የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች በቅርስ መዝገብ
ዓርብ፣ ኅዳር 30 2009በተለያየ ዘርፍ ልዩ ልዩ የዓለም ሃገራት ባህል የተንፀባረቀበት ይህ ጉባዔ ከ 121 በላይ የዓለም ሃገራት የመጡ ኢትዮጵያዉያንን ሳይጨምር 710 ተሳታፊዎችን ያካተተ ነበር። ጉባዔዉ ባህላዊ ክንዉኖችን በዓለም የቅርስ መዝገብ ብቻ ሳይሆን ግጭት በሚበረታባቸዉ የዓለም ሃገራት ባህላዊ ቅርስ በምን ይዞታ ላይ ይገኛል ሲልም ተወያይቶአል። ይህ ዝግጅታችን በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ ስለተዘጋጀዉ ስለ 11ኛዉ የ «UNESCO» የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ጉባዔን ያስቃኛል።
አዲስ አበባ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ የተካሄደዉ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም ማለት የ«UNESCO» የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች የአምስት ቀናት ጉባዔ ከምንጊዜዉም በላይ ደማቅ እንደነበር ተነግሮአል። ኢትዮጵያን ጨምሮ 24 የዩኒስኮ አባል ሃገሮች፤ ሃገራት ይመዝገብልን ብለዉ ያቀረቡዋቸዉን ባህላዊ ቅርሶችን ተመልክተዉና በተለያዩ ሃገራት የሚገኙ የማይዳሰሱ ቅርሶች ላይ ዉይይት አድርገዉ አጽድቀዋል። አዲስ አበባ በሚገኘዉ የተባበሩት መንግሥታት አዳራሽ በተካሄደዉ በዚህ ጉባዔ ንግግርና ዉይይት ብቻ የተካሄደበት ሳይሆን ባህላዊ ክንዉኖችም የታዩበት መድረክም ነዉ ሲሉ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ ተናግረዋል።
«ጉባዔዉ የባህል ጉባዔ ነዉ። የባህል ጉባዔ ሲባል ባህል የሚንፀባረቅበት በንግግር ሃሳብ ብቻ የሚንሸራሸርበት ሳይሆን በተለያየ መንገድ የሚገለፁባቸዉ ነገሮችን አይተናል። ስብሰባዉን ለማዘጋጀት አዲስ አበባችን ከየትኛዉም ቦታ የበለጠ የተካነች መሆንዋ የሚታወቅ ነዉ። ይህ ለመጀመርያ ጊዜ በተዘጋጀዉ የዩኒስኮ ጉባዔ ላይ የተካፈሉትና ከተለያዩ ሃገራት የመጡት ሚኒስትሮች የባህል አምባሳደሮች ፤ እንዲሁም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ከባህል ጋር ቁርኝት ያላቸዉ ሰዎች ነበሩ። ለነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያን የሚያስተዋዉቅ ፕሮግራም ማለት ከባህል ጀምሮ የተለያዩ ኃይማኖቶችን ሁሉ የሚያሳይ ጉባዔዉን ሰዓት በማይነካና በማይጎዳ መልኩ የማስተዋወቅ መረሃ-ግብር ነበር የተያዘዉ። በእዉነቱ የጉባዔዉ ተካፋዮች በዝግጅቱ በጣም እንደተመሰጡ ብዙ እንዳወቁ ነግረዉናል። አሁንም አገራቸዉ ከተመለሱ በኋላ ቪዲዮዉን እንድንልክላቸዉ የሚጠይቁን በርካታ ተሳታፊዎች ናቸዉ።»
