1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰላም ስምምነቱ ተስፋና ጥርጣሬ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 24 2015

ጉዳዩን የምመለከተው እንደ ሴት ነው ጦርነትን በጣም አልደግፍም፣ እንደዚሁም ተከትለውት የሚመጡትን ውጤቶችን ደግሞ በጣም እቃወማለሁ፣ ከዛ አንፃር ትናንትና የተደረገው ስምምነት የሴቶችንና የሕጻናትን ስቃይ ያቆማል ዘላቂ መፍትሔ ይሆናል ብየም አስባለሁ፣ ከዛ አንፃር ስምምነቱን እደግፋለሁ፡፡»

https://p.dw.com/p/4J1b7
Äthiopien Bahirdar Covid19
ምስል DW/A. Mekonnen

የሰላም ስምምነቱ ተስፋና ጥርጣሬ

የኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ልዑካን ትናንት ደቡብ አፍሪካ ላይ የፈጸሙት የሰላም ስምምነት በኢትዮጵያ ተጨማሪ ሰብአዊና ቁሳዊ እልቂትን ይታደጋል ሲሉ የአፋርና የአማራ ክልል ነዋሪዎች ተናገሩ። አንዳንዶች ደግሞ የወልቃይትንና ራያ አካባቢዎችን ጥያቄ ለመፍታት የተቀመጠው ሀሳብ ያልተብራራ ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡ 
በኢትዮጵያ ኃይሎችና በህወሓት መካከል የተጀመረው የሰሜኑ ጦርነት የበርካቶችን ህይወት ነጥቆ፣ ብዙዎችን ለአካል ጉዳት ዳርጎና በሚሊዮን የሚቆጠሩትን አፈናቅሎና አጎሳቁሎ ዛሬ ድፍን ሁለት ዓመት ሞልቶታል፡፡ ለዚህ ጦርነት እልባት ለመስጠት በአፍሪካ ኅብረት ሸምጋይነት የሁለቱ ኃይሎች ተወካዮች በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ ለ9 ቀናት ያህል ያደረጉትን ውይይት ትናንት ሲያጠናቅቁ የተኩስ አቁም ስምምነቶችን ጨምሮ ሌሎች ውሳኔዎችንም አሳልፈዋል፡፡ 
ስምምነቶቹን በተመለከተ የአማራና የአፋር ነዋሪዎችን አስተያየት ጠይቀናል፡፡ 
ወ/ሮ ቅድስት ቸርነት የተባሉ አስተያየት ሰጪ የጦርነቱ መቆም ለሕጻናትና እናቶች እፎይታን የሚሰጥ በመሆኑ ለስምምነቱ ድጋፋቸውን ገልፀዋል፡፡ 
«ጉዳዩን የምመለከተው እንደ ሴት ነው ጦርነትን በጣም አልደግፍም፣ እንደዚሁም ተከትለውት የሚመጡትን ውጤቶችን ደግሞ በጣም እቃወማለሁ፣ ከዛ አንፃር ትናንትና የተደረገው ስምምነት የሴቶችንና የሕጻናትን ስቃይ ያቆማል ዘላቂ መፍትሔ ይሆናል ብየም አስባለሁ፣ ከዛ አንፃር (ስምምነቱን) እደግፋለሁ፡፡» 
መላከ ሰላም ባሕሩ የተባሉ አባት እንደተናገሩት ደግሞ ከጦርነት የሚገኝ ትርፍ የለምና ስምምነቱ መልካም ዜና ነው፡፡ 
«ሰው የሆነ ሰው ሁሉ እንዲሞት ሳይሆን በሰላም እንዲኖር ነው የምንለምነው፣ የምንመኘውም፣ ምኞታችንም ይህ ስለሆነ፣ አሁን ላይ እየኖርን ነው ወይ ስንል እየኖርን አይደለም ኑሯችን በስጋት ተዋጠ ነው፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ ደግሞ ሰላም እየመጣ ነው እርቅ እየሆነ ነው የሚባል መስማት ሰው ለሆነ ሁሉ እጅግ የሚያስደስት ነው፣ ይህ እንዲቀጥል፣ በቃችሁ እንዲለን ጦርነት 2015 ዓ ም በቂ ሆኖ መከራ ሳይሆን ሰላም፣ አንድነት የምንሰማበት መለያየት ጠፍቶ አንድ ሆነዋል የሚባልበትን የምናይና የምንሰማበት ዘመን እንዲሆን ነው ሁላችን የምንመኘው፤ የእውነት እንዲሆንልን አብዝተን እንጸልይ፡፡» 
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶ/ር በቃሉ ታረቀኝ በበኩላቸው በስምምነቱ ደስተኛ መሆናቸውን ጠቁመው ስለወልቃትና ራያ የተነገረው ያልተብራራና ጥያቄ የሚያስነሳ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ 
«… ወደ ድርድሩ ከመጣን ድርድሩ የተደረገበት ሁኔታ፣ በጣም ዝግ ነው ። የአማራ ትልቁ የችግሩ መነሻ የወልቃይትና የራያ ጉዳይ በጣም ቀይ መስመሮች ናቸው፣ አሁን በዚህ በድርድሩ ላይ አንቀጽ 10፣ 4 ላይ ያለው ግልፅነት የጎደለው አንድ የመደራደሪያ ሀሳብ ተቀምጧል፣ ግጭት ቀጠና በሆኑ አካባቢዎች ላይ «ሕገመንግሥታዊ በሆነ መልኩ ይፈታል» የሚል፣ አሱ በራሱ አወዛጋቢና ምናልባትም ወገኖቻችን የከፈሉትን ዋጋ ላለመስጠት መስሎ ይታየኛል፣ ስምምነቱ ምንም ጥያቄ የለውም እንደግለሰብም የምደግፈው ነው፡፡»
 
