የታኅሣሥ 7 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 7 2017በኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ምርጫ ውዝግቡ ቀጥሏል ። በዛሬው ስብሰባ ምን ተከሰተ? ቃለ መጠይቅ ይኖረናል ።በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በ10 ተጨዋቾች የተጋጠመው መሪው ሊቨርፑል እና አርሰናል በተለያዩ ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል ። ማንቸስተር ሲቲ በማንቸስተር ዩናይትድ ተሸንፏል ። በቡንደስ ሊጋው ሽንፈት የገጠመው ባዬርን ሙይንሽን በደረጃው መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው ። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ የዓለም መድረኮች እንደተለመደው ድል አድርገዋል ።
አትሌቲክስ
በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወኑ የሩጫ ፉክክሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ ውድድሮች አሸናፊ ሁነዋል ። ቻይና ውስጥ ትናንት በተከናወነው የፉዦ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች አንደኛ ሲወጡ፤ በሴቶች ፉክክር አምስተኛ ደረጃ አንዲት ኬኒያዊት ብቻ ጣልቃ ስትገባ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ኢትዮጵያውያት አትሌቶች ተከታትለው ገብተዋል ።
ውድድሩን ገነት ሮቢ 2:27:05 በመሮጥ 1ኛ ወጥታለች ። ሠላማዊት ጌትነት፣ ኑሪት ሽመልስ፣ ባራኪ ገብርኤል እንዲሁም አትሌት አያና ከሁለተኛ እስከ ስድስተኛ ወጥተዋል ። አምስተኛ ደረጃ ያገኘችው ኬኒያዊት አትሌት ሊሊያን ጄቢቶክ ናት ።
በወንዶች ተመሳሳይ ፉክክር አትሌት አብዱ እንድሪስ አንደኛ የወጣው 2:10:54 በመሮጥ ነው ። ቻይናውያን አትሌቶች ዚቼንግ ሊ እና ቦ ሊን ተከትለው ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን አትሌት ስንታየሁ ለገሰ እና ጥላሁን አየለ አራተኛ እና አምስተኛ ደረጃ አግኝተዋል።
ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሱቱሜ አሠፋ ሕንድ ውስጥ በተከናወነው የኮልኮታ 25 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ 1:19:21 በመሮጥ አሸንፋለች ። ኬኒያዊቷ ቪዮላ ቼፕንጌኖ እና ለባህሪን የምትሮጠው ደሲ ጂሳ መኮንን ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ። ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች፦ ዓለምአዲስ እያሱ፣ ደጊቱ አዝመራው፣ ምሥጋን ዓለምአየሁ እና ስንትዐየሁ ለውጠኝ እስከ ሰባተኛ ደረጃ ተከታትለው ገብተዋል ።
በወንዶች ተመሳሳይ ፉክክር ድሉ የኡጋንዳዊው ስቴፈን ኪሳ ሁኗል ። ኬንያውያን አትሌቶች ከሁለተኛ እስከ ሥድስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ። ኢትዮጵያዊው አትሌት ደጀኔ ኃይሉ ስድስተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል። ኢትዮጵያውያኑ ሃይማኖት አለው እና አልአዛር ተፈራ 11ኛ እና 12ኛ እንዲሁም አብርሃም ዘሪሁን 20ኛ ደረጃ አግኝተዋል ። የኅዳር 30 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
አትሌት ንብረት መላክ ታይላንድ ውስጥ በተከናወነው የባንግሴን 21 ኪሎ ሜትር ግማሽ ማራቶን 1:02:32 ሩጦ በማጠናቀቅ አሸናፊ ሁኗል ። ኬንያውያን አትሌቶች አሌክሳንደር ሙንዮ እና ጌኦፍሪ ቶሮይቲችን በመከተል ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ልዑል ገብረ-ሥላሴ አራተኛ ደረጃ አግኝቷል ። ሁለት ኬንያውያንን በመከተል ከ7ኛ እስከ 10ኛ ደረጃ ያገኙት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው ።
ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ለምለም ግርማይ ስድስተኛ ደረጃ ባገኘችበት ተመሳሳይ የሴቶች ሩጫ ፉክክር ኬንያውያን የበላይ ሁነው ታይተዋል ። በውድድሩ ኬንያዊቷ አትሌት ዊንፍሬድ ሞራ 1:10:01 ሩጣ አንደኛ ወጥታለች ። ኡጋንዳዊቷ ሬቤካ ቼላንጋት በ33 ሰከንድ ተበልጣ ሁለተኛ ወጥታለች ። ከሦስተኛ እስከ ሰባተኛ ደረጃ ኬንያውያት ተከታትለው ገብተዋል ።
በታይፒ ማራቶን ትናንት ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አሚድ ፎይዛ 2:32:47 በመሮጥ አሸናፊ ሁናለች ። ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች ኦብሴ አብደታ እና ኬታቦ ጫልቱ የሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ አግኝተዋል ። ሁለተኛ የወጣችው ኬኒያዊቷ አትሌት ካሪን ቼፕቶይክ ናት ። የኅዳር 23 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
በወንዶች ተመሳሳይ ፉክክር፦ ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ጋዲሳ ብርሃኑ እና ዕንየው መኮንን ሁለተኛ እና አራተኛ ደረጃ አግኝተዋል ። በዚህ ውድድር ያሸነፈው ኬንያዊው አትሌት ቢርሚን ኪፕኮሪር ነው ። ኤርትራዊው አትሌት እቑባይ ፀጋዬ ሦስተኛ ደረጃ አግኝቷል ።
ከዚሁ የአትሌቲስ ዜና ሳንወጣ፦ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የፕሬዚደንትነት ምርጫ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ይከናወናል ። በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮ ስፖርት መርኃ ግብር ዋና አዘጋጅ ምስጋናው ታደሰ ጉዳዩን በቅርበት ተከታትሏል ። ባለፉት ጊዜያት በተለይም በፓሪስ ኦሎምፒክ ሰሞን የነበሩት አወዛጋቢ ጉዳዮች በምርጫው ላይ ምን አንደምታ ይዘው መጥተዋል? በምርጫው እነማን ይሳተፋሉ እነማንስ ወደ አመራር ይመጣሉ?
ፕሬሚየር ሊግ
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው መሪው ሊቨርፑል ቅዳሜ ዕለት በሜዳው አንፊልድ ፉልሀምን ገጥሞ ሁለት እኩል ተለያይቷል ። 17ኛው ደቂቃ ላይ አንድሪው ሮበርትሰንን በቀይ ካርድ ያጣው ሊቨርፑል ከመመራት ተነስቶ ለማሸነፍ ብርቱ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። በስተመጨረሻ ነጥብ ተጋርቶ በ36 ነጥብ የመሪነት ስፍራውን አስጠብቋል ። ሊቨርፑል አንድ ተስተካካይ ጨዋታውን የፊታችን እሁድ በቶትንሀም ሜዳ ያከናውናል ። የኅዳር 16 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
በደረጃ ሰንጠረዡ ከሊቨርፑል ተከታዩ ቸልሲ ትናንት ብሬንትፎርድን 2 ለ1 አሸንፎ ነጥቡን 34 አድርሷል ። በጨዋታው ፍጻሜ 98ኛ ደቂቃ ላይ የቸልሲው ማርክ ኩኩሬላ ቀይ ካርድ ዐይቷል ። 30 ነጥብ ይዞ 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል ቅዳሜ ዕለት ከኤቨርተን ጋር ያለምንም ግብ ተለያይቷል ። ኖቲንግሀም ፎረስት በ28 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ከትናንት በስትያ አስቶን ቪላን 2 ለ1 ሸኝቷል ። በ27 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ ትናንት በሜዳው ኤቲሀድ ስታዲየም ማንቸስተር ዩናይትድን ገጥሞ 2 ለ1 ተሸንፏል ።
ቡንደስሊጋ
በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ቅዳሜ ዕለት በማይንትስ የ2 ለ1 ሽንፈት የገጠመው ባዬርን ሙይንሽን በ33 ነጥብ መሪነቱን እንደተቆናጠጠ ነው ። አውግስቡርግን በገዛ ሜዳው 2 ለ0 ያሸነፈው ባዬርን ሌቨርኩሰን በ29 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። በላይፕትሲሽ የ2 ለ1 ሽንፈት የገጠመው አይንትራኅት ፍራንክፉርት በበኩሉ 27 ነጥብ ይዞ 3ኛ ደረጃ ላይ አፍሯል ። ላይፕትሲሽ ተመሳሳይ 27 ነጥብ ይዞ በግብ ክፍያ በመበለጥ ደረጃው 4ኛ ነው ። ኪዬል እና ቦሁም በ5 እና 3 ነጥብ የመጨረሻ 17ኛ እና 18ኛ ደረጃ ላይ ሰፍረዋል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