ከ 700 በላይ የዉጭ ኃገራት የጉባዔ ተሳታፊዎችና ልዑካን የተገኙበት ብሎም አብዛኞቹ ተሳታፊዎች ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ብሎም ወደ አፍሪቃ መምጣታቸዉን የተናገሩበት ነበር ሲሉ የተናገሩት አቶ ዮናስ ደስታ ጉባዔዉ ከስካሁኖቹ ለየት የሚያደርገዉ እንደ ግጭትና ጦርነት ያሉ ሁኔታዎች የባህላዊ ቅርሶችን ህልውና አደጋ ዉስጥ እየከተተ ስለ መሆኑን በመነጋገሩ ነዉ።
«ጉባዔዉ ላይ ብዙ አጀንዳዎችን አይተናል ፤ ትኩረት ስቦ የነበረዉ ግን አንደኛዉ የቅርስ ምዝገባን የሚመለከተዉ ነዉ፤ ሁለተኛዉ ደግሞ በግጭት ምክንያት ማለትም በሰዉ ሰራሽም ሆነ በተፈጥሮ ሁኔታ በአንድ ቦታም ሆነ ሃገር ግጭቶች በርክቶ፤ ሰዎች ለስደት በሚዳረጉባቸዉ አካባቢዎች ላይ ባህልስ በምን መልኩ ይጎዳል? ይጎዳል ከተባለስ በአግባቡ ሊጠና ይገባል? ሊወሰዱ የሚገባቸዉ ጥንቃቄዎችስ ምንድን ናቸዉ? የሚለዉ ነዉ። ለምሳሌ ሶርያ የዉይይታችን አብነት ሆኖ ቀርቦ ነበር። የሶርያ ሕዝብ 21 ሚሊዮን አካባቢ ይሆናል፤ ከዚህ ሕዝብ መካከል ስምንት ሚሊዮኑ ተሰዶአል፤ በፐርሰንት የምናስቀምጠዉ ከሆነ ደግሞ ከሶርያ ሕዝብ መካከል ከሲሶ በላይ የሚሆነዉ ለስደት ተዳርጎአል። ጦርነት አካባቢዉ ላይ ከሚያስከትለዉ ጉዳት ሌላ ሠዎች በመሰደዳቸዉ ባህላቸዉን እየጣሉ የሌላ አካባቢን ባህል እየተቀበሉና በሌላ ባህል ዉስጥ እየሰመጡ ይሄዳሉ። እነዚህ ተሰዳጆችም ወደሌላ ባህል በመምጣታቸዉ የሚያሳድሩት ጫና ሌላዉ አነጋጋሪ የነበረ ነጥብ ነበር። ይህ እንዴት ይገመገማል በሚለዉ ላይ ጉባዔዉ ተወያይቶአል። የዓለሙ ቅርስ ጥበቃ ተቋም ይህን በተመለከተ የሚወስደዉ ድጋፍ ምንድን ነዉ? ይህ ችግር እንዴት ሊቀረፍ ይችላል የሚለዉንም ጥያቄ አይተናል። በቀጣይ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ጥናት ተደርጎበት ብዙ ነገሮች ይቀርባሉ ብዬም እገምታለሁ»
በጉባዔዉ ላይ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል የተባሉትን ቅርሶች ጨምሮ 49 የተለያዩ የዓለም ሃገራት ቅርሶች ለምዘና ቀርበዉ በሦስት ዘርፎች 33 ቅርሶች በዓለም አቀፉ የቅርስ መዝገብ መስፈራቸዉን በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ ተናግረዋል።
የካሪቢኩን ማሪንጌ፤ የሕንዱን ዮጋ ስፖርት፤ እንዲሁም የደቡብ ኮርያዉ የባህር ዉስጥ የተለየ አሳ አይነት አሰጋገር ዘዴ በዓለም ቅርስነት ከተመዘገቡት ቅርሶች መካከል ታዳሚዉን ያስገረመዉ የኦሮሞ የገዳ ሥርዓት እንደነበር አቶ ዮናስ ደስታ ተናግረዋል።
