1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታኅሳስ 18 ቀን 2017 ዓ/ም የዓለም ዜና

Tamirat Geletaዓርብ፣ ታኅሣሥ 18 2017

https://p.dw.com/p/4odKq

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ እገዳ መተላለፉ እንዳሳሰበው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ዛሬ ባወጣው መግለጫ እንዳለው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ የሚተላለፉ ተደጋጋሚ እገዳዎች የሲቪክ ምኅዳሩን በማጥበብ በማኅበር የመደራጀት መብት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳያሳድር ያሰጋኛል ብሏል። ዕገዳውን የጣለው ባለሥልጣን የድርጅቶቹን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ የምርመራ ሥራዎቹን በተቻለ ፍጥነት አጠናቆ ወደ ሥራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ ያመቻች ዘንድም ጠይቋል። የኮሚሽኑ ተጠባባቂ ዋና ዲሬክተር ወይዘሮ ራኬብ መለሰ በተለይ ለዶቼ ቬለ እንዳሉት በሲቭል ድርጅቶቹ ላይ የሚደረገው ምርመራ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ጥሪ ኮሚሽናቸው ጥሪ አድርጓል

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) እንዲሁም፤ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ማዕከል በዚህ ሳምንት ዕገዳ እንደደረሳቸው ማስታወቃቸው ይታወሳል ። የምሽቱ ዜና መጽሔት ዝርዝር ዘገባውን ይዟል።

 

የሁቲ አማጽያን ዛሬ ማለዳ ወደ እስራኤል ሚሳኤል አስወነጨፉ ።

አማጽያኑ ወደ እስራኤል ያስወነጨፉት እስራኤል ትናንት ምሽት ዋነናውን የየመን አውሮፕላን ማረፊያ ኢላማ ላደረገችበት መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃት አጸፋ መሆኑን አስታውቀዋል። እስራኤል ትናንት በሰንአ እና ሄዴይዳ በፈጸመቻቸው መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃቶች 3 ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች በርካቶች መቁሰላቸውን አሶሽየት,ድ ፕረስ ዘግቧል። በትናንቱ የእስራኤል ጥቃት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ለጥቂት መትረፋቸውን አስታውቀዋል። በጥቃቱ ከተገደሉ እና ከቆሰሉ ሰዎች ውስ የመንግስታቱ ድርጅት የአውሮፕላን የበረራ ሰራተኞች እንደሚገኙበት የተመድ ገልጿል።  ጥቃት የደረሰባቸው ሰራተኞች የቀዶ ህክምናን ጨምሮ የህክምና አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ድርጅቱ ጠቅሷል።

አማጽያኑ ዛሬ ያስወነጨፉትን ሚሳኤል ወደ ድንበሩ ሳይገባ በአየር መከላከያ ስረዓቱ ማክሸፉን የእስራኤል መከላከያ አስታውቋል። አማጽያኑ ከሰሞኑ በተከታታይ ወደ እስራኤል ሚሳኤሎች ማስወንጨፋቸውን የጠቀሰው ዘገባው በእስራኤል በርካታ አካባቢዎች የማስጠንቀቂያ ደውሎች መሰማታቸውንም አመልክቷል።

 

 

ኖርዌይ ውስጥ ከበርካታ ሃገራት የመጡ ሃገር ጎብኚዎችን አሳፍሮ ይጓዝ የነበረ አውቶቢስ ተገልብጦ  በትንሹ ሶስት ሰዎች ሞቱ ፤ አራቱ ጽኑ ጉዳት ደረሰባቸው ። 

አደጋው  የኖርዌይ ዋነኛው የምድር ክፍል ከሎፈተን ደሴቶች በሚያገናኘው አውራ ጎዳና ላይ የደረሰ ሲሆን አውቶቢሱ ሐይቅ ውስጥ መስጠሙን ፖሊስ አስታውቋል። አውቶቢሱ ላይ ከተሳፈሩት ውስጥ የቻይና ፣ፈረንሳይ ፣ ህንድ ፣ ማሌዢያ ፣ ኔዘርላንድ ፣ ሲንጋፖር እና የደቡብ ሱዳን ዜጎች እንደሚገኙበት የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። አደጋውን ተከትሎ ጉዳት ደርሶባቸው በህይወት የተረፉትን ሰ,ዎች አቅራቢያ ወዳለ የህክምና ተ,ቋም መወሰዳቸውን የጠቀሰው ፖሊስ ብርቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሶስት ሰዎች በሄሊኮፕተር ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ዘገባው አመልክቷል። በአደጋው የሞቱ ሰዎች ዜግነት ግን ተለይቶ አልተጠቀሰም ። ለአደጋው መድረስ በአካባቢው የነበረው ከባድ የአየር ሁኔታ በምክንያትነት ተጠቅሷል።

