1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሊያ ፕሬዝደንት የኬንያ ጉብኝት

ዓርብ፣ መጋቢት 15 2009

አዲስ የተመረጡት የሶማሊያ ፕሬዝደንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ ለሦስት ቀናት ጉብኝት ትናንት ኬንያ ገብተዋል። ፕሬዝደንቱ ወደ ኬንያ የተጓዙበት ዋነኛዉ ምክንያት የምሥራቅ አፍሪቃ ሃገራት የልማት በይነ መንግሥታት በእንግሊዝኛ ምህፃሩ ኢጋድ ልዩ ስብሰባ ቢሆንም፤ ከኬንያዉ ፕሬዝደንት ጋር የሁለትዮሽ ዉይይትም እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/2ZqqG
Kenia Nairobi Besuch Somalischer Präsident
ምስል Getty Images/AFP/S. Maina

Somalia president first state visit to Kenya - MP3-Stereo

አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝደንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ ወይም መሐመድ አብዱላሂ ፎርማጆ ጎረቤት ኬንያን እንደመንግሥት መሪ ሆነዉ ሲጎበኟት ይህ የመጀመሪያቸዉ ነዉ። ከፍተኛ ባለስልጣናትን አስከትለዉ ወደ ናይሮቢ ትናንት የተጓዙት የሶማሊያ ስደተኞችን ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳዉ አድርጎ ነገ ቅዳሜ በሚነጋገረዉ የምሥራቅ አፍሪቃ ሃገራት የልማት በይነ መንግሥታት፤ ኢጋድ ጉባኤ ላይ ለመገኘት ነዉ። የመረጃ ምንጮች አስቀድመዉ እንደጠቆሙት ፕሬዝደንት መሐመድ፤ የኢጋድ ስብሰባ ከመካሄዱ ሁለት ቀናት ቀድመዉ ናይሮቢ የገቡት ከኬንያዉ አቻቸዉ ፕሬዝደንት ዑሁሩ ኬንያታ ጋር በሁለቱ ሃገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ለመነጋገር ነዉ። ዘገባዎች እንደሚሉት የሁለቱ ሃገራት መሪዎች ዉይይት የሚያተኩረዉ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2015ዓ,ም ናይሮቢ ላይ ሶማሊያ እና ኬንያን እንዲተባበሩባቸዉ በተስማሙባቸዉ ጉዳዮች ላይ ይሆናል። ናይሮቢ የሚገኘዉ ዘጋቢያችን ፍቅረማርያ መኮንን መነጋገያ ይሆናሉ የተባሉትን ነጥቦች እንዲህ ይዘረዝራል።

Somalia Al-Shabaab Kämpfer
ምስል picture alliance/AP Photo/F. A. Warsameh

ኬንያ ሶማሊያ ዉስጥ የሚንቀሳቀሰዉን ጽንፈኛ እስላማዊ ታጣቂ ቡድን አሸባብን ለመዋጋት ጦሯን ካዘመተች ወዲህ ዋና ከተማ ናይሮቢን ጨምሮበተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተደጋጋሚ ጥቃቶች ደርሰዉባታል። ሶማሊያ የሚገኘዉ ሠራዊቷም ከአንዴም ሁለቴ የአሸባብ የጥቃት ኢላማ ሆኗል። በዚህም ምክንያት የሀገሪቱ ምክር ቤት መንግሥት ወታደሮቹን ከሶማሊያ እንዲያወጣ እየጠየቀነዉ።  የሶማሊያዉ ፕሬዝደንት በዚህ ጉብኝታቸዉ ወቅት ከኬንያ ባለስልጣናት ጋር በሚያደርጉት ዉይይት የሁለቱ ሃገራት የፀጥታ ጉዳይ ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል የሚል ግምት እየተሰነዘረ መሆኑን ፍርቅረማርያም ጠቅሷል።

Kenia Das Flüchtlingslager Dadaab
ምስል Getty Images/AFP/T. Karumba

አዲሱ ሶማሊያ ፕሬዝደንት ቃለመሃላ በፈፀሙበት ወቅት በስፍራዉ የተገኙት የኬንያዉ ፕሬዝደንት ሀገራቸዉ የሶማሊያን ሰላም ለማስጠበቅ በአቋሟ እንደምትጸና ቃል ገብተዋል። ቅዳሜ ዕለት የሚካሄደዉ የኢጋድ ስብሰባ ዋናዉ ትኩረት የሶማሊያ ስደተኞች ጉዳይ እንደሚሆን ነዉ የተገለጸዉ። ኬንያ በርካታ የሶማሊያ ተሰዳጆች የተጠለሉበትን ትልቁን የስደተኞች መጠለያ ዳዳብን እንደምትዘጋ በተደጋጋሚ ስታሳስብ ቆይታለች። የሶማሊያዉ ፕሬዝደንት ከኢጋድ ጉባኤ አስቀድመዉ ከኬንያ ባለስልጣናት ጋር በዚሁ ጉዳይ ላይ የሚያደርጉት ዉይይትም ሆነ ኬንያ ከተመድ ኃላፊዎች ጋር ያካሄደችዉ ንግግር መጠለያዉ ሳይዘጋ እንዲቆይ አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚችል ፍቅረማርያም መኮንን ያለዉን ግምት ገልጿል። ሶማሊያ ዉስጥ በጦርነትና ድርቅ ምክንያት 1,1 ሚሊየን የሆኑ ሰዎች ከቤት ንብረታቸዉ እንደተፈናቀሉ ሲገመት፤ 900 ሺህ የሚሆኑ ደግሞ በዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ዉስጥ ይገኛሉ።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