« አዳላህ አልባል እንጂ የገዳ ስርዓት የጉባዔዉን ታዳሚዎች ቀልብ ስቦ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ያለመግባባት ፋሽን በሆነበት በዚህ ዓለም የገዳ ስርዓትን የመሰለ ማኅበረሰቡ አምኖበት በጣም በብዙ ዓመታት ራሱን ጠብቆ የኖረ ስርዓት የቅርስ አካል ሆኖ መምጣቱ ኢትዮጵያ ዉስጥ እንዲህ ለብዙ ዓመታት የቆየ ባህል አለን? ሲሉ ብዙዎችን ያስገረመና ያስደመመ ነበር። በሌላ በኩል የጉባዔዉ አዲስ አበባ ላይ መሰየም እድልን ፈጥሮ፤ በጉባዔዉ ላይ የሞያ ቅርበት ያለን አካላት ብቻ ሳንሆን አባ ገዳዎች፤ የአገር ሽማግሌዎች ፤ የገዳ ስርዓት በዓለም ቅርስነት ከተመዘገበ በኋላ ያሳዩት እዉነተኛ ስሜት ከግማሽ ሰዓት በላይ የፈጀ ዝግጅት ነበር። በዚሁ አዳራሽ ዉስጥ ይህ ሁሉ ሲሆን የተለያዩ ሃገራት የባህል አምባሳደሮች እና የተለያዩ ሃገራት መልክተኞች የተመለከቱትና ሁሉም የተግባቡበት ሁኔታ ነበር። »
የዩኔስኮ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶችን በመዝገብ ጥበቃ ከጀመረ አሥር ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታትም 43 የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች በአፋጣኝ ድጋፍ ሊደረግላቸው የሚገባ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ሲሆን በአስር ዓመታት ጊዜ ዉስጥ 366 የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ከመላው ዓለም መመዝገባቸዉ ተዘግቦአል። ቅርሶቹን ያስመዘገቡ ሃገሮች የተቋሙን ሕግ በመጠበቅ ድንጋጌዎችን ተግባራዊ ማድረጋቸዉ ይፈተሻል፤ ቅርሶቹን ለመጠበቅ ዩኔስኮ የሚሰጠዉ በጀት የአሰራር ሂደትም እንደሚመዘን ተመልክቶአል።»
ማሪንጌ ቻቻን፤ የሕንዱን ዩጋ፤ እንዲሁም የኦሮሞ ገዳ ስርዓት ዘንድሮ ለአስራ አንደኛ ጊዜ የተካሄደዉ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም (UNESCO) የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ጉባዔ በቅርስነት የመዘገባቸዉ ባህላዊ ክስተቶች ናቸዉ። ባለፉት ዓመታት ጨንበላላና ደመራ በዓለ በዚሁ «ኢንታንጀብል ካልቸራል ሄሪቴጅ» የማይዳሰሱ ባሕላዊ ቅርሶች መዝገብ ዉስጥ የተካተኩ የኢትዮጵያ ባህላዊ ቅርሶች ሲሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንዴ ጀርመን ላይ ለጥቆም በባሕርዳር ከተማ ላይ በርካታ ዓለም አቀፍ ምሁራንን ያሰባሰበዉ የአዝማሪ ጉባዔ፤ የአዝማሪን ምስጢርነት ፤የአዝማሪን አስተማሪነት፤ የአዝማሪን የማኅበረሰብ ጉድፍ ነቃሽነት፤ በጥቂቱ እንደማብራርያ ይዞ በመሰንቆዉ እያዝናና የዩኒስኮዉን የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ጉባዔ ቢጎበኝ በመዝገቡ በመጀመርያነት ለመመዝገቡ ጥርጣሪ ያለ አይመስለንም። ምሁራኑም ቢሆን ሳያስቡበት አልቀሩም። በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ ለሰጡን ቃለ ምልልስ በማመስገን ሙሉዉን መሰናዶ የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።
አዜብ ታደሰ
አርያም ተክሌ