1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቤት ክራይ ዋጋ ጭማሪ ክልከላ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 4 2015

ውሳኔውን በተመለከተ የጠየቅናቸው የሕግ ባለሙያ የሆኑት «የግለሰቦችን የግል ንብረትን የመጠቀም መብት የሚጋፋ ነው» በማለት ለችግሩ ሌላ ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈለግ መሥራት ይሻላል ብለዋል።

https://p.dw.com/p/4TjKy
Äthiopien Addis Abeba Stadtansicht
ምስል Solomon Muchie/DW

የቤት ክራይ ዋጋ ጭማሪ ክልከላ

አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ማንኛውም ቤት አከራይ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት የቤት ኪራይ ጭማሪ እንዳያደርግ እንዲሁም ተከራይን ከቤቱ እንዳያስወጣ ክልከላ ተጣለበት። 

የከተማ አስተዳደሩ ይህንን ውሳኔ ከዚህ በፊትም ደጋግሞ ተግባራዊ ያደረገው ሲሆን ለአሁኑ ክልከላ ምክንያት በሚል ያስቀመጠው «የኑሮ ውድነቱ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች ላይ የሚያሳድረውን ጫና ለመቀነስ» ነው። 

የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ መናር ነዋሪዎችን ያማረረ መሠረታዊ ችግር መሆኑን ተከራዮች ደጋግመው የሚናገሩት ሲሆን አከራዮች በበኩላቸው መንግሥት ከሰሞኑ ከፍተኛ ያሉትን የጣራ እና ግድግዳ ግብር በአከራዮች ላይ ከጣለ በኋላ የክራይ ጭማሪ እንዳይደረግ መከልከሉ አግባብ አይደለም ብለዋል። 

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የሕግ ባላሙያ መንግሥት በግለሰብ መብት ውስጥ ገብቶ ውሳኔ ሰጪ መሆኑ ተገቢ እንዳልሆነ ገልፀዋል።

 Addis Ababa City
ምስል Seyoum Getu/DW

አዲስ አበባ ውስጥ የመኖሪያ ቤት ኪራይ በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው እና በየወሩ የታወቀና የተሰፈረ ደሞዝ ላላቸው ዜጎች መፍትሔ የሌለው ፈተና እየሆነ ይመስላል። 
ይህ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ነዋሪ ታሳቢ ያደረገው የከተማ አስተዳደሩ ክልከላ ከፍተኛ የጣራ እና ግድግዳ ግብር ተጣለብን የሚሉ አከራዮችን ያሳሰበ ውሳኔ ሆኗል ፣ የመብት ጥያቄም እያስነሳ ይገኛል።
መስተዳድሩ ያወጣው ደንብ ለተከራዮች ጊዜያዊ እፎይታ ያለው ቢመስልም ጫናው ዞሮ ዞሮ ተከራይ ትከሻ ላይ የማይወርድ ስለመሆኑ ያነጋገርኳቸው አከራይ እና ተከራይ ገልፀዋል። 
ውሳኔውን በተመለከተ የጠየቅናቸው የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ዮሃንስ ተሰማ «የግለሰቦችን የግል ንብረትን የመጠቀም መብት የሚጋፋ ነው» በማለት ለችግሩ ሌላ ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈለግ መሥራት ይሻላል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች በመንግሥት የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አሁን በውድ ዋጋ የሚከራዩና የሚሸጡ ሆነዋል። በሌላ በኩል በከተማዋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በባለሃብቶች የሚገነቡ ቅንጡ የመኖሪያ ቤት መንደሮች ዋነኛ የትርፍ ማስገኛ የሥራ ዘርፍ እየሆኑ መምጣታቸው ይታያል።
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሔር
ነጋሽ መሐመድ

Äthiopien - Addis Abeba - City Churchill Road
ምስል DW/Y. Geberegziabehr