አርዕስተ ዜና
*በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ በሚገኙ የዛይሴ ማኅበረሰብ አባላት ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ የዘፈቀደ እሥርና ወከባ ይፈጸማል ሲሉ ነዋሪዎችና የሕዝብ እንደራሴ ምክር ቤት አባላት ተናገሩ ።
*ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ 50 ሺህ ግድም ትምህርት ቤቶች አብዛኛዎቹ የትምህርት መሰረተ ልማትና ግብዓት እንደሌላቸው ተገለጠ ።
የኬንያ ፕሬዚደንት ዊልያም ሩቱ ከሐገሪቱ ወጣቶች በደረሰባቸው ብርቱ ተቃውሞ ምክንያት፣ የሀገሪቱ ምክር ቤት አርቅቆ ያቀረበላቸው የታክስ ጭማሪ አዋጅ ላይ እንደማይፈርሙ ዛሬ ይፋ አደረጉ ።
*የጀርመን መንግሥት ካቢኔ አሸባሪነትን የሚያወድሱ ከጀርመን ይባረሩ የሚለውን ረቂቅ ሕግ አወደሰ ። ሕጉ ተግባራዊ ከሆነ የውጭ ሃገራት ዜጎች ወደ ትውልድ ሀገራቸው እንዳይባረሩ አስቸጋሪ ሆኖ የቆየውን መስናከል ያጠራል ተብሏል ።
ዜናው በዝርዝር
ባሕርዳር፥ ኢትዮጵያ ከ50 ሺህ ግድም ትምህርት ቤቶች አብዛኛዎቹ የግብዓት ችግር ገጥሟቸዋል
ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ 50 ሺህ ግድም ትምህርት ቤቶች አብዛኛዎቹ የትምህርት መሰረተ ልማትና ግብዓት እንደሌላቸው የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ዐስታወቀ ። በአማራ ክልል ደግሞ በክልሉ ባለው የፀጥታ እጦት 3 ሺህ ትምህርት ቤቶች በዚህ ዓመት አልተከፈቱም ተብሏል ። ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ደግሞ ወደ ትምህርት ቤት አለመግባታቸው ተገልጧል ። የአማራ ክልል «የትምህርት ንቅናቄ » በሚል ያዘጋጀው መድረክ ዛሬ ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ሲጀመር የተገኙት የኢፌድሪ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ የትምህርት ጥራት በተለያዩ ምክንያቶች ማሽቆልቆሉን ተናግረዋል ።
«በሀገራችን ከ50ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አብዛኛዎቹ የመማር ማስተማር መሰረተ ልማቶች የሌሏቸው በመሆኑ ተማሪዎች በተጓደለ የትምህርት ሁኔታ ውስጥ እንዲማሩ ተደርጓል፣ ይህ ደግሞ በትምህርት ትራት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል።»
በአማራ ክልል በዚህ ዓመት በተሰጠው የ6ኛና 8ኛ ክፍል አጠቃላይ ፈተና ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት በምዕራብ ጎጃምና ምስራቅ ጎጀም ተማሪዎች ፈተና እንዳልወሰዱ ቀደም ሲል የተዘግቧል ። ዜናውን የላከልን ዓለምነው መኮንን ነው፤ በዜና መጽሄት ዝርዝር ዘገባ ይኖረናል ።
ሐዋሳ፥የዛይሴ ማኅበረሰብ አባላት ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ የዘፈቀደ እሥርና ወከባ ይፈጸማል ተባለ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ በሚገኙ የዛይሴ ማኅበረሰብ አባላት ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ የዘፈቀደ እሥርና ወከባ ይፈጸማል ሲሉ ነዋሪዎችና የሕዝብ እንደራሴ ምክር ቤት አባላት ገለፁ ፡፡ የዞኑና የወረዳው የፀጥታ አባላት ሰሞኑን በሌሊት ቤት ለቤት በመዘዋወር ወጣቶች ፣ ሴቶች እና ቀሳውስትን ጨምሮ 112 የማኅበረሰቡ አባላትን ይዘው ማሠራቸውን ነዋሪዎቹና የእንደራሴ ምክር ቤቱ አባላቱ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል ። የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት የዘፈቀደ እሥርና ወከባው እየተፈጸመ የሚገኘው በወረዳው ዛይሴ ደንብሌ ፣ ዛይሴ ኤልጎ እና ዛይሴ ወዘቃ በተባሉ የገጠር ቀበሌያት ውስጥ ነው ፡፡ ዶቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ምላሽ ለማግኘት ለጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባይነህ አበራ ቢደውልም ስብሰባ ላይ በመሆናቸው ማናገር እንደማይችሉ ገልጸዋል ፡፡ ዋና አስተዳዳሪው በእጅ ሥልካቸው አጭር የጹሑፍ መልዕክት ቢላክላቸውም መልስ ሳይሰጡ ቀርተዋል ፡፡ ዜናውን የላከልን የሐዋሳው ወኪላችን ሸዋንግዛው ወጋየሁ ነው ። በዜና መጽሄት ተጨማሪ ይኖረናል ።
ናይሮቢ፦የኬንያ ፕሬዚደንት ዊልያም ሩቱ ደረሰባቸው ብርሩ ተቃውሞ ረቂቅ አዋጅ ላይ አይፈርሙም
የኬንያ ፕሬዚደንት ዊልያም ሩቱ ከሐገሪቱ ወጣቶች በደረሰባቸው ብርቱ ተቃውሞ ምክንያት፣ የሀገሪቱ ምክር ቤት አርቅቆ ያቀረበላቸውን የታክስ ጭማሪ አዋጅ ላይ እንደማይፈርሙ ዛሬ ይፋ አደረጉ ። አዋጁን በመቃወም በኬንያ ባለፉት ቀናት ተከታታይ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሁደዋል ። ፕሬዚደንቱ ተቃዋሚዎች ትናንት ወደ ምክር ቤቱ ከተመሙ እና በርካታ ሰዎች በጥይት ከተገደሉ ከአንድ ቀን በኋላ ዛሬ አዋጁ ላይ እንደማይፈርሙ ይፋ አድርገዋል። ከማክሰኞ ብጥብጥ በኋላ ፕሬዚደንቱ የተቃውሞ ሰልፈኞችን «የሀገር ከጂዎች» ሲሉ በብርቱ ወቅሰዋል ። ዛሬ ደግሞ አዋጁን «በብዙ አካባቢዎች አለመርካት በማስከተሉ» ምክንያት ሲሉ የተቃውሞ ድምፁን መስማታቸው ተናግረዋል። ብርቱ ተቃውሞአቸውን በነገው ዕለትም ሊገፉበት ቀጠሮ የያዙት የኬንያ ወጣቶች ግን የሩቶን ሐሳብ «ለሕዝብ ግኑኝነት የታለመ ማዘናጊያ» በማለት ውድቅ አድርገውታል። የታክስ ጭማሪውን በመቃወም ሰልፍ በወጡ ላይ ትላንት ፖሊስ በወሰደው የኃይል ርምጃ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ13 እስከ18 ይደርሳል ተብሎ ነበር። አሁን የወጡ ዘገባዎች ደግሞ የሟቾች ቁጥር ቢያንስ 22 እንደደደረሰ ይጠቁማል ።
ዘሄግ፥የማሊ አማጺያን መሪ አል ሐሰን ማህሙድ በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ወንጀለኛ ተባሉ
የማሊ አማጺያን መሪ አል ሐሰን ማህሙድ የሰብአዊነት ወንጀሎችን ፈጽመዋል ሲል ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት ዛሬ ጥፋተኛ ሲል ወሰነ ። አል ሐሰን ከአልቃይዳ ጋ ግንኙነት አለው በተባለው አንሳር ዲኔ የሽብር ቡድን መሪነታቸው ወቅት ፈጸሙት ለተባለው ወንጀል በሌላ ቀን ፍርድ እንደሚሰጥባቸው ተዘግቧል ። ፈጽመውታል የተባለው ወንጀል ግን እስከ ዕድሜ ልክ እስራት የሚያስቀጣ መሆኑም ተዘግቧል ። አል ሐሰን የተከሰሱበት ወንጀል ተፈመ የተባለው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2012 አንሳር ዲኔ ታጣቂ ቡድን የማሊ ጥንታዊቷ ከተማ ቲንቡክቱን ባወደመበት ወቅት ነው ።
ቤርሊን፥ ጀርመን አሸባሪነትን የሚያወድሱ ከሀገር ይባረራሉ ተባለ
