1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምዕራብ ወለጋ ግድያ እንዲቆም የሲቪክ ማሕበራት ማሳሰባቸው

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 8 2015

"በኦሮሚያ ክልል በወለጋ ዞን በዐማራዎች ላይ የሚደረገውን የማያባራ ጭፍጨፋ በመቃወም ድርጊቱን እናወግዛለን።ሌሎች ለፍትሕ የቆሙ ኢትዮጵውያን ፣የዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣የሰብዓዊ መብት ተማጓች ድርጅቶችና መንግሰታትም እንዲያወግዙት ጥሪ አቅርበናል።"

https://p.dw.com/p/4L6Dc
Äthiopien | 200 Zivilisten finden Zuflucht in der orthodoxen Kirche in Addis Abeba
ምስል Solomon Muchie/DW

የስቪክ ማሕበራት የወለጋ ግድያ እንዲቆም ጠየቁ

 በተለያዩ አህጉሮች የሚገኙ የኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሲቪክ ድርጅቶች ተወካይ የሆኑት ዶክተር ሽፈራው ገሠሠ፣ መግለጫውን አስመልክቶ ለዶይቸ ቨለ እንደተናገሩት ፣በወለጋ በንጹሃን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን እጅግ ዘግናኝና አረመኔያዊ ያሉትን ጭፍጨፋ ድርጅቶቹ በጽኑ ያወግዛሉ።

"እንግዲህ መግለጫው የወጣው ሃያ ድርጅቶች ባለፈው እንደምናደርገው፣አንድ ላይ ሆነው ያወጡት መግለጫ ነው።ይኸውም በኦሮሚያ የማያበራ በወለጋ ዐማራዎች ላይ የሚደረገውን ጭፍጨፋ በመቃወም ነው እናወግዛለን።ሌሎች ለፍትሕ የቆሙ ኢትዮጵውያን ፣የዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣የሰብዓዊ መብት ተማጓች ድርጅቶችና መንግሰታትም እንዲያወግዙት ጥሪ አቅርበናል።"

በዚሁ አሰቃቂ ጥቃት ከተገደሉት በተጨማሪ፣ በርካታ ሰዎች አካለ ጎዶሎ ሆነዋል ብለዋል የድርጅቶቹ ተወካይ። ከጭፍጨፋው ለጊዜው የተረፉት ተፈናቅለው፣ወደሌላ ቦታ እንዳይሄዱ መንገድ በመዝጋት፣ምግብና ውሃም ሆነ ህክምና እዳያገኙ በማፈን፣ እዚያው እንዲያልቅ ፍጹም ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት እየተፈጸመ መሆኑን ከጥቃቱ አምልጠው በየጫካ ከተደበቁት ሰዎች ለመረዳት መቻላቸውንም ገልጸውልናል።

ዶክተር ሽፈራው፣ህሊና ያለው ወገን ሁሉ በአንድነት በመቆም ይህን አረመኔያዊ ወንጀል ያሉትን ድርጊት ሊያስቆመው ይገባል ብለዋል። "ኢትዮጵያን ነገዶች ማወቅ ያለባቸው፣አሁን በዐማራው ላይ የሚደረገውን ጭፍጨፋ በቃ ብለው ማቆም መቻል አለባቸው ።ካልሆነ በሁሉም ላይ ይደርሳል።ይሄ አንድ በአንድ የሚሄድ ነገር ነውና ይህንን ማስቆም አንድ ትልቅ ነገር ነው።"

ወንጀለኞችንም ለፍርድ ለማቅረብ የሚያስችል ምርመራ እንዲጀመር  ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራ አሳስበው፣ ያለፍትህ ስለሃገራዊ አንድነትም ሆነ ስለብልጽግና ማሰብ ቅዠት እንደሆነ ድርጅቶቹ በመግለጫቸው ማመልከታቸውንም ተናግረዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ፣የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የህዝብ ጉዳይ ኮሚቴ (ኤፓክ)በበኩሉ በምህራብ ወለጋ የቀጠለው የሰላማዊ ኢትዮጵያውያን ግድያ በመቃወም መግለጫ አውጥቷል። የኮሚቴው የቦርድ አባልና ፀሐፊ አቶ ዮም ፍሰሐ መግለጫውን አስመልክቶ ለዶደ ቨለ ሲናገሩ፣ግድያው በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በጣም ያሳዘነ እና ያሳሳበ መሆኑን ገልጸዋል።

"በውነቱ በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ሰዐት በተለይም በወለጋ በንጹሃን ላይ የሚደረገው፣ግፍና ጭፍጨፋ መሰደድ እኛን ብቻ ሳይሆን በመላው አሜሪካ ያሉ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ በጣም ያሳሰባቸውና ያሳዘናቸው ነገር ነው። ይሄ ዐማሮችን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብዙ ሲገደሉ ነው የቆየው።ይህን ሁላችንም አጥብቀን አውግዘናል።ይሄ ኢሰብዓዊ ድርጊት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመጥን አይደለም።"

መንግስት የበለጠ ጥረት በማድረግ፣በንጹሃን ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት በአስቸኳይ እንዲያስቆም በመግለጫቸው መጠየቃቸውን አቶ ዮም አመልክተዋል። "መንግስት የበለጠ ጥረት እንዲያደርግናይህን ንጹሃን ላይ የሚደረገውን ጭፍጨፋ እንዲቆም ለምን ሃገራችንን ይጎዳታል።ሕዝቡን ይጎዳል ኤኮኖሚውን ይጎዳል።እና ሕዝብን ይከፋፍላል።በውነቱ መንግስትም ብቻ ሳይሆን ሃይማኖት አባቶች ፣ሽማግሌዎች፣አባገዳዎች ይህንን ነገር ማውገዝና ማስቆም አለባቸው።"

ታሪኩ ሃይሉ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር