1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተፈረመው የሰላም ስምምነትና ተግባራዊነቱ

እሑድ፣ ጥቅምት 27 2015

በአፍሪቃ ኅብረት አስተባባሪነት በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሃት ተወካዮች ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ያበሰሩት የአፍሪቃ ኅብረት ልዩ መልእክተኛ ኦሊሴንጎን ኦባሳንጆ ተግባራዊነቱ በሂደት እንደሚከወን አጽንኦት ሰጥተዋል።

https://p.dw.com/p/4J5dl
Pretoria | Waffenstillstandsabkommen für Äthiopien
ምስል Themba Hadebe/AP/picture alliance

የሰላም ስምምነቱ

ትግራይ ክልል ውስጥ ተለኮሰው ወደ አጎራባች ክልሎች ተዛምቶ ከፍተኛ ውድመት ያስከተለው ጦርነት በተጀመረ ልክ በሁለተኛ ዓመቱ ዋዜማ በሰላም ስምምነቱ መቋጨቱ ይፋ ሆኗል። በአፍሪቃ ኅብረት አስተባባሪነት በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሃት ተወካዮች ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ያበሰሩት የአፍሪቃ ኅብረት ልዩ መልእክተኛ ኦሊሴንጎን ኦባሳንጆ ተግባራዊነቱ በሂደት እንደሚከወን አጽንኦት ሰጥተዋል። ስምምነቱ አስቸኳይ ተኩስ ማቆምን፤ የህወሃትን ትጥቅ መፍታት፤ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ትግራይ ውስጥ የማስጀመር፣ እንዲሁም ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን ማፋጠንን ያካትታል። ከሁለት ዓመታት በኋላ ስለሰላም መነገር መጀመሩ፤ ልዩነትን በጦር መሣሪያ ለመፍታት በሚደረግ ሙከራ በወገን ላይ የሚደርሰው መከራ እንዲያከትም ይረዳል የሚል ተስፋ አሳድሯል። ጦርነቱ ህይወቱን ያሳጣው፤ ኑሮውን ያናጋበት እና ንብረት ጥሪቱን ያወደመበት እንዲሁም ለስነልቡና ቀውስ የዳረገው ወገን የሰላም ስምምነቱ በእርግጥ እንደታሰበው ሥራ ላይ ከዋለ ከጥይት ጩኸትና መሳቀቅ እፎይታ ያገኝ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል። በአንጻሩ የአንድ እናት ልጆችን ወደ ደም አፋሳሽ እና አውዳሚ ጦርነት ገፍቶ በከተተው የገረረ ፖለቲካ ምክንያት የተበጠሰው እና የተበላሸው ማኅበራዊ መስተጋብር የሚሽርበትን መፍትሄ ማፈላለግ ለዘላቂ ሰላም ግዙፍ አስተዋጽኦ እንዳለው የሚናገሩ አሉ። ለሰሜኑ ጦርነት ትኩረት ተሰጥቶ በይፋ መነጋገሪያ ሆኖ ቢዘልቅም የአፈሙዝን ላንቃ በዘላቂነት በምድረ ኢትዮጵያ ዝም ለማስባልም ሆነ የሰላማዊ ሰዎችን ግድያ፣ ጥቃትና መፈናቀል ብሎም ሰቆቃ ለማስቆም ተመሳሳይ ሂደት በኦሮሚያ ክልል ውስጥም ያስፈልጋል የሚሉ ወገኖችም ድምጽ እየተሰማ ነው። የሰላም ስምምነቱ ምን ያህል ተግባራዊ ይሆናል? ክትትሉንስ አፍሪቃ ኅብረት ብቻውን ሊወጣው ይችል ይሆን? በመላው ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣትስ ፋይዳው እስከምን ድረስ ነው? የሚሉትን እና ተያያዥ ነጥቦችን በማንሳት ሦስት እንግዶችን ጋብዘን ተወያይተናል። ሙሉውን ውይይት ለማድመጥ ድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።

Pretoria | Waffenstillstandsabkommen für Äthiopien
ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ ላይ የተካሄደው የሰላም ውይይት በስምምነት ከተጠናቀቀ በኋላምስል PHILL MAGAKOE/AFP

ሸዋዬ ለገሠ