ሶማሊያ በኢትዮጵያ ተጠቃሁ አለች
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 15 2017ሶማሊያ በኢትዮጵያ ላይ ያቀረበችው ወቀሳ፤ የኢትዮጵያ ምላሽ
ሶማሊያ ጁባላንድ ውስጥ በምትገኝ የድንበር ከተማዋ ላይ የኢትዮጵያ ኃይሎች በሚል የገለጸቻቸው አካላት ትናንት ሰኞ ጥቃት ከፍተዉብኛል ስትል አቤት ብላለች።
ለአንድ ዓመት ግድም ከኢትዮጵያ ጋር ዉዝግብ ውስጥ ቆይታ በቅርቡ ቱርክ ውስጥ በስምምነት ግንኙነቷን ያደሰችዉ ሶማሊያ፤ ስምምነቱን የጣሰ ነው ያለችው ይህ ጥቃት ዶሎው በተባለችው ከተማ ውስጥ በሚገኙ ሦስት የጸጥታ ተቋማት ወይም ጣቢያዎች ላይ የተፈፀመ ስለመሆኑ አስታውቃለች።
ይህ የሶማሊያ ክስ ከመሰማቱ በፊት የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ትናንት ወደ አዲስ አበባ የተጓዙ ሲሆን ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር የአንካራውን ስምምነት ለማጠናከር ያለመ ውይይት ስለማድረጋቸው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስታር ዛሬ ገልጿል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህንኑ በተመለከተ ዛሬ ከቀትር በኋላ ባወጣው መግለጫ የቀረበው ውንጃላ ትክክል አይደለም ብሏል። የሚኒስቴሩ መግለጫ ክስተቱ የተፈጠረው "የአፍሪካ ቀንድን ለማተራመስ ዓላማ ያላቸው" ባላቸው ሦስተኛ አካላት ሲሆን፤ ይህም የኢትዮጵያ እና የሶማሊያን የግንኙነት መስትካከል ለማወክ ነው ብሏል።
ሶማሊያ ደረሰብኝ ያለችው ጥቃት ምንድን ነው?
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ "ኃይሎች" ሲል የጠቀሳቸው አካላት በጁባላንዷ ዶሎ የድንበር ከተማ ሦስት የሀገሪቱ ጸጥታ ኃይል ተቋማት ላይ የታቀደበት ብቻ ሳይሆን ሆን ተብሎ የተቃጣ ያለው ጥቃት የተፈጽሞብናል ብሏል።
ትናንት ሰኞ ረፋድ ተፈፀመ በተበለው ጥቃት በሀገሪቱ የጦር ኃይል አባላት ላይ የሞት እና የመቁሰል አደጋ ስለመድረሱ የሚገልፀው መግለጫው በአካባቢው ሲቪል ሰዎች ላይም የደረሰው አደጋ በዝርዝር ባይገለጽም ጉዳት ስለመድረሱ አመልክቷል።
የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤ ኤፍ ፒ እንዳስነበበው ከሆነ ደግሞ ጥቃቱ ተፈፀመ በተባለበት የሶማሊያ ግዛት ውስጥ የነበሩ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ይህ ሁኔታ ውስጥ የገቡት ከሶማሊያ ጋር ቁርቁስ ውስጥ የገባችው የሀገሪቱ ግዛት አካል የሆነችው ጁባላንድ ባለሥልጣናትን ለመጠበቅ በመሞከራቸው መሆኑን ጠቅሷል።
የሶማሊያ ባለሥልጣን የኢትዮጵያ ጉብኝት
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ኃይሎች ተቃጣብኝ ያለው ጥቃት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ከሦስት ሳምንታት በፊት ቱርክ አንካራ ውስጥ የተፈራረሙትን ስምምነት የሚጥስ ነው ብሏል።
ይህ የሶማሊያ ክስ የተሰማው የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ምኒስትር ድኤታ አሊ ሞሐመድ የሁለቱን ሀገራት የአንካራ ስምምነት ለማጠናከር ያለመ ውይይት ለማድረግ ትናንት አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ነው። ሶማሊያ ይህንኑ ጉብኝት አስመልክታ ባወጣችው መግለጫ ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋራ ለሚኖራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላትን የማያወላዳ ቁርጠኝነት የሚያመለከት ብላው ነበር።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ይህንኑ በተመለከተ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እና የሶማሊያው አቻቸው አሊ መሃመድ ኦማር ዛሬ በአዲስ አበባ ተወያይተዋል።
ሚኒስትር ዲኤታው "ኢትዮጵያ ለአንካራው ስምምነት ተግባራዊ መሆን ቁርጠኛ ናት" ስለማለታቸው እና "የሁለቱ ሀገራት ትብብር ማደግ ለቀጠናው ሰላም እና ዕድገት ወሳኝ" ስለመሆኑ መናገራቸውም ተጠቅሷል። የሶማሊያ አቻቸውም ሀገራቸው "የአንካራው ስምምነት በተፋጠነ ሁኔታ እንዲተገበር ትሻለች" ማለታቸው በመግለጫው ተገልጿል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያበቱርክ አሸማጋይነት የደረሱትን ስምምነት ለመተግበር እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት በዚህ ወቅት ይህንን ጥረት የሚጎዳ ክስ ከሶማሊያ በኩል የመምጣቱን ነገር መነሻ አድርገን ሀሳባቸውን የጠየቅነቸው አንድ የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ትንታኝ ተከታዩን ብለዋል።
"የአንካራው ዲክላሬሽን በመጀመርያ ደረጃ ስምምነት አይደለም። መሠረታዊ የሆኑ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ተቀባይነት ያላቸው መርኾዎችን ነው እንደገና እንቆምላቸዋለን የሚል ስምምነት ያደረጉት"።
ሌሎች የአካባቢው ዐበይት ሰሞነኛ ጉዳዮች
የአፍሪካ ቀንድን በተመለከተው ጉዳይ ተጨማሪ ዐበይት የሚባሉ ዘገባዎች እየወጡ ሲሆን ትናንት ወደ ካይሮ የተጓዙት የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አሕመድ ፊቂ ከግብጹ እቻቸው ባድር አብደላቲ ጋር ከተወያዩ በኋላ ከወደ ካይሮ የወጡ መረጃዎች የቀይ ባሕር ዳርቻን ሊጠቀሙ የሚችሉት ከዚሁ ቁልፍ ጠቀሜታ ካለው ባሕር ጋር የሚዋሰኑ ሀገራት ብቻ መሆን እንዳልባቸው ግብጽ አቋም ስለማረመዷ ያትታሉ።
የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ተንታኙ ግን በዚህ አይስመሙም። ምክንያቱም ሀገራት የባሕር በር የማግኘት መብታቸው በዓለም አቀፍ ሕግ የተጠበቀ ነውና ነው መልሳቸው።
"ማንኛውም የባሕር በር የሌለው ሀገር የባሕር በር ያላቸው ሀገራት ሊከለክሉት አይገባም። በወደብ የመጠቀም መብቱን ሊያከብሩለት ይገባል የሚል መርኽ አለ"።
ለቀረበው ክስ የኢትዮጵያ ምላሽ
ሶማሊያ የአንካራን ስምምነት፣ የአፍሪካ ሕብረትን እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ድንጋጌዎች የጣሰ ነው ያለችውን ይህንን ጥቃት በተመለከተ የኢትዮጵያን መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ከምሳ ሰዓት በኋላ መግለጫ ያወጣ ሲሆን ሶማሊያ በኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ያወጣችው ውንጀላ ትክክል እንዳልሆነና ክሱ እንዳሳዘነው ጠቅሷል። መግለጫው "ክስተቱ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ያለውን ግንኙነት መደበኛ እንዲሆን በማይሹ" በላቸው አካላት የተፈጠረ ነው። ይላል።
እነዚህ በስም ያልተጠቀሱ ሦስተኛ ወገኖች "የአፍሪካ ቀንድን ለማተራመስ ዓላማ ያላቸው እና የቀጣናው ሰላም ዘላለማዊ አጥፊዎች" መሆናቸውንም ገልጿል።
አነዚህ አካላት ሁለቱ ሀገራት አንካራ ውስጥ የገቡትን የሰላም ቁርጠኝነት እንዲያከሽፉ ሊፈቀድላቸው አይገባም ያለው መግለጫው የኢትዮጵያ መንግስት ሶማሊያ ውስጥ ተመሳሳይ አደጋዎችን ለመከላከል ከሚመለከታቸው ይፕፌዴራል መንግስት አካላት ጋር ተባብሮ ይሰራል ብሏል።
በሌላ በኩል ሮይተርስ የዜና ወኪል ይዞት በወጣው መረጃ
የግብፅ ወታደሮች በቀጣይ በጎረቤት ሶማሊያ ይሰማራል ተብሎ በሚጠበቀው የአፍሪካ ሕብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውስጥ ከሶማሊያ መንግሥት ቀረበ በተባለ ጥያቄ ትሳትፎ እንደሚኖራቸው የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስለመናገራቸው ተሰምቷል።
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ኂሩት መለሰ