘሙ ተወስኗል። የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ግን ይኸን አይቀበሉም። አቶ አስመላሽ ከመስከረም 25 በኋላ "ይኸ መንግሥት ሕጋዊ ስላልሆነ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ በምኒስትሮች ምክር ቤት፣ በጠቅላይ ምኒስትር የሚሰጡ ትዕዛዞች እና ውሳኔዎች የሚወጡ ሕጎች ትግራይ ላይ ተቀባይነት የላቸውም" ብለዋል።
መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጋራ የአመቱን የመጀመሪያ ጉባኤ የሚያካሒዱበት ነው። በዚህ ስብሰባ ግን የትግራይ ተወካዮች እንደማይሳተፉ አስመላሽ ተናግረዋል። በሒደት እየሻከረ ወደለየለት ፍጥጫ ያመራው የሁለቱ ኃይሎች ግንኙነት ከመስከረም 25 በኋላ ምን መልክ እንደሚኖረው የሚያሳስባቸው በርካቶች ናቸው።
ቀበና ኢንሳይደር የተባለ እና ለፌድራል መንግሥቱ የሚደላ የፌስቡክ ገጽ "የግራ አስተሳሰብ ሁሌ ግራ ተጋብቶ ግራ ያጋባል። ህወሀት የግራ ጁንታ መሆኑ ይታወቃል። የግራ ፖለቲካ ደግሞ ውሸት ሲደጋገም እውነት እንደሚሆን ያምናል። መስከረም 25/30 የሚደጋገመዉ ለዚህ ይመስላል። ህወሀት ከፈረሶቹ ጋር ብቅ ጥልቅ እያለ ይፎክራል። በህገ-መንግስት እና በፌዴራሊዝም ስም ያለቃቅሳል። ከመስከረም 25/30 በኋላ መንግስት ስለማይኖር " ባለአደራ መንግስት ከሰማይ ይዉረድልኝ" ይላል" የሚል ከረር ያለ ወቀሳ እና ትችት ሰንዝሯል።
ኤልያስ ሑሴን የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ "መስከረም 25 መጪው ሰኞ ነው። ከማክሰኞ እለት ጀምሮ የአብይ አህመድ ስልጣን ያበቃለታል" ብለዋል። ሌላ የፌስቡክ ተጠቃሚ "ለዚህ ሁሉ በአገራችን ለተከሰተው ችግር ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ተጠያቂ ነው ። ምክንያቱም ህወሓት ስልጣን ሲለቅ እንደ ባለአደራ መንግስት መሆኑን አምኖ ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ አገራዊ ስምምነት ማካሄድ ሲገባው፤ ዘራፍ እኔ ይችን አገር ለአስር አመት ለማስተዳደር እቅድ ጨርሻለሁ ማለቱ በጣም የስልጣን ጥመኛ መሆንን ያሳያል። በተቻለ መጠን ፖለቲከኞች ወይም አዋቂ ነኝ ባዮች መጀመሪያ ህዝቡን ከምታንገላቱ እራሳችሁ ተስማሙ" ሲሉ ጽፈዋል።
እሸቴ በቀለ