የሶማሊያ እና ኢትዮጵያ የአንካራ ስምምነት፥ የሶማሊላንድ በዓለ ሲመት
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 5 2017በሶማሊላንድ የወደብ ጉዳይ ለአንድ ዓመት ግድም ሲወዛገቡ የቆዩት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አንካራ ውስጥ ረቡዕ ዕለት በቱርክ አሸማጋይነት «ቴክኒካዊ ውይይት» ለማድረግ መስማማታቸው ይፋ ሁኗል ። ሁለቱ አገራት ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ካልተሰጣት ራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የ50 ዓመት የወደብ ሊዝ አጠቃቀምን በተመለከተ የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ይፋ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ ሲወዛገቡ ቆይተዋል ።
በያኔው ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅና ትሰጣለች ሶማሊላንድም በምትኩ ለኢትዮጵያ 20 ኪሎ ሜትር የወደብና ወታደራዊ ጦር ሰፈር በሊዝ ታመቻቻለች ተብሎ ነበር ።
የአንካራው ሒደት፥ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ
ረቡዕ ዕለት አንካራ ውስጥ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ «ቴክኒካዊ ውይይት» ለማድረግ መስማማታቸው ሲገለጥ ዝርዝር ጉዳዮች ይፋ አልሆኑም ። ሆኖም የኢትዮጵያ ወደ ባሕር መውጪያ ፍላጎት፦ «አስተማማኝ፤ ደሕንነቱ በተጠበቀ እና ዘላቂ» በሆነ መንገድ «በሶማሊያ ፌዴራል ሪፐብሊክ መንግሥት ሉዓላዊ ሥልጣን ስር» እንደሚከወን ሁለቱ አገራት መስማማታቸው ተዘግቧል ። ለንደን የሚገኙት የአፍሪቃ ጉዳዮች ተንታኙ አቶ አብዱርሐማን ሠይድ ስለ ስምምነቱ ያብራራሉ ።
«ስምምነቱ በኢትዮጵያ በኩል የሶማሊያን ሉዓላዊ ግዛት ማክበር እንዳለባት ተቀብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ። እናም ይሄ ዋናው መግቢያ ነበር ። ምክንያቱም ይኼን የሶማሊያ ፕሬዚደንት እንደ[ ቅድመ ሁኔታ] ነበር ሲያስቀምጡት የቆዩት ። ምክንያቱም ከሶማሊላንድ ጋር የተደረገው ስምምነት የሶማሊያን ሉዓላዊ ግዛት የማያከብር ነው ሲሉ ነው የቆዩት ባለፈው ዓመት ። እና ይኼን በኢትዮጵያ በኩል ተቀብለዋል ።»
የሶማሊያ እና የኢትዮጵያ መሪዎችን ያደራደሩት የቱርክ ፕሬዚደንት ራቺብ ጣይብ ኤርዶሃን ሶማሊያ ለኢትዮጵያ ወደ ባሕር መውጪያ ድጋፍ ታደርጋለች ብለው ተስፋ መሰነቃቸው ተዘግቧል ። «ዛሬ ባደረግነው ስብሰባችን በተለይ የኢትዮጵያ ባሕር የመጠቀም ፍላጎትን በተመለከተ ወንድሜ ሼክ ሞሐመድ አስፈላጊውን ባሕሩን የመጠቀሚያ ድጋፍ ይሰጣሉ በሚል ተስፋ አደርጋለሁ» ሲሉ ራቺብ ረቡዕ ዕለት መናገራቸው ተገልጧል ። ፕሬዚደንቱ «አዲስ» ላሉት ጅማሬም «የመጀመሪያ ርምጃ» መጀመሩን በዕለቱ ይፋ አድርገዋል ።
«ሶማሊያና ኢትዮጵያ አገራችን ላይ በጣሉት እምነት የተነሳ ከ8 ወራት ገደማ በፊት በጀመርነው የአንካራ ሂደት አዲስ ደረጃ ላይ ደርሰናል ። ቂምን እና አለመግባባቶችን ድል በመንሳትም በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ ሰላም እና ትብብር ወደ ተመሰረተ አዲስ ጅማሬ የመጀመሪያውን ርምጃ ጀምረናል ።»
ቱርክ ከኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ጋር ያላት ግንኙነት