የኖርዌይ የሎፎተን ደሴቶች የሰሜኑን ንፍቀ ክበብ አንጸባራቂ የአድማስ ብርሃን  ለመመልከት ተወዳጅ የክረምት መዳረሻ ነው።

 

የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር የሀገሪቱን ፓርላማ በይፋ በተኑ።

ሽታይን ማየር አጠቃላይ ምርጫ የሚደረግበት ቀንም ቆርጠዋል።

የፕሬዚደንቱ ዉሳኔ ይጠበቅ እንደነበር የጠቀሰው የጀርመን ዜና አገልግሎት የሶስት ፓርቲዎች ጥምር የነበረው የመራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ መንግስት ባለፈው ህዳር ከፈረሰ በኋላ ጀርመን ከመደበኛ የጊዜ ሰሌዳ አስቀድሞ  ምርጫ ለማድረግ መገደዷን ገልጿል። መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ባለፈው ታህሳስ 7 ቀን 2017 ዓ/ም ፓርላማው መተማመኛ ነፍጓቸዋል። ይህንኑ ተከትሎ ፓርላማው ከሶሻል ዴሞክራት (ኤስፒዲ) እና ወግ አጥባቂው የክርስቲያን ዴሞክራቶች ፓርቲ (ሲ ዲ ዩ) ምርጫዉን የካቲት ውስጥ ለማድረግ ከስምምነት ደርሰዋል።

የጀርመን ህገ መንግስት አንቀጽ 39 እንደሚለው መራሄ መንግስቱ ከፓርላማው የመተማመኛ ድምጽ ባጡ ወቅት በአንድ  ወር ጊዜ ውስጥ ምርጫ መደረግ አለበት ።

የመራሄ መንግስቱ የመተማመኛ ድምጽ ማጣት የወቅ አጥባዊ የክርስትያን ዴሞክራቶች ፓርቲ ሲዲዩ የሶሻል ዶሞክራቶች ፓርቲን በ10 ነጥቦች እንዲመራ ማስቻሉን ከተሰበሰቡ የህዝብ አስተያየቶች መረዳት መቻሉን ዘገባው አመልክቷል።

 

በደርግ ዘመነ መንግሥት የሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት አቶ ሽመልስ አዱኛ ትናንት ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈፀመ። 89 ዓመታቸው ነበር።

በ1970 ዎቹ በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ከፍተኛ ድርቅ ያስከተለውን ረሃብ ለመቆጣጠር የእርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ያገለገሉት አቶ ሽመልስ አዱኛ አስከፊውን ጉዳቱ ለመቀነስ በተደረገ ርብርብ በይበልጥ ከሚጠቀሱት አንዱ ናቸው።

ልጃቸው አቶ ብሩክ ሽመልስ ለዶቼ ቬለ እንዳሉት አቶ ሽመልስ በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ ታኅሣሥ 15 ቀን 2017 ዓ. ም አርፈው ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስትያን ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል። 

ከአቶ ሽመልስ አዱኛ ጋር በ1982 አብረው እንደሠሩ የገለፀት አቶ ተስፋዬ ድረሴ በበኩላቸው፤ አቶ ሽመልስ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት በሳምንት አንድ ቀን ጽሕፈት ቤታቸውን ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ ክፍት አድርገው በቅንነት ያገለግሉ የነበሩ ሰው እንደነበሩ ለዶቼ ቬለ አስታውሰዋል።

አቶ ሽመልስ አዱኛ የአራት ወንድ እና የአንድ ሴት ልጆች አባት ነበሩ።

ታምራት ዲንሳ 

ኂሩት መለሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።