1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የራስ ገዝዋ ሶማሊላንድ የፕሬዝዳንት ሥልጣን ርክክብ ድባብ ምን ይመስል ነበር?

ሰለሞን ሙጬ
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 4 2017

ጤና ይስጥልኝ አድማጮቻችን እንደምን አመሻችሁ። በዛሬው ሥርጭታችን ኂሩት መለሰ የዓለም ዜና ታቀርብልናለች። እኔ አዜብ ታደሰ ደግሞ የአንድ ሰዓቱን ዝግጅታችንን እየመራሁ እስከ ፍጻሜው አብሬያችሁ እዘልቃለሁ ። አብራችሁን ቆዩ

https://p.dw.com/p/4o6vi
የሶማሌላንድ የስልጣን ርክክብ 12.12.2024
የሶማሌላንድ የስልጣን ርክክብ 12.12.2024ምስል Solomon Muche/DW

ሶማሌላንድ "የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ስምምነት የእኛ ጉዳይ አይደለም"

የራስ ገዝ ሶማሊላንድ የፕሬዝዳንት ሥልጣን ርክክብ ድባብ ምን ይመስል ነበር?

የራስ ገዟ ሶማሊላንድ ስድስተኛ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት አብዲራሕማን ሞሐመድ አብዱላሂ ትናንት ቃለ መሀላ ፈጸመው ከተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ሥልጣን ተረክበዋል። ራሷን እንደ ሉዓላዊ ሀገር ቆጥራ የምትንቀሳቀሰው "ሶማሊላንድ ሪፐብሊክ" ከየትኛውም ሀገር ይሁን ተቋም እውቅና ባታገኝም ሰላማዊ የምርጫ ሂደት እና የሥልጣን ርክክብበማድረግ ረገድ ግን በአፍሪካ ተምሳሌት መሆን ችላለች። በትናንቱ የሥልጣን ርክክብ ወቅት አሸናፊ እና ተሸነፊ የሆኑት ፕሬዝዳንቶች ላይ ይታይ የነበረው የደስታ ድባብ ነበር። የስልጣን ርክክቡም ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ አልፏል። ተሰናባቹ የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቤሂ በበዓለ ሲመቱ ላይ የሥነ ሥርዓቱን ታዳሚዎች ሲያስቁ፣ ሲያስደስቱ እና የመሸነፍ ስሜት ሳይታይባቸው ኹነቱን በአግባቡ መርተዋል። ከአዲሱ ፕሬዝዳንት አብዱራህማን ሞሀመድ ጋርም ሲተቃቀፉ፣ ሲጨባበጡ ነበር የታዩት። ከተለያየ ሀገር ለዚሁ ሥነ ሥርዓት ወደ ሀርጌሳ የሄዱ የሶማሊላንድ ሰዎች አንድ ነገር ደጋግመው ሲናገሩም ለማስተዋል ችያለሁ። ይህም "ዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ርክክብ ባህላችን ነው" የሚለው ነው። ከዚህ በተጨማሪ ከፍተኛ የፀጥታ ጥበቃ በሚደረግበት እንዲህ ያለው ትልቅ ሥነ ሥርዓት ላይ የፀጥታ አስከባሪዎችን እና ወታደሮችን ማየት የተለመደ ቢሆንም ነዋሪዎን በሚረብሽ እና ለፍርሃት በሚዳርግ ሁኔታ ከመጠን ያለፈ የጦር መሣሪያ የታጠቀ ኃይል በሥነ ሥርዓቱ ማክበሪያ ስፍራ አይታይም ነበር።

የሶማሌላንድ የስልጣን ርክክብ 12.12.2024
የሶማሌላንድ የስልጣን ርክክብ 12.12.2024ምስል Solomon Muche/DW

ከሥነ ሥርዓቱ በኋላ የከተማው ድባብ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ ከሥነ ሥርዓቱ መጠናቀቅ በኋላ ሀርጌሳ ከተማን ተዘዋውሬ ተመልክቼ ነበር። ትናንት ሀሙስ እስከ ምሽት 3 ሰዓት ገደማ ከጓደኞቼ ጋር የሀርጌሳን ዋና ዋና የከተማዋ ክፍል በእግር ለመመልከት ችያለሁ። በዚህም መደበኛ የዘወትር ሕይወት ሲቀጥል ለማስተዋል ችያለሁ። ዋና ዋና የንግድ ተቋማትት፣ ሆቴሌች፣ ሱቆች፣ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ፣ የጎዳና ላይ ንግዶች እንደወትሮው ሁሉ በዚሁ የፕሬዝዳንት ሥልጣን ርክክብ በተደረገበት ዕለት መደበኛ ሆኖ ሲቀጥል ተመልክቻለሁ። በማግስቱ ዛሬ ማለዳም ምንም እንኳን ዕለቱ አርብ በመሆኑ የንግድ ተቋማትን በጥዋቱ የመክፈት ልማድ በሀገሩ ባይኖርም ከረፋድ ጀምሮ ግን መደበኛው የዘወትር የሥራ እንቅስቃሴ እንደነበር ለመመልከት ችያለሁ። 

በስልጣን ላይ የነበረው ፓርቲ ውጤቱን እንዴት ተቀበለው? 