የቱርኩ ፕሬዚደንት ከሁለቱም አገራት መሪዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዳላቸው ይነገራል ። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2011 ጀምሮ ቱርክ ሶማሊያ ውስጥ በስፋት መዋዕለ-ንዋይ እያፈሰሰች ነው ። ያም ብቻ አይደለም በሶማሊያ ወታደራዊ ጦር ሰፈር የመሠረተችው ቱርክ በሺህዎች የሚቆጠሩ የሶማሊያ ወታደሮችንም ታሰለጥናለች ። ሞቃዲሾ አየር ማረፊያ እና ወደብን እንደምታስተዳድር ብሎም መጠነ ሰፊ ወታደራዊ እና ሰብአዊ ድጋፍ ለሶማሊያ እንደምታደርግም ይነገራል ። ካለፉት ሦስት ዓመታት አንስቶ ደግሞ ቱርክ ዐቢይ ለሚመሩት መንግሥት ሰው አልባ ጢያራ (ድሮኖችን) በመሸጥም ታስታጥቃለች በሚል ይዘገባል ።
ቱርክ ከሁለቱም አገራት መሪዎች ጋር በቅርበት እንደምትሠራ አቶ አብዱራህማን ያብራራሉ ። «ቱርክ ከኢትዮጵያ እና ከሶማሊያ ጋር ያላት ግንኙነት በጣም ጥሩ ነው ። ከኢትዮጵያ ጋር ብዙ የዲፕሎማሲ እና የኤኮኖሚ ግንኙነት አላቸው፥ ከሶማሊያም ጋር የወታደራዊ እና ሥልታዊ ግንኙነቶች አሏቸው ። እናም ከሁለቱም አገራት ጥሩ ግንኙነት ስላላቸው ለማስማማት ሲሞክሩ እና ሲጥሩ ነበር የቆዩት እስካሁን ። ለዚህ ቱርክ በጣም ጥሩ ቦታ ነው ያሉት ሁለቱን አካላት ለማስማማት ።»
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በሶማሊላንድ የተነሳ የገቡበትን ውዝግብ ያረግባል የተባለለትን «ቴክኒካዊ ውይይት» ለማድረግ ቱርክ ውስጥ መስማማታቸው በሁለቱ አገራት መሪዎች እና ፖለቲከኞች ዘንድ የተለያዩ የድጋፍ እና የተቃውሞ አስተያየቶችን አጭሯል ። በየካቲት ወር ውስጥ ዳግም ለመገናኘት ቀጠሮ የተያዘላቸው ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መተማመንን ሊያጎለብቱ እንደሚገባ አቶ አብዱርሐማን ሠይድ ገልጠዋል ።
«በሁለቱ አጋርት መካከል መተማመን መኖር አለበት፤ ለዚያም ጊዜ ያስፈልጋቸዋል ። በዚያ ላይ ደግሞ በሁለቱ በኩል ፍርሐት መኖር የለበትም ። ኢትዮጵያ ለሶማሊያ የምታሰጋ መሆን የለባትም፥ ሶማሊያም ቢሆን እንደዛው ። የሶማሊያ ግንኙነት ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ችግር ካለባቸው አገራት ጋር እንደ ኤርትርራ ወይንም ግብጽ እንዴት ይሆናል? እነዚህ ሁሉ ነገሮች መተማመን ለመገንባት ጊዜ ሊያስፈልግ ነው ። ቴክኒካዊ ስምምነቶቹ ወይንም ውይይቶቹ ቆይተው ነው የሚመጡት ።»
በሁለቱ አገራቱ ያለው መተማመን
ተጎራባች አገራት በሆኑት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል መተማመን መጎልበቱ ለ«ቴክኒካዊው ውይይት» ውጤታማነት ወሳኝ መሆኑ ይነገራል ። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አሕመድ ከሶማሊያ ጋር ለነበረው ውይይት «የሦስተኛ ወገን» ያሉት አካል ጣልቃ ገብነት ተገቢ እንዳልነበር ገልጠዋል ። ይልቁንም «የቤተሰብ ምክክር መሆን ነበረበት» ብለዋል ።
የሶማሊያ ፕሬዚደንት ሐሠን ሼክ ሞሐመድ በበኩላቸው፦ ከኢትዮጵያ ጋር የገቡትን ውዝግብ በመፍታት ረገድ የቱርኩን ቆይታ ለአገራቸው «የዲፕሎማሲ ድል» ሲሉ አወድሰዋል ። ፕሬዚደንቱ ስምምነቱን ለአገራቸው ድል አድርገው ቢቆጥሩትም፤ ጠቅላይ ሚንሥትራቸው ሐሠን ዓሊ ክሄይሬይ ግን የአንካራውን ስምምነት ለጊዜው «ጸጥ ያለ እሳተ ገሞራ» ሲሉ በብርቱ ነቅፈዋል ። ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን «ሕገ ወጥ» ያሉትን የወደብ ስምምነት መሰረዝ ነበረባት ሲሉ ሞግተዋል ።
ከጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ ጋር በወደብ ጉዳይ የመግባቢያ ሠነድ ፈርመው የነበሩት የራስ ገዟ ሶማሊላንድ የቀድሞው ፕሬዚደንት ሙሴ ቢሂ ደግሞ የቱርኩን ስምምነት አጣጥለዋል ። የሞቃዲሹ መንግሥትንም፦ «ቁጥር አንድ የሶማሊላንድ ጠላት» ሲሉ በሶማሊኛ ባደረጉት ንግግር ወርፈዋል ። የየአገራቱ መሪዎችን እና ፖለቲከኞች የሰጧቸውን አስተያየቶች የአፍሪቃ ጉዳዮችን የሚከታተለው የቢቢሲ ቁጥጥር (BBC Monitoring)ምንጭ ጠቅሶ ዘግቧል ።