አቶ ግዛቸው ጥላሁን የተባሉ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ስምምነቱ ለትግራይ ህዝብ አስፈላጊ የሆኑ እርዳታዎች እንዲደርሱት ያደርጋል ነው ያሉት፣ ግን አንዳንድ ጉዳዮች ብስምምነቱ በግልፅ አልተብራሩም ሲሉ አስረድተዋል፡፡ 
«ያላረፈደ ነገር ስለሆነ ትናንት በተደረገው የሰላም ድርድር በጣም ደስተኛ ነኝ፣ ህወሓት ትጥቅ መፍታት አለበት፣ ለትግራይ ህዝብ የሚያስፈልገው እርዳታ መድረስ አለበት፣ ሰላም መረጋገጥ አለበት፣ ሌሎች ጉዳዮች አማራውን ማዕከል ያደረጉ፣ ለዚህ ሁሉ ጦርነት ለዚህ ሁሉ ችግር ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን በተመለከተ ግን በግልፅ አልሰማንም፣ የወልቃት ጉዳይ አለ፣ የራያ ጉዳይ አለ፣ ለብዙ ህዝብ ሞት ምክንያት መንስኤ የሆነ የዚህ መሬት ጉዳይ በጣም ዋና ጉዳይ ነው ብዬ አምናለሁ ለአማራ ህዝብ፡፡»
 
አቶ አህመድ ያዮ የተባሉ የአፋር ክልል ነዋሪ ጦርነቱ በሁለቱም ወገኖች በርካታ ጥፋቶችን ማስከተሉን አስታውሰው የተኩስ አቁሙ በተለይ ለአጎራባች ክልሎች ሰላም መስፈን ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል፡፡ 

«በነርሱም (ህወሓት) ብዙ ኪሳራ ያደረሰባቸው ጦርነት ነው። ህዝብ የማስጨረስ ሥራ ነው የተሠራው፣ አሁንም ችግር ካለ አማራና አፋር ነው የሚጎዳው፣ እርቁ ለእኛም ጥሩ ነው የተጎዳው ተጎድቷል ከእኛም ከነሱም ያው የአንድ አገር ዜጋ እስከሆንክ ድረስ ለትግራይ ህዝብ እንኳ የማያስብ ቡድን ነው እና ትጥቅ ፈትቶ ወደ ሰላም እመጣለሁ ካለ ይህ ጥሩ ነገር ይመስለኛል በተግባር መሬት ላይ ወርዶ ከተሠራበት፡፡ »
 
ግርማው አሸብር የተባሉ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካውያን መፍታት መጀመራቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ከ2013 ዓ ም ጀምሮ በበርካታ የአፋር፣ የአማራና የትግራይ ክልሎች ነዋሪዎች በርካታ ማኅበራዊ፣ ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ መመሳቀሎች ደርሰዋል፡፡ 
ዓለምነው መኮንን 
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ሸዋዬ ለገሠ