የጀርመን ካቢኔ አሸባሪነትን የሚያወድሱ የዉጪ ሐገር ዜጎች ከጀርመን ይባረሩ የሚለውን ረቂቅ ሕግ ተቀበለ ። የጀርመን መንግሥት በሕግ አርቃቂዎች የቀረበለት «የአሸባሪነት ወንጀልን» የሚያበረታቱ ወደ ሀገራቸው ይሰናበቱ የሚለው ረቂቅ ሕግ ላይ ዛሬ ተስማምቷል ። ሕጉ ተግባራዊ ከሆነ የውጭ ሃገራት ዜጎች ወደ ትውልድ ሀገራቸው እንዳይባረሩ አስቸጋሪ ሆኖ የቆየውን መስናከል ያስወግዳል ተብሏል ። ጀርመን ይህን ሕግ ያረቀቀችው፦ እስራኤልና ምዕራባዉያን መንግስታት በአሸባሪነት የፈረጁት የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሐማስ እስራኤል ላይ ያደረሰውን ጥቃት እና ሌሎች የሽብር ተግባራትን ለሚያወድሱ የበይነ መረብ ጽሑፎች አጸፌታ ለመስጠት ነው ተብሏል ። በአዲሱ ረቂቅ ሕግ አንድ ሰው አንዳችም የወንጀል ክስ ባይኖርበት እንኳ ለሽብር ተግባርን አንዴም ቢሆን ድጋፍ ካሳየ ከሀገር እንዲባረር ሥልጣን ይሰጣል ።ይሁንና እንደ ዩቲዩብ፤ ኢንስታግራም እና ቲክቶክ ባሉ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ላይ የቀረቡ የጥላቻ ጽሑፎችን የመውደድ (like) ወይንም ሌላ የድጋፍ ምልክት ማኖር ከጀርመን ለመባረር በቂ አይደለም ተብሏል ።
ብራስልስ፥ ናቶ አዲስ ዋና ጸሐፊ ሾመ
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) የኔዘርላንድ ተሰናባቹ ጠቅላይ ሚንስትርን ቀጣዩ ዋና ጸሐፊ አድርጎ ሾመ ። ጠቅላይ ሚንስትር ማርክ ሩተ በዋና ጸሐፊነት የተመረጡት ብቸኛው ተፎካካሪያቸው የነበሩት የሮማኒያ ፕሬዚደንት ክላውስ ሎሀኒስ ከውድድሩ መውጣታቸውን ካሳወቁ በኋላ ነው ። ኔዘርላንዳዊው ፖለቲከኛ ለከፍተኛው ኃላፊነት የተመረጡት የሩስያና የዩክሬን ጦርነት በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት ኔቶም ሆነ አባላቱ መዘዙን መጋፈጣቸው የማይቀር ነው በተባለበት ወቅት ነው ። የኔቶ ዋና ጸሐፊ ዬንስ ስቶልተንበርግም በቅርቡ የሚተኳቸው ኔዘርላንዳዊም የኔቶን ዓላማ በማስፈጸም «ጠንካራ መሪ» ናቸው ሲሉ አወድሰዋቸዋል ። የሩስያ ዩክሬን ጦርነት የናቶ ዐቢይ ጉዳይ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተውበታል ።
«የዩክሬን የወደፊት እጣ ፈንታ በዩሮ አትላንቲክ ቤተሰብ እጅ ላይ ነው ። የዩክሬን እጣ በናቶ የሚወሰን ነው ። በዚያ ላይ ሁሉም አጋሮች ይስማማሉ ።»
የኔዘርላንድ ተሰናባቹ ጠቅላይ ሚንስትር የናቶ ሹመትን በተመለከተ ሩስያ በበኩሏ ማርክ ሩተ ወደ ኃላፊነቱ መምጣታቸው የናቶ «አጠቃላይ መስመር» ላይ የሚቀየር ነገር የሚኖር አይመስልም ብላለች ። ከዐሥር ዓመት በላይ የናቶ ዋና ጸሐፊ ዬንስ ሆነው ያገለገሉት ኖርዌጂያዊው ዬንስ ስቶልተንበርግ የፊታችን መስከረም 21 ለአዲሱ ዋና ሐፊ ሥልጣናቸውን ያስረክባሉ ።
17ኛው የአውሮጳ እግር ኳስ ዛሬም ቀጥሏል
በጀርመን አዘጋጅነት የጀመረው 17ኛው የአውሮጳ እግር ኳስ ጨዋታ ዛሬም ቀጥሎ ምሽቱን አራት ግጥሚያዎች ይኖራሉ ። ወደ 16ቱ የጥሎ ማለፍ ዙር ለማለፍ በሚደረጉ የምሽቱ የመጨረሻ ጨዋታዎች፦ ስሎቫኪያ ከሩማንያ እንዲሁም ዩክሬን ከቤልጂየም ጋር እየተጋጠሙ ነው ። ከሰአታት በኋላ ደግሞ ጂዮርጂያ ከፖርቹጋል እንዲሁም ቼክ ከቱርክ ጋ ከተጋጠሙ በኋላ ወደ ቀጣይ ዙር ያለፉት 16ቱ አጠቃላይ ቡድኖች ይለያሉ ። ከዛሬ ግጥሚያዎች በምድብ «ሠ» የሚገኙት አራቱም ሃገራት፦ ማለትም ሮማኒያ፤ ቤልጂየም፤ ስሎቫኪያ እና ዩክሬን እያንዳንዳቸው ሦስት ነጥብ ያላቸው መሆኑ ጨዋታውን እጅግ አጓጊ አድርጎታል ። ከምድብ «ረ» ፖርቹጋል በ6 ነጥብ ትመራለች ። ሩርክ በ3 ነጥብ ትከተላለች ። ቼክ እና ጆርጂያ አንድ ነጥብ አላቸው የሚለያዩት በግብ ክፍያ ነው ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