የቱርክ ፕሬዚደንት ሚና
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን በማደራደር ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት የቱርክ ፕሬዚደንት አንካራ ውስጥ በተደረገው ሦስተኛ ዙር ድርድር በስተመጨረሻም የሁለቱ አገራት መሪዎችን አጨባብጠዋል ። ከመሀል ሆነውም የሁለቱ አገራት መሪዎችን እጆች ይዘው ታይተዋል ። ስምምነቱን ዩናይትድ ስቴትስ አወድሳለች ። ውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ አንቶኒ ብሊንከንም ቱርክ ስምምነቱን «በማመቻቸቷ» አመሰግነዋል ። የተባበሩት መንግሥታ ድርጅት (ተመድ)ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽም የቱርኩን ፕሬዚደንት ለሚናቸው አመሥግነዋል ። ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በመጪው የካቲት ወር ውይይት ለማድረግ ተስማምተው ነው የተለያዩት ። ውይይቱም በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሏል ። እናስ በቀጣይ አራት ወራት ውስጥ ምን ይፈጠር ይሆን? አብረን እንከታተላለን ።
የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የአንካራው ስምምነት ይፋ በሆነ ማግስት ሐሙስ ዕለት ደግሞ የሁለቱ አገራት የውዝግብ ሰበብ በሆነችው ራስ ገዟ ሶማሊላንድ የፕሬዚደንት በዓለ-ሲመት ተፈጽሟል ። የሶማሊላንድ ስድስተኛ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት የቀድሞው ተቃዋሚ መሪ አብዲራሕማን ሞሐመድ አብዱላሂ ሐርጌሳ ውስጥ ቃለ መሐላ ፈጸመው ከተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ሥልጣን ተረክበዋል ።
የሶማሊላንድ ፕሬዚደንት በዓለ ሲመት
የተቃዋሚው ዋዳኒ ፓርቲ ተወካይ አዲሱ የሶማሊላንድ ፕሬዚደንት የቀድሞው ፕሬዚደንት ሙሴ ቢሂን 64 በመቶ ድምፅ በማግኘት ነበር ያሸነፉት ። በባለፈው የኅዳር ምርጫ ወቅት የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የወደብ የመግባቢያ ስምምነት ጉዳይ ከዋነኛ የምርጫው አጀንዳዎች አንዱ ነበር ። አዲሱ የሶማሊላንድ ፕሬዚደንት የያኔውን የመግባቢያ ስምምነት ከሚተቹት በኩል መሆናቸው ይነገራል ። ግልጽነት ይጎድለዋል ያሉትን ስምምነትም ከሶማሊላንድ ሥልታዊ ጥቅም እና ዓለም አቀፍ ዕውቅና የማግኘት ትልም አንጻር ዳግም ለመቃኘት ቃል ገብተው ነው የተመረጡት ። በበዓለ ሲመቱ ወቅት የሶማሊላንድ ፕሬዚደንት አብዲራሕማን አንገብጋቢ ያሉትን ጉዳይ ይፋ አድርገዋል ።
«የአዲሱ መንግሥቴ ቀዳሚ ተግባር፦ የቀይ ባሕርን ጨምሮ የአጠቃላይ ቀጣናውን ደህንነት በማስጠብቅ የምትረዳው አዲሲቱ ሶማሊላንድ ከሌላው ዓለም ጋር ያላትን ግንኙነት ማደስ ነው ።»
ከፍተኛ ቁጥር ያለው መራጭ ተገኝቶ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንደተመረጡ የተነገረላቸው የራስ ገዟ ሶማሊላንድ አዲሱ ፕሬዚደንት በአንድ በኩል በሀገር ውስጥ ጉዳይ ማለትም ሱዑል ክልል ውስጥ ያለው ውጊያ ይጠብቃቸዋል ። ሶማሊላንድ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ዕውቅና የምታገኝበትን መንገድ ማመቻቸትም ዋነኛ ተግባራቸው ነው ። እመረምረዋለሁ ያሉት የቀድሞው ፕሬዚደንታቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያደረጉት ስምምነትም አንዱ ሌላ ጉዳይ ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር