የብልጽግና ፓርቲ ጉባዔና የአማራ ክልል ነዋሪዎች አስተያየት
ሰኞ፣ መጋቢት 5 2014ሰሞኑን የተካሄደው የብልፅግና ፓርቲ ጉባዔ ሁሉንም ያሰተፈና ዴሞክራሲያዊ እንደነበር አንዳንድ የአማራ ክልል ነዋሪዎች ተናገሩ፣ ሰላምን በክልሉ ለማስፈን ወደ ተግባር በፍጥነት ከመግባት አኳያ ግን አሁንም ጥርጣሬ አላቸው፡፡ ዶይቼ ቬሌ የገንዳውሀ፣ የደሴ፣ የላሊበላና የባሕርዳር ከተሞች ነዋሪዎችን አስተያየት ጠይቋል፡፡ የብልፅግና ፓርቲ የመጀመሪያ የሆነውን ጉባኤ ባለፉት 3 ቀናት በአዲስ አበባ አካሂዷል፡፡ የጉባኤውን ሂደትና ከጉባኤው ይጠብቁት የነበረውን ውሳኔ በተመለከተ አስተያየታቸውን ከሰጡን መካከል በደቡብ ወሎ ዞን የደሴ ከተማ ነዋሪው መከተ ካሳው ሂደቱ ዴሞክራሲያዊ ነበር ብለዋል፡፡
ከባህር ዳር ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡን አቶ ቢራራ በዜ ደግሞ የምርጫ ሂደቱ ከዴሞክራሲ የወጣ እንደነበር ትዝብታቸውን አስቀምተዋል ምክንያታቸው ደግሞ አንድ ጉባኤ ሲካሄድ አስመራጭ ኮሚቴ ይቋቋማል እንጂ የፓርቲው ሊቀመንበር ምርጫን ማካሄድ አልነበረበትም ነው ያሉት፡፡ መድክ ላይ የተነገረው ተግባር ላይ ይውላል ወይ? የሚለው ሥጋታቸው እንደሆነ ነው አስተያየታቸውን የሰጡን የደሴው ነዋሪ የተናገሩት፡፡ በሰሜን ወሎ ዞን የላሊበላ ከተማ ነዋሪው አቶ ቸኮለ ታዘበው በበኩላቸው ጉባዔው ሁሉንም ማካተቱ የዲሞክራሲን መንገድ ያሳያል ነው ያሉት፡፡ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪው ቢራራ በዜ ግን በዚህ ሀሳብ አይስማሙም፣ ምርጫው አሁንም እንደቀድሞው ኮታን ማዕከል ያደረገ ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡
በጉባኤው የተነሱና ውይይት የተደረጉባቸው አንግብጋቢ ጉዳዮች ይፈታሉ ብለው ተስፋ እንዳላቸው የላሊበላው አስተያየት ሰጪ አቶ ቸኮለ ተናግረዋል፡፡ አቶ ሙሉጌታ ዓለምነህ ነዋሪነታቸው በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሀ ከተማ ሲሆን ጉባኤው አሁንም የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅ ያሳለፈው ውሳኔ አጥጋቢ አይደለም ሲሉ አመልክተዋል፣ በዞናቸው እገታ የየቀን ተቀን ስራ እንደሆነ በማሳወቅ፡፡
እንደ ባህር ዳሩ አስተያየት ሰጪ ቢራራ በዜ በጉባኤው የተቀመጡ ውሳኔዎች በግዜ ማዕቀፍ መቀመጥ ነበረባቸው፣ ጉባኤው እሰራቸዋለሁ በሎ ውሳኔ ያሳረፈባቸው ጉዳዮች የመፈፀሚያ ጊዜያቸው ባለመቀመጡ ተዓማኒነት አይኖራቸውም ብለዋል፡፡ ብልፅግና ፓርቲ ሰሞኑን ባደረገው ጉባኤ፣የድርጅቱን ሊቀመንበርና ሁለት ሊቀመናብርትን፣ 45 ስራ አስፈፃሚዎችንና 225 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን በመምረጥ ተጠናቅቋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ
ኂሩት መለሰ