1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሙቀት ማዕበል በአውሮጳ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 14 2014

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከመጠን ያለፉ የአየር ጠባይ ሁኔታዎች እዚህ ጀርመንም ሆነ በተለያዩ ሃገራት እየተከሰቱ ነው። ባሳለፍነው የሳምንት መጨረሻ ጀርመንን ጨምሮ በብዙዎቹ የአውሮጳ ሃገራት የነበረው ከፍተኛ የሙቀት ማዕበል በአንዳንድ አካባቢዎች እሳት አስነስቷል። በቀጣይም የሙቀቱ መጠን እየጨመረ ድርቅ ሊያስከትል እንደሚችል እየተነገረ ነው።

https://p.dw.com/p/4D1gX
Symbolbild Hitzewelle
ምስል Weber/Eibner-Pressefoto/picture alliance

ጽንፍ የወጣው የአየር ሁኔታ

የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የበጋ ወራት ከወትሮው አስቀድሞ መግባቱን ነው የየሃገራቱ የሜትሪዎሎጂ አገልግሎት መረጃዎች የሚያመለክቱት። እዚህ ጀርመን ከዚህ ቀደም ሚያዝያ እና ግንቦት በዝናብ ታጅበው ሰኔ ዕለት በዕለት ቀስ እያለ ከዝቅተኛ የሙቀት መጠን ወሩ ወደ መጨረሻው ሲቃረብ ከፍ ማለቱ የተለመደ ቢሆንም ዘንድሮ ግን ከመጠን ያለፈው ሙቀት አስቀድሞ ተከስቷል። ይኽ ስፔን ላይም ተመሳሳይ እንደሆነ ነው ማድሪድ የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ገልጸውልናል።

እዚህ ጀርመንም የበጋው ሙቀት አስቀድሞ በመምጣቱ በምህረት የለሹ ቅዝቃዜ ሲቆራመድ የከረመው ሁሉ በረዥሙ የቀን ብርሃን መንፈሱ ፈክቶ በናፍቆት የጠበቃትን ፀሐይ በአኮቴት ቢቀበልም ፀሐይዋ ግን ከሙቀቷ አልፋ ታቃጥል ጀምራለች።

Hitzewelle | Spanien Bilbao
ቢልባኦ ስፔንምስል Vincent West/REUTERS

በየዓመቱ የበጋውን ሙቀት ተከትሎ ከሰደድ እሳት ጋር የምትታገለው ስፔን ዘንድሮም ተመሳሳይ ችግር ገጥሟታል። በሰሜናዊ ስፔን ናቫሬ ክፍለ ሀገር በ12 መንደሮች የሚገኙ አንድ ሺህ ገደማ ነዋሪዎች ትናንት አካባቢውን ለቀቅው ለመሸሽ መገደዳቸው ተነግሯል። የሙቀት ማዕበሉ በየጊዜው ተጠናክሮ በሚደጋገምባት ስፔይን በተለይም ሀገሪቱ ከፖርቱጋል ጋር በምትዋሰንባቸው አካባቢዎች 25 ሺህ ሄክታር ደን በዚሁ እሳት ወድሟል። ለማሳያነት ጀርመን እና ስፔንን አነሳን እንጂ እነ ግሪክ፣ ፖርቱጋልም ሆኑ ፈረንሳይ እና ሌሎችም የአውሮጳ ሃገራት የሙቀት ማዕበል እና መዘዙን እየታገሉ ነው። የዛሬ 20 ዓመት የተከሰተው የሙቀት ማዕበል በመላው አውሮጳ ወደ 70 ሺህ ገደማ ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉ ተመዝግቧል። ያኔም ኃይለኛው ሙቀት በሰኔ ወር ላይ የጀመረ ሲሆን ሐምሌን ይዞ ነሐሴ አጋማሽ ላይ እንዳበቃም መረጃዎች ያሳያሉ። ዘንድሮም እንደተባለው ሙቀቱ ቀደም ብሏል። ገና ነገ ከነገ ወዲያ እዚህ ጀርመን የሙቀት መጠኑ ወደ 30 ዲግሪ ከፍ እንደሚል ከወዲሁ ተነግሯል። ሙቀቱ ደግሞ ብቻውን አይመጣም። ሙቀቱን የሚከተለው የውኃ እጥረት ሊሆን እንደሚችል ምልክቶች መታየት በመጀመራቸውም ዓመቱ የድርቅ ዓመት ሊሆን እንደሚችልም እየተገለጸ ነው። ከቀናት ከፍተኛ ሙቀት በኋላ ጀርመን ውስጥ በበርካታ ቦታዎች ሰኞ ዕለት የዘነበው ዝናብ መሬቱ እጅግ በመድረቁ ምክንያት የጋለ ድንጋይ ላይ እንደፈሰሰ ውኃ እዚያው መቅረቱን ነው የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን የዘገቡት። የተመድ የአካባቢ ጥበቃ መርሃግብር እንደሚለው በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም ከ2,3 ቢሊየን በላይ ሕዝብ የውኃ እጥረት አጋጥሞታል። ድርቅም እየተደጋገመ ነው።

