1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሸገር ከተማ አስተዳደር ቤት ፈረሳ አመክንዮ እና ዳፋ

Eshete Bekele
እሑድ፣ ሚያዝያ 15 2015

የሸገር ከተማ አስተዳደር ባለሥልጣናት "ሕገ ወጥ" ያሏቸውን መኖሪያ ቤቶች ሲያፈርሱ "ማኅበራዊ ቀውስ" መፈጠሩን ባያምኑም ዜጎች ብርቱ ችግር ገጥሟቸዋል። ቤታቸው የፈረሰባቸው ዜጎች አቤቱታ የቀረበላቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኃላፊዎች የተሳተፉበት ውይይት የእርምጃውን አመክንዮ እና ዳፋ ይፈትሻል

https://p.dw.com/p/4QQOH
Äthiopien Vertriebene Menschen bei Legetafo
ምስል DW/Solomon Muchie

እንወያይ፦ የሸገር ከተማ አስተዳደር ቤት ፈረሳ እና ውዝግቡ

በአዲስ አበባ ዙሪያ የነበሩ ከተሞችን አንድ ላይ በማዋቀር እንደ አዲስ የተቋቋመው የሸገር ከተማ አስተዳደር ባለሥልጣናት "ሕገ ወጥ" ያሏቸውን የመኖሪያ ቤቶች እያፈረሱ ነው። የሚፈርሱት “ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸው” የተባሉ ግንባታዎች ሲሆኑ አብዛኞቹ የመኖሪያ ቤቶች ናቸው። "በተለይም ከ2005 ዓ.ም. በኋላ የተገነቡ ቤቶች እንዲፈርሱ በተወሰነው መሠረት" እርምጃው እየተወሰደ እንደሚገኝ የሸገር ከተማ አስተዳደር ባለሥልጣናት ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ገልጸዋል። ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ መሠረት "ከቤቶቹ ባለቤቶች ጋር በክፍለ ከተማ፣ በወረዳ እና በቀበሌ ደረጃ ውይይት ተደርጎ በቂ ግንዛቤ" እንዲፈጠር መደረጉን ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል። 

በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው የሸገር ከተማ አስተዳደር ባለሥልጣናት እርምጃው "ማኅበራዊ ቀውስ" ፈጥሯል የሚል እምነት ባይኖራቸውም የመኖሪያ ቤቶቻቸው የፈረሰባቸው ዜጎች ግን ለብርቱ ችግር ተዳርገዋል። በአረብ ሀገር ሰርተው ባጠራቀሙት ጥሪት የገነቡት እና ለስምንት ዓመታት የኖሩበት መኖሪያ ቤታቸው የፈረሰባቸው አንዲት የሁለት ልጆች እናት "አራስ ነኝ። የትም እየተንከራተትኩ ነው" ሲሉ የሆነባቸውን ሳግ እየተናነቃቸው ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። ባለቤታቸው የቀን ሠራተኛ እንደሆኑ የገለጹት እኚሁ እናት የመኖሪያ ቤታቸው ሲፈርስ "ያዘዘን መንግሥት ነው"  የሚል ምክንያት እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

ቤታቸው ያለማስጠንቀቂያ እንደፈረሰባቸው የገለጹ ሌላ አባወራ በበኩላቸው በተጠጉበት የዘመድ ግቢ ከነ ልጆቻቸው "ሸራ ውስጥ" ለመኖር መገደዳቸውን ተናግረዋል። የመኖሪያ ቤት ከፈረሰባቸው አካባቢዎች መካከል ሰበታ፣ ቡራዩ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ፣ መነ አብቹ ይገኙበታል። ቤት የፈረሰባቸው ሰዎች " ከቀድሞ ወይም ነባር ባለ ይዞታዎች ቦታ ወይም ቤት በመግዛት ኑሮ መሥርተው" በአካባቢዎቹ ይኖሩ እንደነበር መናገራቸውን አቤቱታቸውን የተቀበለው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያወጣው መግለጫ ይጠቁማል። ከዚህ በተጨማሪ "በየአካባቢው ከሚገኙ ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የውኃ እና የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ" ነበሩ። 

የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም እና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በርካታ የመኖሪያ ቤቶች የፈረሰባቸው ዜጎችን አቤቱታ ተቀብለዋል። በዚህ ውይይት የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ እና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ዶክተር ብራይትማን ገብረሚካኤል ተሳትፈዋል። የሸገር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጉግሳ ደጀኔ ለመሳተፍ ፈቃደኝነታቸውን ገልጸው የነበረ ቢሆንም ውይይቱ በተካሔደበት ዕለት ሳይገኙ ቀርተዋል። 

ሙሉ ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