«በሲዳማ እሥርና ማሳደድ እየተፈጸመ ነው » ሲፌፓ
ማክሰኞ፣ መስከረም 29 2016
በሲዳማ ክልል መንግሥትን በሚተቹ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ላይ እሥርና ማሳደድ እየተፈጸመ ነው ሲል የሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ / ሲፌፓ / አስታወቀ። ፓርቲው እስከ ትናንት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱን ጨምሮ 20 የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮችና አባላቱ በሌሊት ተስረው መወሰዳቸውን ገልጿል።
የፓርቲው አባላት እሥር
ፓርቲው በክልሉ መንግሥት እየደረሰብኝ ይገኛል ባለው ጫና በአመራሮቹና በደጋፊዎቹ ላይ ሕገ መንግሥታዊና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ እንደሚገኙ አስታውቋል። የክልሉ መንግሥት የሀሳብ ተቃውሞና ትችት ያደርሰቡኛል ያላቸውን እያሳደደ ይገኛል፤ አንዳንዶቹንም በወታደራዊ ካምፖች ውስጥ ሳይቀር አሥሯል ሲል ፓርቲው ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል። ከታሳሪዎቹ መካከል የፓርቲው አመራሮችና አባላት እንደሚገኙበት ለዶቼ ቬለ የተናገሩት የሲዳማፌዴራሊስት ፓርቲ ሊቀመንበር ረዳት ፕሮፌሰር ተሰማ ኤሊያስ «እስከ ትናንት 20 የፓርቲው አመራሮችና አባላት በክልሉ የፀጥታ አባላት ታሥረዋል። ከታሠሩት መካከል የፓርቲው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የቁጥጥር ኮሚሽን ከፍተኛ ሃላፊዎች የፓርቲው የወረዳ ቅርንጫፍ ሃላፊዎች ይገኙበታ። የእሥር ሂደቱም ያለፍርድ ቤት መጥሪያ በሌሊት ነው የተፈጸመ የሚገኘው። በአጠቃላይ ሁኔታው በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀ የሚመስል ሁኔታ ነው ያለው» ብለዋል።
የሲዳማ ክልል አንጻራዊ ሰላም የሰፈነበትና የጎላ የፀጥታ ሥጋት የሌለበት መሆኑን የጠቀሱት የፓርቲው ሊቀመንበር «የአሁኑ እሥርና ወከባ ሐሰተኛ ወንጀላዎችን በማዘጋጀት በክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ሀይሎች ዝም ለማሰኘት ያለመ ነው» ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት ሥጋት
ዶቼ ቬለ በፓርቲው ቅሬታ ላይ የሲዳማ ክልል የሥራ ሃላፊዎችን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት ሃላፊዎቹ ለሳምንት የድርጅት ሥልጠና ገብተዋል በመባሉ አስተያያታቸውን ማካተት አልተቻለም። ያም ሆኖ የሲዳማ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ «አንዳንድ አካላትና ግለሰቦች በሕዝቡ ውስጥ መጠራጠርና ልዩነት በመፍጠር ግጭት ለመቀስቀስ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።» ሲል ከቀናት በፊት በተረጋጋጠ የፌስ ቡክ ገጹ አሥፍሯል።
ቢሮው «በስውር የተደራጁ» ባላቸውና በሥም ባልጠቀሳቸው ሀይሎች ላይ የክልሉ የፀጥታ ግብረ-ሃይል በቅርበት በመከታተል የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ይሠራል ሲልም አመልክቷል።
የፓርቲው አቤቱታ እና የምክር ቤቱ ምላሽ
የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ በበኩሉ ክልሉ በዘመቻ መልክ በጀመረው የእሥር እንቅስቃሴ ሰላማዊ የፖለቲካ ምህዳሩን አደጋ ላይ መውደቁን የጠቀሱት የፓርቲው ሊቀመንበር ረዳት ፕሮፌሰር ተሰማ ይህንንም ለአገር አቀፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፤ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አቤቱታቸውን ማቅረባቸውን ተናግረዋል ።
ፓርቲው ለምክር ቤቱ አቤቱታውን ማቅረቡን ለዶቼ ቬለ ያረጋገጡት የአገር አቀፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋር ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ «ምክር ቤቱ የዚህ አይነት ቅሬታቸውን የሚመለከተው ብቻውን ሳይሆን ከብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ጋር በመሆን ነው። ፓርቲው አሁን ያቀረበው ቅሬታ ትክክል ነው ወይስ አይደለም የሚለውን እናጣራለን። ለዚህም ክስ የቀረበበት የሲዳማ ክልል ምላሽ እንዲሰጥ በማድረግ ቅሬታውን የምናጣራ ይሆናል።» ብለዋል።
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ሸዋዬ ለገሠ
እሸቴ በቀለ