የሶማሌላንድ የስልጣን ርክክብ 12.12.2024
የሶማሌላንድ የስልጣን ርክክብ 12.12.2024ምስል Solomon Muche/DW

በዚህ የሥልጣን ርክክብ ሥነ ሥርዓት ላይ ብዙ የውጭ ሀገራት ተወካዮች፣ የግዙፍ ተቋማት ተወካዬች፣ የDP World ተቋም የሥራ መሪዎች ተገኝተው ነበር። በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት በሶማሊያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሪቻርድ ራይሊ "የሶማሌላንድ ሕዝብ ለዚህ ቀጣና ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ እና ለዓለም የእውነተኛ ዲሞክራሲ ስርዓት ምሳሌ ሰጥቷል" በማለት ሀገራቸው ለወደፊትም ከጎናቸው እንደምትሆን የፕሬዝዳንት ጆሴፍ ባይደን ያሉትን መልዕክት አስተላልፈዋል። በአንፃሩ ጅቡቲ በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ አልተጋበዘችም፣ ታይዋን ግን የምርጫውን ሂደትም፣ የርክክብ ሥነ ሥርዓቱንም ደግፋለች አግዛለችም። 

3 የፖለቲካ ፓርቲዎች በዋና ተፎካካሪነት ያሏት ሶማሊላንድ ገዢ የነበረው ፓርቲ ተሸንፎ አሁን ደረጃው ዝቅ ብሎ ሶስተኛ ሆኗል። የቀድሞ የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ እና አሁን የተሸነፈው ፓርቲ እና መንግሥት ደጋፊ የነበሩ ሰው ለዶቼ ቬለ ዛሬ ጥዋት ሀርጌሳ ውስጥ ባለው መንሱር ሆቴል ውስጥ በሰጡት ቃለ ምልልስ "ተሸንፈናል" ሲሉ የምርጫው ውጤትም፣ ሁኔታውም እንደገረማቸው በግልጽ ተናግረዋል። "ሕዝቡ መርጧል፣ ያንንም ተቀብለናል" ሲሉ መልሰዋል። 

"የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ስምምነት የእኛ ጉዳይ አይደለም"

በአፍሪካ ሕብረት እና ኢጋድ የሶማሊላንድ ልዩ መልእክተኛ የሆኑት አምባሳደር አብዱላሂ ሞሐመድ በሶማሊላንድ ጉዳይ እድሜ ልካቸውን የሠሩ ናቸው። እኒሁ ሰው ከዚህ ቀደም ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ስምምነት አስመልክቶ ዶቼ ቬለ ሶማሊላንድከኢትዮጵያ እውቅና አገኘችማለት ነውን? በሚል ላቀረበላቸው ጥያቄ "ሶማሊላንድ እስካሁን በኢትዮጵያ እውቅና አልተሰጣትም። ነገር ግን እንደሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የሶማሊላንድን እውቅና ከኢትዮጵያ እንጠብቃለን" ብለው ነበር። ረቡዕ ዕለት በቱርክ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን አሸማጋይነት አንካራ ውስጥ በተደረገው የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ግንኙነት ሁለቱ ሀገራት ስምምነት ላይ መድረሳቸው እና ወደ ሰላም ለመምጣት አቋም መያዛቸው ተነግሯል። ይህ ለሶማሊላንድ ምን ማለት ነው? ብለን ጠይቀናቸው ነበር። 

የሶማሌላንድ የስልጣን ርክክብ 12.12.2024
የሶማሌላንድ የስልጣን ርክክብ 12.12.2024ምስል Solomon Muche/DW

"ይህ የተለየ ጉዳይ ነው" በማለት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እና ስምምነት ሶማሊላንድን እንደማይመለከታት ገልፀዋል። የመግባቢያ ስምምነቱ በሁለቱ ሀገራት ሕግ አውጪዎች ይፀድቃል የሚል ተስፋ ይዘው በነበሩበት ወቅት አዲስ አስተዳደር በሶማሊላንድ መምጣቱን የሚገልፁት እኒሁ ሰው ይህንን የተመለከተው ሰነድ ለአዲሱ ፕሬዝዳንት እንደቀረበላቸው እና እንደተሰጣቸውም ገልፀዋል። እንደ እሳቸው አባባል "ሂደቱ ይቀጥላል ብለን ነው፣ ይህም ይተገበራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ሲሉ መልሰዋል። የመግባቢያ ስምምነቱንም ሶማሊላንድ እስካሁን ካከናወነቻቸው ሥራዎች ሁሉ መሠረታዊ ሊባል የሚችል መሆኑን ገልፀዋል።

 

ሰለሞን ሙጬ 

አዜብ ታደሰ 

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር