የሲቪል ማኅበረሰብ ምህዳር የመዳከም ሥጋት
ረቡዕ፣ ጥቅምት 20 2017በሲቪል ማኅበረሰብ እና ግለሰቦች ነፃነት ላይ የሚደረጉ «ስልታዊ አፈናዎች» በሀገሪቱ ላይ የሚደረጉ የዴሞክራሲ ጥረቶች ላይ ከፍተኛ ሥጋት መጋረጣቸው ተገለፀ ። ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የሕግ ማዕቀፎች ላይ የተወሰኑ ያላቸው ማሻሻያዎች ቢደረግም የኢትዮጲያ ሲቪል ማኅበራት ከፍተኛ ጫና እየገጠማቸው መሆኑን የዴሞክራሲ እና ዕድገት ማዕከል (CARD) ዐሳውቋል ። «የሲቪል ማኅበራት እና ነፃ ድምፆች እየታፈኑ፣ የዲሞክራሲ ዕድገት እና የዜጎች ተሳትፎ እየተዳከመ» መምጣቱን ያመለከተው ካርድ፤ ከ2012 ዓ.ም ወዲህ 54 የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች በደረሰባቸው እንግልት ምክንያት ከሀገር ለመሰደድ ስለመገደዳቸውንም ጠቅሷል። ሰለሞን ሙጬ ከአዲስ አበባ ተጨማሪ አለው ።
የዲሞክራሲ እና ዕድገት ማዕከል (CARD) የፖለቲካ ልዩነትን አለማቻቻል፣ የደህንነት ዋስትና አለመኖር እና የተረጋጋ የፋይናንስ አቅም አለመገንባት የሲቪክ ተቋማቱ በሙሉ አቅማቸው ስለ ሰብዓዊ መብቶች፣ ስለ ሰላም ግንባታ እና ስለ ዲሞክራሲ እንዳይሰሩ እንቅፋት ሆኗል ብሏል።
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ሞገስ ደምሴ ለዶቼ ቬለ እንዳሉት የአለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ ሁኔታዎች ተዳምረው ይህንን ችግር እያስከተሉ ነው። "በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ግጭት መሠረት አድርጎ የሲቪክ ምህዳሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበበ መጥቷልየሚል ግምገማ ነው ያለው"
"ደህንነቱ የተጠበቀ የሲቪክ ምህዳር እንዲፈጠር ለመሟገት ካርድን ይቀላቀሉ" በሚል ዘመቻ እያከናወነ ያለው ይሄው የመብት እና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ላይ የሚሰራው ሲቪል ድርጅት ያወጣው ግምገማ በሌሎች መሰል ድርጅቶች እንዴት ይታያል የሚለውን የተጠየቁት የቪዥን ኢትዮጵያ ኮንግረስ ዋና ዳይሬክተር ተከታዩን ብለዋል።
"ሀገራችሁ ውስጥ ሰላም የለም የሚሉ ለጋሾች ተፈጥረዋል"
ካርድ እንደሚለው ኢትዮጵያ በ2016 ዓ . ም የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት መጠቆሚያ ላይ ከ 180 ሀገራት 141 ኛ ላይ ተቀምጣለች። ከ 2012 ዓ. ም ጀምሮ ደግሞ 54 የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች በደረሰባቸው እንግልት ምክንያት ከሀገር ለመሰደድ ተገደዋል። ይህ የሥራው እንቅፋት ግልጽ ማሳያ መሆኑንም ዶክተር ሞገስ ገልፀዋል።
"በአብዛኛው ብቅ ጥልቅ የሚል ያልተቀናጀ ፣ ያልተደራጀ አይነት ውትወታ እና የጉትጎታ ሥራዎች ናቸው የሚኖሩት እና እነዚህ ደግሞ ብዙም ተጽእኖ ሊያመጡ ይችላሉ የሚል እምነት የለንም"
በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምላሽ ለማግኘት ያደረግኹት ጥረት ለጊዜው አልተሳካም። ባለስልጣኑ ግን ዳግም ምዝገባ ያላደረጉ ያላቸውን ከ አንድ ሺህ በላይ እና ህልውናቸውን አላረጋገጡም ያላቸውን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለፈው ዓመት መሰረዙ ይታወሳል። አቶ ታደለ ይህንን ያስታውሳሉ።
"ጠንካራ ሲቪክ ማህበር ቢኖረን የውትወታ እና የማሳመን ሥራ ይሠራ ነበር። ይህን መሥራት አልቻልንም። አስታራቂም እኮ መሆን ነበረብን"
በሲቪል ማህበረሰቡ እንዲሁም በግለሰብ ነፃነት የሚደረጉ "ስልታዊ" ያላቸው አፈናዎች በሀገሪቱ ላይ የሚደረጉ የዴሞክራሲ ጥረቶች ላይ ከፍተኛ ሥጋት ጋርጠዋል ያለው ካርድ "ሊዘነጉ የማይገባ እውነታዎች" በማለት ባወጣቸው መረጃዎች "ከ2011 ዓ. ም ጀምሮ ከ 200 ጋዜጠኞች በላይ ታስረዋል፣ ይህም ነፃ የሆኑ መገናኛ ብዙኃን እንዲዘጉ አድርጓል" ብሏል።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር