የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በድጋሚ ተራዝሟል
ማክሰኞ፣ ኅዳር 20 2009ሁለት ሴት ዕጩዎችን ጨምሮ 18 ተወዳዳሪዎች የተሰለፉበት የሶማሊያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በቀጣዩ ታህሳስ ወር ሊካሄድ እንደሚችል የሶማሊያን ጉዳይ የሚከታተለው የተባበሩት መንግስታት ተልዕኮ ጠቁሟል፡፡ ቁርጥ ያለ ቀን ግን ገና አልተወሰነለትም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እየተካሄደ ባለው የሀገሪቱ የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ እስካሁን የተመረጡት አባላት ሁለተኛ ሶስተኛውን አንኳ መድረስ አለመቻላቸው ነው፡፡
እስካሁን ባለው መረጃ 275 መቀመጫዎች ላሉት የተወካዮች ምክር ቤት የተመረጡት 164ቱ ብቻ ናቸው፡፡ የምክር ቤቱ አባላት መሟላት ግድ የሚለው የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት የሚሰይሙት እነርሱ በመሆናቸው ናቸው፡፡ ሶማሊያ በሌላው ሀገር የተለመደውን “የአንድ ሰው አንድ ድምጽ” የምርጫ አሰራርን አትከተልም፡፡ በሀገሪቱ ባለው አስተማማኝ ያልሆነ የጸጥታ እና ደህንነት ችግር ምክንያት ለጊዜው በመፍትሄነት የተወሰደው “ቀጥተኛ ያልሆነ” የምርጫ አካሄድ ነው፡፡
በዚሁ “የእጅ አዙር” ምርጫ በጎሳ መሪዎች የሚመረጡ ወደ 14 ሺህ ገደማ የሚሆኑ ሶማሊያውያን የተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ይመርጣሉ፡፡ ከእርስ በእርስ ጦርነት እያገገመች ላለችው ሶማሊያ እንዲህ አይነቱን ምርጫ እንኳ በተቀደለት ጊዜ ማካሄድ አዳጋች ሆኖባታል፡፡ አራቴ ወደ ሌላ ጊዜ የተላለፈው ምርጫ እንደተባለው በታህሳስ ወር ለመካሄዱ ማንም እርግጠኛ አይደለም፡፡
በሶማሊያ የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሀፊ ልዩ ልዑክ ማይክል ኬቲንግ ለዶይቸ ቨለ እንደተናገሩት ከሆነ ቀኑ የሚወሰነው በተወካዮች እና በህግ መወሰኛ ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ ፍጥነት ነው፡፡
“ነገሮች በፍጥነት የሚሄዱ ከሆነ ምናልባትም እስከነገ ሁለት ሶስተኛው የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ይመረጣሉ፡፡ ያኔ የምክር ቤት አባላቱ ወደ ሞቅዲሹ በመምጣት በተወካዮች ምክር ቤት መመዝገብ እና የምስክር ወረቀታቸውን መውሰድ ይጀምራሉ፡፡ ይህ ከተከናወነ እና ሁለት ሶስተኛ አባላት ከተመዘገቡ በኋላ ምክር ቤቱ የጊዜ ሰሌዳውን ያሳውቃል፡፡ መቼ አንደሚሆን መገመት ብቻ ነው የሚቻለው፡፡ መቶ በመቶ የተረጋገጠ ባይሆንም በእኔ ግምት ከታህሳስ ስድስት እስከ 11 ባለው የጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ ነው የሚሆነው” ብለዋል፡፡
እንደ ልዩ ልዑኩ አባባል ከመዘግየቱ ይልቅ ይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነገር የምርጫው ሂደቱ በራሱ መካሄዱ ነው፡፡ ብዙዎች ሂደቱ ጭራሹኑ እንደማይካሄድ ያምኑ እንደነበር ኬቲንግ ይጠቅሳሉ፡፡ ምርጫ ብሎ ከመጥራት ይልቅ የምርጫ ገጽታ ያለው የፖለቲካ ሂደት እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡
ከምርጫው ጋር ተያይዘው የሚነሱ ድምጽን በገንዘብ መግዛት እና ማስፈራራት የመሳሰሉ ድርጊቶች እንደነበሩ ልዩ ልዑኩ ይቀበላሉ፡፡ ውንጀላዎችን ተከትሎ በሚመለከተው አካል በተደረገ ማጣራት ቁጥራቸው አነስተኛ ሆነው መገኘቱን ይገልጻሉ፡፡
“እነዚህ ብርቱ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ከምርም መወሰድም ይገባቸዋል፡፡ መፍትሄ ካልተሰጣቸው የምርጫው ሂደት ተቀባይነት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡ እነዚህን ክሶችን እና ውንጀላዎችን እንዲያጣራ የተቋቋመው አካል የቀረቡለትን 1‚600 ቅሬታዎች መርምሮ 49 ወይም 50 የሚሆኑትን ብቻ እንደሚከታተል አሳውቋል፡፡ ብዙዎቹ ቅሬታዎች ከምርጫው ሂደት ጋር የሚገናኙ ሳይሆኑ በጎሳ፣ ንዑስ ጎሳ እና ንዑስ ንዑስ ጎሳዎች መካካል ያሉ አለመግባባቶች ናቸው” ይላሉ፡፡ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ጥናት ተቋም በሆነው ቻታም ሐውስ የአፍሪቃ ቀንድ ረዳት ተመራማሪ አህመድ ሱሌይማን ምርጫው በወሳኝ ደረጃ ላይ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት ጭምር ችግሮች እየታዩ ቢሆንም ካለፈው ምርጫ የተሻለ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
“የተወሰኑ ውንጀላዎች ነበሩ፡፡ ማስፈራራት እና ድምፅ መግዛት የመሳሰሉ ማረጋገጫ የቀረበባቸው እና ለምርጫው መዘግየትም ምክንያት የሆኑ አሉ፡፡ በሂደቱ ምሉዕነት እና ተአማኒነት ላይ የሚነሱ አሳሳቢ ጥያቄዎች አሉ፡፡ በዚህ ምርጫ እንደሚኖር ከሚጠበቀው ውስጥ በገንዘብ ለመመረጥ መሞከር ነው፡፡ ይህ ባለፈው ምርጫም የነበረ ነው፡፡ በዚህ ምርጫ ያለው ልዩነት ግን ሂደቱ በራሱ ብዙ ተወካዮችን ያመጣ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ውንጀላዎቹ የሚያመጡትን ተጽእኖዎች እና ባለፈው ምርጫ በድምጽ ማጭበርበር የተከሰተውን ዓይነት ትልቅ ተጽእኖ መቀነስ የሚችል ነው” ሲሉ ያብራራሉ፡፡
የአሁኑ ምርጫ ከባለፈው በተሳትፎ፣ በሚሸፍነው ቦታ፣ በቁጥጥር እና በተመራጮች ላይ በሚደረገው ጥብቅ ፍተሻ የተሻለ እንደሆነ ተመራማሪው ይገልጻሉ፡፡ ይህ ማለት ግን በዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ዘንድ የሚታሰበውን ያህል ደረጃውን የጠበቀ ምርጫ ይኖራል ማለት እንዳልሆነ ያስገነዝባሉ፡፡ አሁን በሶማሊያ እየተከናወነ ያለው ምርጫ የሽግግር ሂደት አንድ አካል ነው ባይ ናቸው፡፡
ተስፋለም ወልደየስ
ኂሩት መለሰ