Spanien Tafalla | Waldbrände
ምስል Eduardo Sanz/Europa Press/Abaca/picture alliance

የሙቀት ማዕበል ድርቀት ማስከተሉ እንዳለ ሆኖ ድንገት የሚመጣው ዝናብ ባልከፋበት አካባቢ አየሩን በደረድ ሲያደርግ በባሰበት ስፍራ ደግሞ በሰው እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ማስጠንቀቂያ እየተሰጠ ነው።  በደቡብ እና ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ እንዲሁም በሌሎች በርከት ባሉ አካባቢዎች ድርቅ ጉዳት እያስከተለ መሆኑ በሚነገርበት በዚህ ወቅት ከሰሞኑ አዲስ አበባ ላይ የወረደው ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ የሰው ሕይወት መቅጠፉ ተሰምቷል።

Deutschland Waldbrand Brandenburg Treuenbrietzen Beelitz
የሙቀት ማዕበሉ ያስከተለው ሰደድ እሳት በጀርመንምስል Cevin Dettlaff/dpa/picture-alliance

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተደጋግሞ የሚታየው ከመጠን ያለፈው ቅዝቃዜም ሆነ የሙቀት ማዕበል የአየር ንብረት ለውጥ እውን የመሆኑ ዋነኛ ማመላከቻ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ። የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት መቀነስ ወሳኝ እንደሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከስምምነት በተደረሰው መሠረት በኢንዱስትሪው ያደጉ ሃገራት ታሪካዊ ኃላፊነት ስላለባቸው የየበኩላቸውን ለማድረግ ቃላቸውን ሰጥተው ነበር። ሆኖም የዩክሬን ሩሲያ ጦርነት ባስከተለው የጋዝ አቅርቦት እጥረት ስጋት ዳግም ከባቢ አየርን በካይ ወደሆነው የኃይል ምንጭ ለመመለስ ዳርዳር እያሉ ነው። አሁንም ግን የሙቀቱ መጠን በተለይ በቀጣይ የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የበጋ ወራት ባላቸው ሃገራት እስከ 40 ዲግሪ እና ከዚያም በላይ ከፍ እያለ እንደሚሆን ፤ ከድርቅ ሌላ ድንገተኛ ዝናብ እና ጎርፍ ሊከተል እንደሚችል የአየር ሁኔታ ቅድመ ትንበያ መረጃዎች እያሳሰቡ ነው። ለሁሉም በዚህ የሙቀት ጊዜ ውኃ በብዛት መጠጣትን የህክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

Deutschland Waldbrand Brandenburg Treuenbrietzen Beelitz
የደን ቃጠሎውን ለማጥፋት የተደረገው ጥረት በከፊልምስል Stephanie Pilick/dpa/picture-alliance

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